ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ1440ኛው ዓመተ ሒጅራ የረመዳን ወር ጾም ፍቺ፣ ዒድ አል ፈጥር በዓል ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት:
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ1440ኛው ዓመተ ሒጅራ የረመዳን ወር ጾም ፍቺ፣ ዒድ አል ፈጥር በዓል ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ለ1440ኛው ዓመተ ሒጅራ የረመዳን ወር ጾም ፍቺ፣ ዒድ አል ፈጥር በዓል ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ዒድ አል ፈጥር - የጾም ወር ማጠናቀቂያና መሸኛ በዓል ነው።
በረመዳን ወር መጨረሻ እና በሸዋል ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ የሚውል በዓል ነው ዒድ-አልፈጥር። በቅዱሱ የረመዳን ወር ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ሙስሊሙ ራሱን ከመብልና መጠጥ ከማቀብ ባለፈ በመልካም እና በጎ ተግባርም መትጋት ይጠበቅበታል።
በዚህ ረገድ፣ ነቢዩ መሐመድ (ሠለላ አለይህ ወሠለም) “አስከፊ ንግግር እና ተግባራትን ያልተወ ሠው ከምግብና ከመጠጥ መታቀቡ ብቻ በአላህ ዘንድ ከቁምነገር የሚገባ አይደለም” በማለት ትክክለኛውን መንገድ ማመላከታቸው በሐዲስ ሰፍሮ ይገኛል።
በመሆኑም በጾምና ሰላቱ፣ በምስጋናና በልግስና ታጅቦ ሠላሳ ቀናትን የሚዘልቀው የረመዳን ወር ነፍስን አለምላሚ ሥጋን ግን ጎሳሚ፣ ከዚያም በተጨማሪ ፈታኞቹ ቀናት ካለፉ በኋላ የሚመጣው አዲስ ቀን፣ የኢድ በረከትን የታደለና ድካምንም የሚያስረሳ ተደርጎ ይወሰዳል።
በእምነታችን የተነሳ ትዕዛዛቱን ለመፈፀም በጽናት የምንቀበለው መከራ ሁሉ ከባድ ቢሆንም ማለፉ ግን አይቀሬ ነው። ያልፋል። አስተላለፉ ግን ‹ሲምር ያስተምር› እንደሚባለው ምሕረትም ትምህርትም አግኝተንበት ነው። የረመዳን ወርና መሸኛው ኢድ አል ፈጥር በዓል ከመነሻ እስከመድረሻ ያለው ሥርዓት በእንዲህ ዓይነቱ በረከት የታደለ ነው።
የረመዳን ወር የጾምና የመታዘዝ፣ የድካምና የመፈተንም ወቅት ነው። ነገር ግን ከሚበላባቸውና ከሚጠጣባቸው ወሮች ይልቅ ቅዱሱ ወር ደግሞ እርሱ ነው። ይህ ወር በሥጋዊ ዕይታ ሲቃኝ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሁለት ጉዳዮችን በውስጡ አቅፎ የያዘ ይመስላል፤ ፈተናና በረከት።
ከጠዋት እስከ ማታ በጾም፣ በጸሎት እና በመልካም ምግባር ማሳለፍ ከባድ ፈተና ነው። በጾሙ ወቅት የሚገኘው ስጦታ ደግሞ በረከት ነው። አንድን ወቅት ጥሩ ጊዜና ጥሩ ወቅት ነው የምንለው እየተፈተን የምናልፍበት፣ አልፈንም የምንሸለምበት ጊዜ ሲሆን ነው።
ከእጭና ኩብኩባ ተሸጋግሮ ወደ ቢራቢሮነት ለመለወጥ እንደሚታገል ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ተንፏቃቂ ነፍስ፣ ክንፍ አብቅሎ የሚበር ነፍስ እስከመሆን ባለው ጉዞ በትግልና ፈተና ማለፍ ግድ ነው። ትግሉ ግን በረከት ያለበት ፈተና ነው።
ሀገራችን አሁን ያለችበት ወቅት የፈተናና የበረከት ወቅት ነው። ከነባርና ወቅት አመጣሽ ፈተናዎቻችን ተላቅቀን ለማለፍ የምናደርገው ትግል በፈተና የተሞላ ነው። ከባድና የማይቻል ቢመስልም ማለፉ ግን አይቀርም። ይህ ተጋድሏችን ብዙ ነገሮችን ተምረን፣ በብዙ ጠባዮቻችንም የተነሣ እስከ ተስፋ መቁረጥ አስመርረውን የምናልፍበት ጉዞ ነው።
ክፉ የተባሉትን ነገሮች ሁሉ ፈጽመናቸው ክፉ ከዚህ በኋላ አያሳየን የምንልበት የፈተና ወቅት ነው። ወቅቱ ግን የፈተና ብቻ አይደለም። የትናንቱን እንደ ወንፊት የምናጠራበት፣ ለነገውም ኃይል የምንሰንቅበት እንጂ።
የተጠራቀመውን ችግር ሁሉ ጠርገን የምንጨርስበት የጽዳት ወቅት ነው። ለዚህም ነው ይህን የታሪክ ወቅት ፈታኙ ቅዱስ ጊዜ የምንለው። ቀዶ ጥገና ለሚያደርግ ሰው ያ ጊዜ ፈታኙ ጊዜ ነው። ሰመመኑም የሞት ታናሽ ወንድም ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ለሕመምተኛው በሽታውን ነቅሎ የሚገላገልበት የበረከቱ ጊዜም ነው። ለሀገራችንም እንዲሁ ነው። ይህ ወቅት ውዲቱ ሀገራችን በሁሉም መስክ ከባድ ሕክምና የምታደርግበት ፈታኙ ጊዜዋ ነው። ግን የተሻለ መድኃኒትና ጤና የምታገኝበት ቅዱሱ ጊዜዋም በዚህ ውስጥ ተፀንሶ ይወለዳል።
የዒድ በዓል ከመከበሩ በፊት ባሉት የመጨረሻ ቀናት ሙስሊሞች ዘካት አል ፈጥርን ማውጣት አለባቸው። ዘካት ለድኾች የሚሰጥ እርዳታ ነው። ይህ ዘካት ከራስ በፊት ለሌላው ማሰብን የሚያስተምረን ሥርዓት ነው። ያውም በሁለንተናዊ ዐቅሙ ከኛ የሚያንሰውን ሰው በማሰብ። በሀብት፣ በዕውቀት ወይም በአካላዊ ዐቅም ሊሆን ይችላል። ይህንን ወገን ለማስቀደም ነው የፈጥር ዘካ ከዒድ በፊት መከናወን ያለበት።
የአንድ ማኅበረሰብ የሥልጣኔ መገለጫዎች ከሆኑት ነገሮች አንዱ በሁለንተናዊ መልኩ የተጎዱ የማኅበረሰቡን ክፍሎች ለመደገፍ የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት እና ተግባራዊ ለማድረግ መቻሉ ነው። አካል ጉዳተኞችን፣ ድኾችን፣ ዐቅመ ደካሞችን፣ አረጋውያንን፣ ሕጻናትን፣ የተገለሉ ማኅበረሰቦችን ለመደገፍና ማኅበረሰባዊ ተሳትፏቸውን ከፍ ለማድረግ ምን እየሠራን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን።
እንደ ዒድ ያለውን የደስታ ወቅት በሚገባ ለማጣጣም ከእኛ በፊት መቅደም ያለባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ማየት፣መጎብኘትና መደገፍ አለብን ። የእኛ አውራ ዶሮ ሌቱ ወደ ንጋት የመሸጋገሩን ብሥራት ከእኛ በተጨማሪ ለሌሎች መንደርተኞችም በአኩኩሉው ማገልገል እንደሚችል ሁሉ እኛም በእምነት አስተምህሮቱ መሠረት ዘካቱል ፍጡር በማውጣትና የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት ድርብ ድርብርብ ተጠቃሚ እንሁን።
የዒድ በዓል በሚያስገርምና በሚያስደንቅ መልኩ የአዲሶች ኅብረትና አንድነት ግጥምጥሞሽ ነው ። ከአዲስ ጨረቃ መወለድ፣ ከአዲስ የንጋት ጀንበር መፈጠር፣ ከወርቃማ ጮራዎች መፈንጠቅ ጋር በመደመር አዲስ ቀንና አዲስ ወር በአድማሱ ላይ በበዓል ድባብ ይዘረጋል።
የረመዳን ወር የጾም ፍቺ እና የዒድ አል-ፈጥር በዓል ሠላት በአብሮነት እና በአንድነት በጀምአ የሚሰገድበት ወቅትም ነው።
በዓለም ዙሪያ ከቢሊየን በላይ በሚሆኑ ሙስሊሞች በተመሳሳይ ቀን በሚከበረው የዒድ በዓል ጀምአና አብሮነት ከምንም ጊዜ በላይ ይፈለጋል፣ይፈቀዳል፤ ይወደዳል። በዓሉ ለብቻ አይከበርም።
በየአካባቢው ያለውን ሕዝብ ሁሉ ሊሰበስብ ኢትዮጵያ: በሚችል ቦታ ላይ በጀምዐ በመስገድ እና ተክቢራ በማሰማት ይከበራል። በመንደር፣ በሰፈርና በቤት ውስጥም ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት ከወዳጅ ዘመድ በተጨማሪ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር በመሆን በሃላል ምግብና መጠጥ በዓሉን በአንድነትና በጋራ በደስታ ያከብሩታል፣ ያሳልፉታል።
ኢትዮጵያውያን በሚከተሉት ሃይማኖት ሳቢያ በመካከላቸው የሚለያይና የሚያራርቅ ግንብ ከመገንባት ይልቅ እምነታቸውን በየግላቸው በመያዝ በአንድነትና አብሮነት ዘመናት የተሻገሩ ታላቅ ሕዝቦች ናቸው።
የኢትዮጵያን ችግሮች ለማለፍና ከደስታው ወቅት ለመድረስ ጀምዐ ኅብረትና አንድነት ወሳኝ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ዛሬ እንደ ዒድ ጀምዐ ያለ አንድነትን ትፈልጋለች።
ከባድ አቀበት በመውጣት ላይ በመሆኗ ጉልበት እንድታመጣ በአንድ ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ሳንባዎቿ መተንፈስ ይኖርባታል። ለዒድ ሰላት ሕዝበ ሙስሊሙ አንድ ሆኖ ማነህ? ማነሽ? ከየት ነህ? ከየት ነሽ? ሳይል ለአንድ ዓላማ በጀምዐ እንደሚወጣው ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ማነህ? ማነሽ? ከየት ነህ? ከየት ነሽ? ሳንል ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ አንድ ሆነን ከምንሰለፍበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ለሀገራዊ ጥሪ ሀገራዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል። በሀገራችን የሚከሠቱ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግሮች ሁሉ እንደ ረመዳን ጾም ቀናቸውን ቆጥረው ይጠናቀቃሉ። ያልፋሉ።
ኢትዮጵያም እንደ ዒድ የደስታ ዘመን ይጠብቃታል። ረመዳን ምንም እንኳን ፈታኝና ከባድ ወቅት ቢሆንም ብዙ አረጋውያን ሙስሊሞች ግን ሲያልቅ ትዝታው በአእምሯቸው ተስሎ ይቀራል።
ጽናትና ቆራጥነታቸውን ያስታውሱበታልና። ይህ ሀገራችን እያለፈችበት ያለችው ወቅትም ያልቃል። ይሸኛል። በጽናትና በሀገራዊ ስሜት የጸኑ ዜጎቿ ሁሉ ወቅቱን በተጋድሎ ታሪክ ትናንት በማለት የሚያስታውሱት ትዝታ ይሆናል።
በመጨረሻም ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሙሉ ለ1440ኛው የዒድ አል - ፈጥር በዓል እንኳን አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የደስታ የሰላም፣ የይቅርታ ፣ የፍቅር እና የአንድነት እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ። ኢድ ሙባረክ! #PMOEthiopia
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ