በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የኢትዮጵያ ምርጫ ህግ ይሻሻላል - ፕሬዚዳንት ሙላቱ



የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለተኛ አመት የስራ ዘመን ዛሬ ተከፍቷል።

ከመክፈቻው በፊትም በቅርቡ በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ በነበረው ሁከት እና ግርግር እንዲሁም በአንዳነድ የሃገሪቱ አበበቢዎች ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

የምክር ቤቶቹን የስራ ዘመን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳነት ሙላቱ ተሾመ፥ ባለፈው ዓመት ሃገሪቱ በብዙ መስኮች ወደፊት ከመራመዷ ጎን ለጎን የተለያዩ ችግሮች የተከሰቱበት ወቅት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
 
በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ሁከቶችና ግጭቶች መቀስቀሳቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፥ በዚህም የበርካታ ዜጎችና የጥታ ሃይሎች ህይዎት መጥፋቱን ተናግረዋል።

ሃገሪቱ ባለፉት አመታት የገነባችው ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት እንዳስቻላት ጠቅሰው፥ በዚህ መስክ የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ይበልጥ ለማጎልበትና የፖለቲካ ምረሩን ለማስፋት በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጉን የማሻሻል ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
 
ያጋጠሙ ችግሮች፦ ሃገሪቱ ባጋጠማት የድርቅ አደጋ ሳቢያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ለርሃብ ከመጋለጣቸው ባሻገር በእንስሳት ሃብቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ጠቅሰው፥ መንግስት ችግሩን በራስ አቅም ለመፍታት ባደረገው ጥረት ሊደርስ ይችል የነበረን ሰብዓዊ ቀውስ ማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም መንግስት በራስ አቅም ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት ለጋሽ ሃገራት ከሰጡት እርዳታ ጋር ተዳምሮ የድርቁ አደጋ በዜጐች ላይ ጉዳት ሳያደርስ እንዲያልፍ ማስቻሉንም ነው የተናገሩት።

በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶች

ወቅታዊውን የሃገሪቱን ሁኔታ ባነሱበት ንግግራቸው፥ በህብረተሰቡ ዘንድ የተነሱ ፍትሃዊ ጥያቄዎችን ተገን በማድረግ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች ቅሬታን ወደሁከትና አውዳሚ እንቅስቃሴ ለመቀየር መረባረባቸውን ተናግረዋል።

በንግግራቸው ሃገሪቱ በእድገት ጎዳና መገስገስ መጀመሯን አንስተው፥ ይህን የማይደግፉ አንዳንድ ሃይሎች ሃገሪቱን ለማተራመስ በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ለበርካታ ዓመታት አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖባት በቆየችው ሃገር የተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለይ ደግሞ ወጣቶች የተሳተፉባቸው ሁከቶችና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡

በዚህ ሳቢያም የወጣቶችና ሌሎች ዜጎች እንዲሁም የፀጥታ ሃይሎች ህይወት መጥፋቱን አንስተዋል።
በዚህ ሳቢያም የዜጎች የዕለት ተዕለት እንቃሴ መስተጓጎሉንም ነው የተናገሩት፤ ችግሩን ለመፍታት የተሟላ የመፍትሄ ሃሳብ በማዘጋጀትና ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ የሌለው መሆኑን በመጥቀስ።
በተለይም ግዙፍ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች በራስ አቅም መገንባት መጀመራቸው ያልተዋጠላቸው እነዚህ ሃይሎች ሃገሪቱን ለማተራመስ በቀጥታ እየተረባረቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
 
በዚህም በሃገሪቱ በአሸባሪነት የተፈረጁት ኦነግና ግንቦት ሰባት ከግብፅ መንግስትና ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለሃገሪቱ ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ያላቸውን ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎችና ሌሎች ተቋማት በማጋየት ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል ነው ያሉት፡፡ 

እነዚህ ሃይሎች በቅርቡ ታላቁን የኢሬቻ በዓል ከማወክ ጀምሮ በልዩ ልዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያካሄዱት ውድመትና ቃጠሎ በማንኛውም ሚዛን ፍትሃዊነት የሌለው መሆኑንም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።
 
በመሆኑም መንግስት ይህን የመሰለው አፍራሽና ከባድ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ታዝሎ የመጣ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ እንዲመከትና ወንጀለኞቹም በጥብቅ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ለዚሁ ሲባልም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታውን ገምግሞ ተግባራዊ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡
ግብርና እና ኢንዱስትሪ
ሃገራዊ እድገቱን ለማስቀጠል ትልቅ ፋይዳ ባለው የግብርና ፕሮግራም ላይ ዘንድሮም ልዩ ትኩረት እንደሚደረግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፥ ጥሩ እድገት ሲያሳዩ የቆዩ የግብርና መስኮችን ለላቀ ውጤታማነት ለማብቃት መቀሳቀስ እንደሚገባ አንስተዋል።
በተለይም በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና በሰብል ምርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ የሰብል ምርት ካለው ፋይዳ አንጻር በሙሉ አቅም እንረባረባለን ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ባለፈም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ከፍተኛ ዋጋ ወዳላቸው ምርቶች ለማሸጋገር ቅድመ ሁኔታ የማሟላት ጉዳይ በእቅዱ መሰረት ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
ለዚህም በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ የሚለሙ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ደኖችና የእንስሳት ሃብት ልማት ተግባራዊ ይደረጋል።
ከዚሁ ጋር ተመጋጋቢ እንዲሆን የሚፈለገው የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማስፋፋት ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
ከእነዚህ መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አንዱ ሲሆን፥ በዚህ ረገድ በዋና ዋና ማዕከላት ላይ የሚነቡ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
 
ሃገራዊ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ካላቸው ተሳትፎ ባሻገርም፥ የውጭ ባለሃብቶች ለሃገራዊ ልማት ስትራቴጅው አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
 
በመሆኑም በሃገሪቱ ኢንዱስትሪያዊ ልማትን በማፋጠን ለማምጣት የሚፈለገውን ሽግግር አስተማማኝ ለማድረግ ለገጠር ኢንዱስትሪ ልማት የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
 
ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች፦ የሲቪል ሰርቪሱን ጨምሮ ሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተጨማሪ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡
 
የሃገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ ከእድገቱ ጋር ተመጋጋቢ በሆነ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆነ እንዲሄድ ለማድረግ በየወቅቱ የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ማስተካከያ ይደረጋል።

የምርጫ ህጉን ስለማሻሻል

ከፍ ሲል ከተገለፁት የህዝብን ተጠቃሚነት በተለይ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መብትና ጥቅም ከማስከበር በተጨማሪ የአገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በተለይም በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የአገሪቱን የምርጫ ህጋግ የማሻሻል ስራ ይከናወናል ነው ያሉት።

አገሪቱ የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ አገሮች እንዳለ የሚሰራበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ ነው የህጉማሻሻያ የሚደረገው ብለዋል።

ስለሆነም የምርጫ ህጉ የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓቶችን በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረና የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲስተካከል ይደረጋል፤ ይህም በፓርቲዎች መካከል በሚካሄድ የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛና አገራዊ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ ግልፅነትን የተላበሰ የድርድር ሂደት እንደሚፈፀም አስታውቀዋል

ህገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን በሚደነግገው መሰረት ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተገቢ ጥያቄዎች በዚህ በጀት ዓመት ውስጥ የተሟላ እልባት እንዲሰጣቸው ይደረጋልም ብለዋል።
 
ከዚህ ባለፈም በዘንድሮው ዓመት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመደንገግ የሚወጣውን አዋጅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋጆች ይወጣሉ ብለዋል ፕሬዚዳንት ሙላቱ፡፡

የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተመለከተ

የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መነሻ በማድረግና ከልብ በመቀበል መንግስት ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ራሱን ከዚህ ዝንባሌ ለማፅዳት ቁርጠኛ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
 
ከዚህ በመነሳት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስራውን በሚጀምርበት በሚቀጥለው ወር የፌደራል መንግስትን በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል፡፡
 
በዚህ መሰረት የመንግስት ስልጣንን ካለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ የሚገታና በውጤት አልባነት የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ መቆየት የማይቻል መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ የመንግስት ምክር ቤት የማደራጀት እንቅስቃሴ ይካሄዳል፡፡
 
የአርሶ አደሮች መፈናቀል

በከተሞች አቅራቢያ በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች የተከሰተው የአርሶ አደርና የአርብቶ አደሮች መፈናቀል ከሃገራዊ እድገቱ እና እየተስፋፋ ካለው የኢንዱስትሪና ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዘ መሆኑንም በንግግራቸው አንስተዋል።
በመሆኑም ዘመናዊ እርሻዎችና ትልልቅ ግድቦች መስፋፋታቸው ቀጣይ በመሆኑ፥ ሁኔታውን ከአርሶና አርብቶ አደሩ መብትና ጥቅም ጋር በተጣጠመ አኳኋን መፈፀም እንደሚገባ ገልጸዋል።
 
በተያዘው አመት ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል አቅጣጫ በመያዝ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ለማስፋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለይ ደግሞ አይቀሬ ከሆነው የከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ የገጠር መሬትን ለላቀ ጥቅም ለማዋል የሚደረግ እንቅስቃሴ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን መሰረታዊና ታዳጊ ጥቅሞች አሳልፎ በማይሰጥ መንገድ እንደሚፈፀም ይረጋገጣል፡፡
በዚህ ረገድ ክፍተት ያለባቸውን ነባር ህጎችና አሰራሮች በማስተካከል፣ በአፈፃፀም የሚታዩ ስህተቶችን ታግሎ በማረም፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና ከሁሉ በላይ ደግሞ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን በሚያሳትፍ አኳኋን እንዲፈፀም ይደረጋል፡፡
 
ከዚህ ባሻገር ግን ለሃገራዊ እድገቱ ካበረከቱት አስተዋፅኦ በላይ አላግባብ የመጠቀም አዝማሚያ የተጠናወታቸው ጥቂት ኃይሎች በመኖራቸው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ሊፈተሽ የሚገባው መሆኑን ነው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ያነሱት።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman