ምርኩዝም ኩራዝም የሆነ ልጃቸውን በአደባባይ የተነጠቁ እናት ልጄ ጥራኝ ይላሉ
አንድ ልጃቸው በአሸባሪው ህወሓት ሴት ታጣቂ በአደባባይ የተገደለባቸው አይነ ስውሯ እናት ወራሪው ቡድን ያለጧሪና ቀባሪ አስቀረኝ ይላሉ፡፡ ዞኑ ሰሜን ወሎ፣ ከተማው ደግሞ ላልይበላ ነው። በዕለተ እሁድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ፤ መልካሙ በቀለ፣ ከአቅመ ደካማ እናቱ ጋር ቤት ያፈራውን ሊቀምስ አብሯቸው ተቀምጧል። ቁርሱን አፉ ላይ ጣል እንዳደረገም አፍታም አልቆየም፤ ጠደፍ ብሎ ወጣ። መለስ እንደሚልና እንደሚያያቸው ያውቁ ስለነበር እናቱ ወይዘሮ ቦሰና ገላው፣ ቶሎ አለመመለሱን አልወደዱትም፤ በደከመና ቡዝዝ ባለ አይናቸው ፍዝዝ ብለው በር በሩን ያዩ ጀመር። ጧሪና ቀባሪ ልጃቸው ግን አልከሰት አላቸው። ከደሳሳ ጎጇቸው ደጃፍ ላይ ኩርምት ብለው ሳይነሱ የምሳ ሰዓት አለፈ። ተስፋ ሳይቆርጡ አንዴ ወደ ደሳሳ ጎጇቸው ገባ ይሉና ብዙም ሳይቆዩ ደግሞ ካዘነበለው የግቢያቸው አጥር ወጣ ብለው ያለወትሯቸው የናፈቁትን የልጃቸውን አይን ለማየት ተመኙ። የእናትነት አንጀታቸው ሲላወስ አንዳች የተፈጠረ ክፉ ነገር ይኖር ይሆን ሲሉም ክፉኛ ተጨንቀው ማሰብ ጀመሩ። የፈሩት ይወርሳል፤ የጠሉት ይደርሳል እንዲሉ፤ ጀምበር ከመጥለቋ በፊት 11 ሰዓት ላይ ጆሯቸውን የሚሰቀጥጥ፣ አንጀታቸውን ይበልጥ የሚያንሰፈስፍ፣ ቆሽታቸውን የሚያደብን መጥፎ ዜና ሰሙ። አይን አይኑን የሚያዩትና አይናቸው የሆነ ልጃቸው ከቤት እንደወጣ ወዲያው ሦስት ሰዓት ላይ አሸባሪው የሕወሓት ኃይል አደባባይ ላይ ረሽኖታል ተባሉ። ይህን ለእናቱ ምርኩዝም ኩራዝም የሆነ ልጅ ከተደፋበት ማንም እንዳያነሳው ተብሎ በአሸባሪ ቡድኑ ትዕዛዝ በመሰጠቱ፣ ማንም ደፍሮ ሊያነሳው አልቻለም። ይህም በመሆኑ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ድረስ በተደፋበት ቦታ ይቆያል። ከአሁን አሁን ይመጣልኛል ብለው ከጎጇቸው በር ላይ አይናቸውን ክርትት ክርትት ሲያደርጉ