ምርኩዝም ኩራዝም የሆነ ልጃቸውን በአደባባይ የተነጠቁ እናት ልጄ ጥራኝ ይላሉ

አንድ ልጃቸው በአሸባሪው ህወሓት ሴት ታጣቂ በአደባባይ የተገደለባቸው አይነ ስውሯ እናት ወራሪው ቡድን ያለጧሪና ቀባሪ አስቀረኝ ይላሉ፡፡
ዞኑ ሰሜን ወሎ፣ ከተማው ደግሞ ላልይበላ ነው። በዕለተ እሁድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ፤ መልካሙ በቀለ፣ ከአቅመ ደካማ እናቱ ጋር ቤት ያፈራውን ሊቀምስ አብሯቸው ተቀምጧል። ቁርሱን አፉ ላይ ጣል እንዳደረገም አፍታም አልቆየም፤ ጠደፍ ብሎ ወጣ። መለስ እንደሚልና እንደሚያያቸው ያውቁ ስለነበር እናቱ ወይዘሮ ቦሰና ገላው፣ ቶሎ አለመመለሱን አልወደዱትም፤ በደከመና ቡዝዝ ባለ አይናቸው ፍዝዝ ብለው በር በሩን ያዩ ጀመር። ጧሪና ቀባሪ ልጃቸው ግን አልከሰት አላቸው።
ከደሳሳ ጎጇቸው ደጃፍ ላይ ኩርምት ብለው ሳይነሱ የምሳ ሰዓት አለፈ። ተስፋ ሳይቆርጡ አንዴ ወደ ደሳሳ ጎጇቸው ገባ ይሉና ብዙም ሳይቆዩ ደግሞ ካዘነበለው የግቢያቸው አጥር ወጣ ብለው ያለወትሯቸው የናፈቁትን የልጃቸውን አይን ለማየት ተመኙ። የእናትነት አንጀታቸው ሲላወስ አንዳች የተፈጠረ ክፉ ነገር ይኖር ይሆን ሲሉም ክፉኛ ተጨንቀው ማሰብ ጀመሩ።
የፈሩት ይወርሳል፤ የጠሉት ይደርሳል እንዲሉ፤ ጀምበር ከመጥለቋ በፊት 11 ሰዓት ላይ ጆሯቸውን የሚሰቀጥጥ፣ አንጀታቸውን ይበልጥ የሚያንሰፈስፍ፣ ቆሽታቸውን የሚያደብን መጥፎ ዜና ሰሙ። አይን አይኑን የሚያዩትና አይናቸው የሆነ ልጃቸው ከቤት እንደወጣ ወዲያው ሦስት ሰዓት ላይ አሸባሪው የሕወሓት ኃይል አደባባይ ላይ ረሽኖታል ተባሉ።
ይህን ለእናቱ ምርኩዝም ኩራዝም የሆነ ልጅ ከተደፋበት ማንም እንዳያነሳው ተብሎ በአሸባሪ ቡድኑ ትዕዛዝ በመሰጠቱ፣ ማንም ደፍሮ ሊያነሳው አልቻለም። ይህም በመሆኑ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ድረስ በተደፋበት ቦታ ይቆያል። ከአሁን አሁን ይመጣልኛል ብለው ከጎጇቸው በር ላይ አይናቸውን ክርትት ክርትት ሲያደርጉ የነበሩ አዛውንት እናቱም የማታ ማታ በሰሙት የልጃቸው ሞት ቅስማቸው ተሰበረ። በአሸባሪ ቡድኑ ትዕዛዝ አስክሬኑ ቤት ገብቶ ለአፍታም ሳይቆይ ወዲያው ተካልቦ ወደማረፊያ ስፍራ በመሄድ አፈር እንዲቀምስ መደረጉን በተቆራረጠና ሐዘን በሰበረው ድምጽ ይናገራሉ።
የልጄን ሞት የሰማሁት 11 ሰዓት ላይ፤ የተቀበረውም ወዲያው ነው የሚሉት እናቱ፣ እርሱ ከተከራየው ቤት ሽምብርማ ከሚባለው አደባባይ ጎን በመሆኑ፤ ጨካኞችም የገደሉት እዛው አደባባይ ላይ ነው ይላሉ። ሆቴል ውስጥ ተቀጥሮ ራሱንም እርሳቸውንም የሚያስተዳድር ልጃቸው የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን ሁሉ ነገራቸው የሆነ ልጃቸውን በማጣታቸው ከእርሱ ድጋፍ ይልቅ ሐዘኑ ስሜታቸውን ስለጎዳው መቋቋም ተስኗቸዋል።
እኔ ታማሚ ነኝ፤ እግሬ አይሰራም፤ ልጄን ለምን ነጠቃችሁኝ ብዬ አልጠይቅ ነገር እነርሱ ዘንድ ማን ይቀርባል? አውሬውን መቅረብስ እንደምን ይቻላል? ልጄ ጠዋት ሦስት ሰዓት ከተደፋበት ማንም ሳያነሳው ውሎ የማታ ማታ ኬንዳ (ኬሻ) ብጤ አልብሰው ብቻ ቤቴ ውስጥ ገባ አድርገው ወዲያው አውጥተው ቀበሩት ይላሉ።
እማማ ቦሰና፣ ልጃቸው ወይ የመንግሥት ሠራተኛ አይደለም፤ ወይ ደግሞ የመንግሥት ወታደር አይደለም። ራሱንና ደሃ እናቱን የሚጦር ለፍቶ አዳሪ ነው ሲሉ ሲቃ እየተናነቃቸው ለምን ገደሉብኝ? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ዓይነ ስውር ነኝ፤ ለምኜ ነው የምበላው። ወትሮም ቢሆን ስራ ሰርቼ ለመብላት የማልችለዋ ብቻዬን ቀርቻለሁ። ልጄን ካጣሁ ቀን ጀምሮ የሚያጎርሰኝ ለነፍስ ያለ ሰው ነው። ቤቴ እንኳ የቆርቆሮ ልባስ የሚያደርግልኝ በማጣቴ የለበሰው ኬሻ ነው። ዝናብ ጠብ ሲል ይዘንብብኛል፤ ግድግዳው ሁሉ ይረጥባል። ከጣራው ላይ የተቀመጠው ኬሻ ከማርጀቱ የተነሳ ሽው የምትል ነፋስ እየቆነጠረች ወስዳ ጨርሰዋለች ሲሉ ነው ተስፋ በቆረጠ ድምጸት የሚናገሩት።

አሁን ከሐዘኔ ጋር ብቻዬን ቀርቻለሁ። ለመውለዱማ ሦስት ነበር የወለድኩት። አንዷ በቅርቤ የለችም፤ አንደኛውም ቢሆን ለራሱም የሚሆን አይደለም። ይኸኛው ከሆቴል ቤት ተላላኪ ሆኖ ደግፎ ይዞኝ ነበር። የምጽናናበት ምንም የለኝም፤ ጎረቤት እንዳልል የምታዪው ነው፤ ትተው በመሄዳቸው አካባቢው ኦና ነው ሲሉም ሐዘን በጎዳው ፊታቸው ላይ የወረደውን እንባ እየጠራረጉ ይናገራሉ።
ከዚህ በኋላ ምን ያህል ልኖር ብዬ ነው፤ ልጄ በጎንህ አድርገኝ እያልኩ እለምነዋለሁ፤ አምላኬንም ቶሎ ውሰደኝ ብዬ ነው የምጸልየው በማለት እማማ ቦሰና የመኖር ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ። ከዚህ በኋላ ቀባሪ የሌለኝ ነኝ፤ ሬሳዬንስ ማን ያወጣዋል? የኔ ኑሮ ከዚህ ወዲያ መላም የለውም። ከባዶ ቤት ተጎልቼ አይጥ የሚሯሯጥበትን ጣራ ብቆጥር ምን እፈይዳለሁ? ሞትም ብለምነው እምቢ አለኝ። ልጄ ምንም ሳያደርግ ‹ቁም! ተንበርከክ!› ብላ የገደለችው ሴት የሽብር ቡድኑ ታጣቂ መሆኗንም ለኢፕድ ተናግረዋል፡፡
ልጄ ሐዘኔን አስታቅፎ ከባዶ ቤት ቁጭ አድርጎኝ ሄደ ሲሉ ነው እማማ ቦሰና የተናገሩት። የጭካኔ በትሩ የከፋው የወራሪው ቡድን ልጃቸውን በአደባባይ ከመንጠቁ የተነሳ ዛሬ ያለጧሪ ቀባሪ ቀርተዋል። በርዶኛልም፤ ርቦኛልም። ቀኝ እጄ በአደባባይ ተቆርጦብኛል፤ መሸሸጊያ የሌለኝ ብቸኛ ነኝ በማለት ሐዘናቸውን አካፍለውናል።
Source:FBC

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa