ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕት

ክብርት የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ለአንድ እራት አምስት ሚሊዮን ብር የከፈላችሁ እውነተኛ የኢትዮጵያ ባለሃብቶች ዛሬ የዚህ በአል እውነተኛ ታዳሚ በመሆናችሁ ለእናንተም የሚገባችሁን ክብር ሰጥቼ መጀመር እፈልጋለሁ።
ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ባለበት ሀገር ውስጥ 16 ሰዓት እየሰራችሁ የቤተመንግስቱን ፕሮጀክት በስድስት ወር ጊዜ ማጠናቀቅ ለቻላችሁ የፕሮጀክት ኃላፊዎች እንደምንችል ለሕዝብ ልምድ ያሣዩና ለእኛም ተስፋ የሆኑ ሙያተኞች በእኛ መካከል አላችሁ። የሚገባችሁን ክብር ሰጥቼ ማለፍ እፈልጋለሁ።
በለውጥ እርምጃዎቻችሁ ታጅቦ ላይመለስ በማለፍ ላይ ያለው አመት ከእድሜው ቁጥር በላይ ታላቅ ፈተና የደቀነብን ግን ደግሞ ኢትዮጵያ በፈተና የማትወድቅ መሆኗን ዳግም ያስመሰከረ ዘመን ነበር 2011 ዓ.ም።
ያሳለፍነው አንድ አመት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ እንደሀገርና ሕዝብ ለዘመናት ተጭኖ የነበረው ድህነት፣ጉስቁልና የመብት ረገጣና አፈና ጦርነት የመበታተን አደጋ በዘላቂነት እንዲወገድ እንዲሁም የዘመናት ጸረ-ዴሞክራሲያዊ የቁልቁለት ጉዟችን እንዲገታ የጦርነት ታሪካችን ጦርነት ሆኖ እንዳይቀጥል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ጋር እንዲታረቁ ፤የዜጎች ክብርና ሀገራዊ አንድነት እንዲረጋገጥ የአንድ አመት ሳይሆን የአስር አመቱን ውዝፍ እዳ የተጋፈጥንበትም አመት ነበር።
ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ከለውጥ በፊት የነበሩባቸው አያሌ ጭነቶቻቸው በለውጡ ከጭንቅላታቸው ላይ የተራገፈላቸው ቢሆንም በምትኩ ካረፉባቸው አዳዲስ ጭነቶች ገና አልተገላገሉም።
በሕዝብ ትግል ከመጣው ለውጥ በፊት እንደነበሩት በርካታ አመታት በውስጥና በውጭ ግልጽ የሆነ ጦርነት በሀገር ደረጃ ባይኖርም ሰላሙ እረፍት ከሚሰጥበት ዴሞክራሲው ሙሉ በሙሉ ከአፈና የተላቀቀበት፣ ኢኮኖሚው ከጥቂቶች ተጠቃሚነት በዘለለ ብዙኃኑን ተጠቃሚ ወደሚያደርግበት ተስፋ ሰጭ ብልጽግና ገና አልተሸጋገረም። በመሆኑም ሀገራችን ከሀዘን እስከ ደስታ፤ ከተስፋ ማድረግ እስከ ተስፋ መቁረጥ፤ ከመደመም እስከ መቆዘም፤ ከማድነቅ እስከ መሳቀቅ፤ከፌሽታ እስከ ዋይታ፤ ከጥግ እስከ ጥግ ያሉ የሥሜት ዋልታዎችን እየረገጠች አልፋ ነው ዛሬ ከአዲስ አመት ዋዜማ የደረሰችው። እንኳን ለአዲሱ አመት ዋዜማ በሰላም አደረሳችሁ ።
አዲስ ዘመን ማለት ያልተነካ አዲስ ሀብት ማለት ነው። ያንን ሀብት በትክክል መጠቀም ማባከንም ይቻላል። የዘመን መለወጫ ቀን ማለት ከሁለቱ አንዱን የምንመርጥበት እለት ማለት ነው። ኢትዮጵያውያን መልካሙን በመምረጥ ከጎናችን እንደምትቆሙ ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን ማለት ገና ምንም ያልተጻፈበት ባለ 365 ገጽ መጽሀፍ ነው። በዚህ መጽሐፍ ላይ አኩሪም አሳፋሪም፤ አስደሳችም አሳዛኝም፤ ጠቃሚም ጎጂም ታሪክ መጻፍ ይቻላል።
የዘመን መለወጫ ቀን ማለት ከሁለቱ አንዱን ለመምረጥ የምንወስንበት ቀን ማለት ነው። የመጀመሪያው ገጽ የሚጀምረው ነገ በመሆኑ የነገ ሥራችሁን ዛሬ መወሰን ከመላው ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ይሆናል።
ጊዜ ወደፊት ብቻ ነው የሚሄደው። የአንድ አቅጣጫ ተጓዥ ባቡር ነው። መጠቀም እንጂ በራሱ በአይነቱ ማጠራቀም የማንችለው ሀብት ነው። አካባቢያችን በሙሉ ይቀየራል። የተፈጥሮን ሕግ ያከብራል።ወንዙ ይጠራል።አበባው ያብባል። ተደብቀው የነበሩ እንስሳትና አራዊቶች ይወጣሉ፤ አዝመራው ያሽታል፤ነፋሱ ያውዳል፤ሰማዩ ይጠራል፤ክረምቱ ይወጣል።
በክረምት የሚሰራን በበጋ ፣በበጋ የሚሰራን በበልግ፣ በበልግ የሚሰራን በጸደይ መስራት አይቻልም። በወቅቱ መጠቀም የሚቻለው ወቅቱን አስቀድሞ አውቆ ፣ በሚገባ አቅዶ፣ ተዘጋጅቶ፣ መስራት ሲቻል ብቻ ነው።
2012 ዓ.ም የመጪውን አስር የብልጽግና አመታት አቅጣጫ ቀይሰን የምንተምበት የቀጣይ መቶ አመታት የሥልጣኔ መንገድ መሰረት የምጥልበት ወሳኝ እጣ ፈንታችን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ለሚሉ ደግም ተሻግረን የምናሳይበትና የምናረጋግጥበት አመት ነው።
በቀጣዩ አመት ከድህነት ጋር ለዘመናት ያቆራኘንን ልማድ እና ተረክ ትተን የብልጽግናን ተረክ ከአዲስ ማንነት ጋር በማጣመር ወደ እምርታዊ የለውጥ ሂደት የምንገባበት የጅማሮ አመትም ይሆናል። የብልጽግና መንገዳችን በሞራልና በሥነምግባር ተመርቶ፣በሐሳብና በእውቀት ብርሃን ታጅቦ ፣በነዋይና በቁስ ሀብት ተከቦ በተደላደለ መሰረት ላይ ከስር ጀምሮ እንዲገነባ በጥንቃቄ በመታቀዱ በተግባር ሂደትም የታገዘ በመሆኑ በቀጣይ አስር አመታት እድሜ ወደ ብልጽግና የሚመራን ብቻ ለመቶ አመታት ስልጣኔ የብልጽግና መንገዳችን የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ የቀና ጉዞ ለመጀመር ነገ ‹‹ሀ››ብለን የምንጀምርበት ይሆናል።
የብልጽግና መንገዳችን በቀጣይ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ በ2030 ከአፍሪካ ከአንድ እስከ አምስት ከፍተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ ኢትዮጵያ የምትመደብበት ይሆናል።
አምናለሁ አብዝቼም ተስፋ አደርጋለሁ። የዛሬ ሕጻናትና ወጣቶች የዛሬ አስር አመት የሚደርሱበትን ። በጎ እድል ከእነርሱ አስር አመት በፊት የነበሩ ልጆችና ታዳጊ ወጣቶችን ዛሬ ከተጋፈጡት ፈተናና ትግል ጋር ማነጻጸር እንኳንም የመረጣችሁትን የብልጽግና መንገድ በትጋት ተግባራዊ አደረጋችሁ በማለት ያመሰግኑናል።

ዘመን ማደስና በታደሰ ዘመን መኖር ይለያያሉ። በታደሰ ዘመን መኖር የተፈጥሮ ግዴታ ነው።ልናስቀረው አንችልም። የእኛን ጥረትም አይፈልግም። ሰው ብንሆንም ባንሆንም አይቀርልንም።ዘመን ማደስ ግን የጀግንነት ስራ ነው። ሰው የመሆን ተግባር ነው።
ኢትዮጵያውያን ሰው የመሆን ተግባር ብቻ ሳይሆን ጀግንነታችንን ዳግም ለአለም ማስመስከር ይገባናል። ማንኛውም ሰው በሰው ላይ የሚካሄድ ተግባር ሁሉ የሰውየውን ሕልውና የማይነካ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል።ሕክምና ሕክምና የሚሆነው የታማሚውን ሕይወት በሚያሥቀጥል እንጂ በሚያጠፋ መሆን የለበትም።መዝናናት፣መማር፣ሥራና ሌላውም ሁሉ እንቅስቃሴ ከሕልውና ጥፋት ባነሰ ሁኔታ መከናወን ይኖርበታል።
የኢትዮጵያን ሕልውና የሚገዳደር ማንኛውም ሙከራ ወይም ጥረት ሕልውናን የሚያጠፋ ተፈጥሮን የሚቃረን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በመደመር የሚከላከሉት ይሆናል።
ማንኛውም የሚደረግ እንቅስቃሴ የሀገርን ሕልውና የማይነካ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል። በዘመን መለወጫ አካባቢ የምናየው የተፈጥሮ ሂደት ይሄንን ነው የሚያረጋግጠው።ተፈጥሮ ራሷን በራሷ ለአደጋ አታጋልጥም ።ራሷን በራሷ ጠብቃ በአንድ በኩል ያለውን ችግር በሌላ በኩል አቃንታ ነው የምትኖረው።
ሰዎች በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሱት አደጋ እንጂ ተፈጥሮ ራሷን ለሕልውና አደጋ አታጋልጥም። ማንም የተፈጥሮ ዜጋም የተፈጥሮን ሕልውና አይጋፈጥም።ተፈጥሮ ራሷም።ሀገርም እንዲሁ ናት።
በመጪው ዓመት ቅድሚያ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ሌላው ጉዳይ በራሳችን ልቦናና አዕምሮ ውስጥ ያለውን ጸጋ ተጠቅመን የሰላም መሰረት የሆነውን ፍቅርን መተባበርን፣ ቅንነትን ፣ትህትናን፣ ደግነትን በማብዛት ጥላቻን ከላያችን ማራቅ ብቻ ሳይሆን ውስጣችንን የሚበላ መርዝ መሆኑን አምነን ከውስጣችን ማጥፋት ይኖርብናል። ጥላቻ ሰውን ያጠፋል፤ ፍቅር ግን ሰውን አልፎ ሀገርን ያድሳል። ይገነባልም።
ሰላም የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም። ሰላም በፍቅር እንጂ በጠመንጃና በታንክ ኳኳታ አይረጋገጥም። ከቦምብና ፈንጂ ፍንዳታ አይመነጭም ። ሰላም መሰረቱ ምንጩም በራሳችን ባለቤትነት ስር ካለው ልቦና ከሚፈልቀው ፍቅር ብቻ ነው የሚገኘው ።
በአዲሱ ዓመት ሀገራዊ ሰላም መለያችን ሆኖ ሊበቅልና በፍካት ሊገለጥ ይገባዋል። በሀገራችን ሰላም ፍቅር ጎህ መቅደድ ይኖርበታል። እያንዳንዳችን በሀገር ደረጃ የምህረት ቀስተ ደመና እንዲዘረጋ ህዝባችንም የተስፋና የሰላም አክሊል እንዲጭን የየበኩላችንን አስተዋጽኦ ከማድረግ ባሻገር አብሮነትና በአንድነት መቆም ይኖርብናል።
ተስፋ የሚኖረን በዙሪያችን ሰላም በልባችን ፍቅርና ምህረት ሲመላለስ ብቻ ነው። ሰላም በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ አለ። ሰላም በእያንዳንዳችን ቤት ውስጥም አለ። ሰላም በእያንዳንዳችን ደጃፍ አለ። በፍቅር በለጋስነት ወደ መንደር ወደ ሀገር እንውሰደው። በፍቅር በቅንነት ወደ ህዝብ እናሻግረው። የተጠራቀመ የውሀ ጠብታ ተሰባስቦ ጅረት ፤ ጅረትም ተሳባስቦ ወንዝ በመሆን አቅም እንደሚፈጥር ሁሉ እያንዳንዳችን ለሰላም መስፈን ከራስ ወደ ቤተሰብ፤ ከቤተሰብ ወደ ማህበረሰብ ከማህበረሰብ ወደ ህብረተሰብ በማሻገር በመደመር እሳቤ ሀገራዊ ገጽታን ብናላብሰው የሰላም ባለቤቶች እንሆናለን። እንደ ሀገር ተስፋ የሚኖረን ሰላም ሲኖረን ብቻ ነው።

ያለፈው ዓመት ብዙ እጆቻችን ውስጥ የገቡ ድሎችን ካጋጠሙን አያሌ ችግሮች ጋር ተደባልቀው ደስታና ሀዘን ተስፋና ፍርሀት ድልና ትግል የተፈራረቁባቸው ነበሩ። መጪው ዓመት ግን ዛሬ ችግር የሆኑብን ፈተናዎችን ቀውስ ውስጥ ሊጨምሩብን ነው ብለን የፈራናቸውን ተግዳሮቶች በፍጥነት ወደ ዕድል መሰላሎችና ወደ ክብር መዳረሻ ዕድሎች የምንቀይርበት ይሆናል።
በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያን ለውጥን ለመጀመር ቀዳሚዎች፤ ለውጥን ወደ ዘላቂ ስኬት ለማሸጋገር ግን ውራዎች ተብልን የምንወቀስበትን ምዕራፍ ዘግተን መቻላችንን በመቻል ፣ በመሥራት የምናሳይበት ይሆናል ይገባልም። በአለማችን የዲሞክራሲ ችግኝ ተተክሎ እንደጸደቀበት ሂደት ሁሉ በእኛም ሀገር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጅማሮዎችን እንዲያብቡ ምህዳሩም እየሰፋ እንጂ እየጠበበ እንዳይሄድ የተሻለ እንጂ የከፋ ዘመን ተመልሶ እንዳይመጣ በሥርዓትም ፣በተቋምም ፣ በመጠናከር እውነተኛ ሽግግርን ለልጆቻችን ማረጋገጥ ይኖርብናል።
መጪው ዓመት ያለፈውን እያስታወስንና እያወሳን የምንጋጭበት ሳይሆን መጪውን እያለምንና እየተለምን በአንድነት በፍቅር ተደምረን የምንፈስበት ጨርሶ የመጀመር ዓመት ይሆናል።
ኢትዮጵያ ሰላምና ደስታ እንድትሆን ለሌሎች የሰላምና የደስታ ምክንያት እንሁን። ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ ሌሎች እንዲሳካላቸው ምክንያት እንሁን ። ኢትዮጵያ እንድትከበር ሌሎችን እናክብር ። ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ሌሎች እንዲቀጥሉ እንትጋ። ኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነቷ እንዲቀጥል ከእኛ ከሚለዩ ጎረቤቶቻችን የሥራ አጋሮቻችን ጋር በአንድነትና በፍቅር ለመኖር ዛሬ እንወስን።
ቀጣዩ ዓመት ታላላቅ ሀገራዊ ተግባራትን የምናከናው ንበት ነው። መጪው ዘመን ሀገራችንን ወደ ተሻለ ዕድል የምናሸጋግርበት ወሳኝ ዓመት ነው። መጪው ዓመት የመፈጸም ይሆናል። መጥራት፣ በጊዜ፣ በታሰበው ዋጋና ዕቅድ ማጠናቀቅ እንጀምራለን። የጀመርነውን የለውጥ ሂደት ከታሰበበት ግብ እና የስልጣኔ ጎዳና ጋር የምናዋህድበት ዘመን ይሆናል። የጀመርነውን የእርቅና ሰላም ሂደት ተጠናቆ ሰላምን ባህል የምናደርግበት ዘመን ይሆናል። ባቀድነው መሰረት የምናካሂደው ምርጫ የሀገራችንን የዲሞክረሲ ታሪክ ወደ ማይወርድበት ከፍታ የሚያደርስ ዘመን ይሆናል።
በየሥፍራው ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት የሚገቡበት ዘመን ይሆናል። የጀመርነውን የአረንጓዴ አሻራ ከችግኝ ወደ ዛፍ ለማሸጋገር የምንከባከብበት ዘመን ይሆናል። ከተሞቻችንን የማጽዳትና የማደስ ጅማሮ ከዘመቻ ወደ ቋሚ ባህልነት የሚለወጥበት ዘመን ይሆናል። በየከተሞቻችን ውስጥ የሚታዩት ጅማሬ ግንባታዎች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት የሚገቡበት ዘመን ይሆናል። በግልና በቤተሰብ በከተማና በክልል የተጀመሩ መልካም ስራዎች ዳር የሚደርሱበት ሰው ሁሉ የጀመረውን ለማጠናቀቅ ቃል የሚገባበት ጊዜም ይሆናል። የማንፈጽመውን የማንጀምርበት ከገባነው ቃል ሳንዛነፍ ያቀድነውን የምንፈጽምበት ዓመት ይሆናል። በግለሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ ሁላችንም የቀና ጉዞ የምርጫችንና የስራ፣የድካም ፍሬ ውጤቶቻችን ይሆናሉ።
መልካም ነውና ሰላምን መርጠናል ።ዲሞክራሲና መደመርን ህብረትና አንድነትን መደጋገፍና መተጋገዝን ለሀገራዊ ብልጽግና ተመራጭ መንገድ አድርገን ይዘናል። በጠፍ በሀገራዊ አፈር ላይ የተከልናቸው ችግኞች ወደ መሬት ማህጸን ጠልቀው በግንድ ቅርንጫፎቻቸው ደግሞ ከፍ ብለው አፍርተው ይታዩ ዘንድ ተስፋ እናደርጋለን። ህጻናት ህልማቸውን ፣ ልጆች ፍላጎታቸውን ፣ወጣቶች ተስፋቸውን ፣ጎልማሶች ዕቅዳቸውን ፣አዛውንቶችም ፍጻሜያቸውን የሚኖሩባት አንዲት የተባበረች ለልጆቿ ሁሉ የምትመች ሀገር አብረን የምንፈጥርበት እንዲሆንልን እንመኛለን ፤ ተስፋም እናደርጋለን ።
ኢላማውን መምታት የሚሻ ቀስት የሚያነጣጥረው በኢላማውና በግቦቹ ላይ እንጂ በራሱ በቀስቱ ላይና በደጋኑ ላይ አይደለም። እኛም ከዚሁ ትምህርት ብንወሰድ መልካም ይሆናል። ምንም ልንለውጠው ከማንችለው ትናንት ይልቅ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ልናደርግበት በምንችልበት ነገ ላይ እንረባረብ ። ስለትናንትና አበክረን ስንናገር ዛሬና ነገ እንዳያመልጡን እንንቃ። መልካም አዲስ ዓመት ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ። ቀጣዩ አዲስ ዓመት ለኢትዮጰያ የብልጽግና ዘመን ይሆናል፤ አመሰግናለሁ።

መስከረም 1ቀን 2012 ዓ.ም

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman