የውህደቱ ዓላማና አስፈላጊነት
የውህደቱ ዓላማና አስፈላጊነት
ስለ አዲሱ ውህድ ፓርቲ በተሻለ ለመገንዝብ ይረዳ ዘንድ አላማውና አስፈላጊነቱ እንደሚከተለው በስፋት ተተንትኖ ቀርቧል፡፡
የሳምንት መወያያ ርዕስ ላይም ስለ ውህደቱ ላነሳችው ስጋትና ጥያቄዎች በተወሰነ መልስ ይሆናችሁል፡፡
በተከታታይነትም ግልጽነት የመፍጠር ስራ ይቀጥላል፡፡
መልካም ንባብ፡፡
1. ግንባሩ ተልዕኮውን በማጠናቀቁ፣
ኢህአዴግ በሚመሠረትበት ወቅት የብሔር ጭቆናን ለማስቀረትና የብሔር ጥያቄ ለመመለስ የተፈጠረ ስትራቴጂካዊ ግንባር ነው፡፡ የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት ፀድቆው ዲሞክራሲያዊና ፌደራላዊ ሥርዓት እውን ከሆነ በኋላ የብሔር ብሔረሰቦች እራስ በራስ የማስተዳደር መብት፣ ቋንቋ፣ ባህል እና በማንነት የሚኮሩበት ህገ-መንግስታዊ መብቱ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ግንባሩ የተፈጠረበት ዋንኛውን ዓላማ አሳክተዋል ማለት ይቻላል፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች በዚህ ህገ-መንግስት መነሻ እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መብት በመጎናፀፋቸው በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ይኸው ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የስርዓቱ ዋና መለያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን ያልተገደበ መብታቸውን መሰረት ያደረገ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር፣ አደረጃጀትና አሰራር ማቋቋሙ ነው፡፡
በአብዛኛው የዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየው መሰል አደረጃጀቶች ማለትም (የግንባር፣ ንቅናቄ፣ ነፃ አውጭ ወዘተ) ባለው ሥርዓት ላይ በማመፅ በትጥቅ ትግል ወይም በሌላ አግባብ የሚታገሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢህአዴግም የደርግ ስርዓት በትጥቅ በማስወገድ ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት መመስረት ነበር፡፡ አደረጃጀቱ በዚያን ወቅት ተገቢ ቢሆንም ላለፉት 27 ዓመታትም በዚሁ መቀጠሉ በተለያዩ ጉዳዮች አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ ስለዚህ የግንባር አደረጃጀቱ ተልዕኮውን አሳክቶ የጨረሰ ብቻ ሳይሆን ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይራመድ በመሆኑ ወደ አንድ ወጥ ፖርቲ መምጣት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ጭምር ነው፡፡
2. አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ መፍጠር፣
ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሄሮችና ሃይማኖቶች መገኛ ሆና ሳለ ይህን በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻሏ ብሄረ መንግስት ግንባታዋ ረጅም ጊዜን ወስዶባታል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንት ደግሞ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማህበረሰብ የመፍጠር ሂደት ችግር መሆኑን በመለየት ህገ-መንግስቱ ሲፀድቅ ይህን ዓላማ መሰረት ያደረገ ግብ እንዲቀመጥ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይህን አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት የወሰኑት በራሳቸው ፍላጎትና በነፃ ፈቃዳቸው ላይ ተመስርተው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት አላማቸው የሚሳካው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሲከበሩ ብቻ ነው፡፡
አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር የሚፈጥሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን መቅረፅና ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም የኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እንዲጠናከር የዜጎች በፈለጉት አካባቢ የመንቀሳቀስ ነፃነት ያለምን ገደብ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡
በህገ-መንግስቱ ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጐት አንድ ጠንካራ እና ዲሞክራሲያዊ ሀገር የመፍጠር ራዕይን እውን ለማድረግ ይህ አደረጃጀት አብሮ የማይጣጣም በመሆኑ መሪ ድርጅቱ አንድ ሳይሆን አንድ የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር ስለማይቻለው አንድ ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ የመፍጠር አስፈላጊነት በእጅጉ የጐላ ያደርገዋል፡፡
3. ወቅታዊ የብሔር ፅንፈኝነት ጫፍ የረገጠ መሆኑ ፣
በሀገራችን የቀድሞ ስርኣቶች የብሄር ብሄረሰቦች መብት አለመረጋገጥ ምክንያት ትግል ተካሄዶ ኢህአዴግ ደርግን በማስወገድ የእኩልነት መብት የሚሰጥ ህገመንገስት በመረጋገጡ የብሄር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የተደረገ ቢሆንም የብሄር መብትን ከአገራዊ አንድነት ጋር አጣጥሞ ባለመሄድ ምክንያት ብሄርተኝነት እየተስፋፋ አሁን ላይ ጫፍ የደረሰበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡
ፅንፈኛ ብሄርተኝነት በዘመነ አለማቀፋዊነት ልዩነቶችን አቻችሎ ከአብሮነትና ከዴሞክራሲያዊ አንድነት ሊገኙ የሚችሉትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ጸጋዎች ከማሳደግ ይልቅ በተቃራኒው ይጓዛል፡፡ በዚሁ የጥርጣሬና የጥላቻ መንፈስ ከጋራ ልማቱ በጋራ መጠቀም እየተቻለ እንዳይሳካ ያደርጋል፡፡
በመሆኑም ህዝብን በድህነትና በኃላቀርነት የማስቀጠል አደጋ ያስከትላል፡፡ ፅንፈኛ ብሔርተኝነት አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ አድርጎ ከማየት የሚነሳ አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ የአንደኛውን መልማት የሌላኛው ድህነት አድርጎ የሚመለከት ነው፡፡ የአንደኛው ህዝብ መብት መረጋገጥ የሌላኛውን መብት እንደሚነፍግ አድርጎ ይመለከታል፡፡ ይህም በመሆኑ ከመነሻው ዴሞክራሲያዊ ውይይቶችን ቀርቅሮ ይዘጋል፡፡
ችግሮችን ሊፈታ የሚፈልገው በፀረ-ዴሞክራሲና በአፈና አግባብ ነው፡፡ ክርክሮችና ውይይቶች እንዲበራከቱ አይፈቅድም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ውይይት፣ የአብላጫ ወሳኝነት፣ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባሉ ነገሮችን አይቀበልም፡፡ የስርዓት አልበኝነትና የፀረ-ዴሞክራሲያዊያን መንቀሳቀሻ ማዕከል ይሆናል፡፡
ፅንፈኝ ብሔርተኝነት ተሰባጥረው የሚኖሩ ህዝቦችንና አንድነታቸውን በጥላቻ ይመለከታል፡፡ በህዝቦቹ መካከል ጥላቻና አለመተማመን እንዲሰፍን ይሰራል፡፡ በህዝቦቹ መካከል ልዩ ልዩ ምክንያቶችን እየጫረ ደም አፍሳሽ ግጭት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡ ህዝቦችን የሚያስተሳስሩ የአንድነት ገመዶችን እየለቀመ ይበጣጥሳቸዋል፡፡ ለዚሁ አላማው ማስፈፀሚያ አስፈሪና አሰቃቂ የሆኑ ጭፍጨፋዎችን ጭምር ያካሂዳል፡፡
ፅንፈኝ ብሔርተኝነት ከየትኛውም አቅጣጫ ይነሳ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት እሳቤን ተፃርሮ የሚቆም ነው፡፡ ብዝኃነት በሰፈነበት ሁኔታ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ተገነባ ማለት ማንኛውም አይነት የፅንፈኝ ብሔርተኝነት እድሜው ያጥራል ማለት ነው፡፡ የጋራ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት በሰፈነ ቁጥር አክራሪ አስተሳሰቦች ቦታ ያጣሉ፡፡ ይህም በመሆኑ አንድ የኢኮኖሚና አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚካሄደውን ጥረት በሙሉ እየተከታተለ ለማጥፋትና ህብረትን ለማፍረስ ይሰራል፡፡
በብሄር ከመደራጀት ወደ ውህድ ፓርቲ በመሸጋገር የብሄር ፅንፈኝነት ከሚፈጥሩ ምቹ መደላድሎችን በማሳጣት መቀጨጭ የሚያስችል እድል ይፈጥራል፡፡
ስለሆነም ጽንፈኝነት ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመስራት የሚዲያና የሃማኖት አባቶች ተሳትፎ በማሳደግ፣ መንግስትም ነፃ የሆነ አስተዳደር በመመስረት እራሱን ዲሞክራሲያዊ ህብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያ የቆመ መሆኑን በማስመስከር፣ ተገቢውን ህግ በማውጣትና በማስፈፀም፣ ህዝባዊ ዕርቅ በመፈፀም፣ ፍትህን እኩል ተጠቃሚነትን በማስፈን፣ መንግስት ይቅርታ በመጠየቅ፣ ህዝብ እርሰ በርሱ ይቅርታ እንዲጠያየቅ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፣ የሀገር አንድነትን በመስበክ፣ ሁሉም አቀፍ የሆነ ልማት በማምጣት፡ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ዕድል በመፍጠር ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ከሀገራዊ አንድነት ጋር ተጣጥሞ እንዲጎለብት በማድረግ፣ ልዩነታችን ውበታችን መሆኑን ማስተማር፣ ፅንፈኛ ብሄርተኝነት ላይ ጉዳቱን ማስተማር እና መልካም አስተዳደር እንዲኖር ማድረግ ይገባል፡፡
ስለዚህ አደረጃጀቱ ሁሉንም የሚያሳትፍ በሆነ አግባብ አንድ ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ መመስረት ወቅታዊና ተገቢ ያደርገዋል፡፡
4. ፌዴራል ስርአቱ እና የፓርቲ ውህደት ተያያዥነት የሌላቸው መሆኑ ፤
ሀገራችን ኢትዮጵያ ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ የምትከተለው የፌዴራል ስርዓት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረትም ዘጠን ክልሎች የተዋቀሩ ሲሆን እነዚህን ክልሎች መሰረት በማድረግም ብሄራዊ ድርጅቶች እየመሯቸው ይገኛሉ፡፡ በፌዴራላዊ ስርዓት እያንዳንዱ ክልል የራሱ ድርጅት ይኑረው የሚል አሰራርም ሆነ ህግ የሌለ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የፌዴራል ስረዓት የሚከተሉ አገራት ልምድም ይህን አያሳይም፡፡ ስለሆነም ብሄራዊ ድርጅት መኖርና የአገራችን ፌዴራል ስርዓት የተሳሰሩና የግድ የሚል አይደለም፡፡
አንድ ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ መፍጠር ማለት ፌደራላዊ ሥርዓቱ ጋር ምንም የሚያጋጨው ነገር ፈፅሞ የለም ፡፡ በጣም ግልፅ መሆን ያለበት ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር ፓርቲን አንድ እናድርግ ሲባል በህገ-መንግስቱና በፌደራላዊ ሥርዓቱ ማዕቀፍ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግና አጋሮቹ ብቻ ህገ-መንግስቱንም ይሁን ፌደራላዊ ሥርዓቱን መቀየር አይችሉም፡፡ ይህ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡ በሌላ በኩል ኢህአዴግና አጋሮቹ ወጥ ፓርቲ የሚሆኑት ፌደራሊዝሙን ለማፍረስ ሳይሆን ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ፌደራዝም እውን ለማድግ ነው፡፡ ይህ ማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት በእኩል የሚወሰንበት፣ ፍትሃዊ እና አካታች የፖለቲካ ውህደት ለመፍጠር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር ማንነትና የጋራ ማንነትን በአግባቡ አስታርቀው ለማስተናገድ ነው፡፡
ይህ ብዥታ ከሁለት መሠረታዊ መነሻ ሊነሳ ይችላል፡፡ አንደኛው ከዚህ በፊት የነበረው የኢህአዴግና አጋሮቹ አደረጃጀት በብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገ ሲሆን ፌደራሊዝሙም ከዚሁ ጋር የሚሄድ የፓርቲው አደረጃጀት ሲለወጥ ፌደራላዊ ስርዓቱ ሊለወጥ ይችላል በሚል የውሁደቱን አጠቃላይ ይዘት ካለመረዳት የሚመነጭ ሲሆን ይህ ውይይት በሚደረግበት ወቅት የፓርቲ ውህደትና የፌደራሊዝም አደረጃጀት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው እንዲያውም በፌደራሊዝም ላይ የሚነሱ ጉድለቶችን በተሻለ ደረጃ በማረም ማስቀጠል መሆኑን ሲረዱ ግልፅ መሆን የሚችል ነው፡፡
በአለም ላይ ያለውም ተሞክሮ እና ልምድ ሁሉም ፌደራሊዝም የሚከተሉ ሀገር የብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም በየክልሉ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ፖርቲዎቸ የሉም፡፡ ሥርዓቱ ፌደራላዊ አወቃቀር ኖሮት ሲያበቃ ፓሪቲዎቹ ግን ሀገራዊ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የእኛም የውሁደት አካሄድ ዓለም አቀፍ ልምድን ከግንዛቤ የወሰደ የብሔር ማንነትና የጋራ ማንነትን በተሳካ አግባብ አስታርቀው ፌደራልዝሙን በተሻለ ለማስቀጠል ነው፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ውሁደቱ እንዳይሳካ በብሔር አጥር ውስጥ ተሸጉጠው የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥና ተስፋ እንዳይቀጥል ማንኛውንም መልካም ነገር ህዝብ በጥርጣሬ እንዲመለከተው የሚሠሩ ሀይሎች ናቸው፡፡ እነዚህን ለማስረዳት ጊዜ ማቃጠል አይገባም ይልቁንም ውሁደቱን በማፋጠን በተጨባጭ አሉባልታውን ማምከን ነው፡፡
እራስን በራስ የማስተዳደርና የብሔር ብሔረሰቦች መብትን በሚመለከትም ከውህደቱ ጋር ብዥታ ለመፍጠር የሚሞክረው ሌላው ገፅታ ነው፡፡ እዚህ ላይ ቀደም ተብለው እንደተገለፀው የውሁደቱ ዋናው ዓላማ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው የብሔር ማንነትና የጋራ ማንነትን በእኩል የሚስተናገዱበት ውሁድ ለመፍጠር ነው ሲባል የብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ መብት የተቀበለ ብቻ ሳይሆን በጥብቅ የሚያከበር ነው፡፡ የድርጅት መዋቅርና መንግስታዊ መዋቅር ልዩነት በግልፅ የተሠመረ ነው፡፡ አዲሱ ውሁድ ፓርቲ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ስለሚያካትት በምርጫው ድርጅቱ በየአካባቢው ብሔር ተወካዮችን በህዝሁ ተቀባይነትን ያተረፉትን ያቀርባል ህዝብ በምርጫ ሲመርጠው እዚያው የራሱን አካባቢ ያስተዳድራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጋር ተይዘው ልክ እንደ መጀመሪያ ነጥብ የብዥታ መነሻ ያለው ሲሆን መረዳትም ያለብን ከላይ በተቀመጠው አግባብ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሌላው የብዥታ ገፅታ ደግሞ ከቋንቋ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በጥናቱ መሠረት የፓርቲው የሥራ ቋንቋ ‘’multi lingual‘’ ወይም በርካታ ቋንቋዎች ሲኖሩት በየአካባቢው የሚነገረው ቋንቋ እና በሀገር ደረጃ ለሥራ ቋንቋነት ከተመረጡት ያሻውን ወስደው ይሠራል ማለት ነው፡፡
ሰለዚህ ቋንቋዎችን የሚያቀጭጭ ሳይሆን እንደውም በሀገር ደረጃ ፓርቲው የሥራ ቋንቃዎችን በርካታ በማድረግ ቋንቃዎቹ ይበልጥ እንዲያደጉ እድል ያጐናፅፋቸዋል፡፡ ስለዚህ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 3 ያሉትን ከጥሬ ሀቁ እጅግ የራቁትን የሀሰት መረጃዎችን በመታገልና በማገለጥ ወደ ውሁደቱ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል፡፡
5. አጋር ድርጅቶችን አግላይ የነበረ መሆኑ
የኢህአዴግ አደረጃጀት በአራት ክልሎች በሚገኙ አባል ብሄራዊ ድርጅቶች በመያዝ የተመሰረተ ነው፡፡ ግንባሩ አጋር ድርጅቶች ያላቀፈ በመሆኑ በሀገሪቱ ወሳኝ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ አምስቱን ክልሎች የሚመሩ አጋር ድርጅቶችን የማያሳትፍ እና አካታች ያልሆነ አደረጃጀት ነው፡፡
ይሁንና እነዚህ ድርጅቶች በውሳኔው ሂደት ሳይሳተፉ ነገር ግን የኢህአዴግን ውሳኔ የሚተገብሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በውሳኔ ሂደት ክልሎችን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ እንዲተላለፍ በማድረግ ክልሎቹ በልማትና በዴሞክራሲ ስርኣት ግንባታ መድረስ ከሚገባቸው ደረጃ እንዳይደርሱ የራሳቸው ውስጣዊ ሁኔታ እንደተጠበ ሆኑ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡
ከዚህም የላቀው ጉዳይ በሀገራዊ ጉዳይ እኩል የሚመክሩበት እድል ማነሱ ለሀገራቸው ባይተዋርነት ስሜት እንዳይፈጥርባቸው በተለያየ ጊዜ ወደ ግንባሩ አባል ለመሆኑ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን በማቅረብ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አደረጃጀቱ አካታች ካልሆነ ከፌደራላዊ ሥርዓቱ ጋር የሚጋጭ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለሆነም አነድ አገራዊ ድርጅት ቢኖር በነዚህ ክልሎች ያለ መንኛውም ዜጋ በሌሎች ክልሎች ካሉ ዜጎች እኩል የመሳተፍ እድልን የሚያሰፋና ፍትሃዊና ሚዛናዊ ውክልናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም አደረጃጀቱ ሁሉንም የሚያሳትፍ በሆነ አግባብ አንድ ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ መመስረት ወቅታዊና ተገቢ ያደርገዋል፡፡
6. የኢህአዴግ ጉባኤ ያስቀመጠው አቅጣጫ መፈፀም ድርጅታዊ ዲስፒሊን መሆኑ፡-
በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ባደረገው ውይይት በግንባሩ ቀጣይ እጣፋንታ ላይ ውሳኔ ለመወሰን ባስቀመጠው እቅጣጫ መሰረት ጥናትን መሰረት በማድረግ አባል ድርጅቶች ውህደት እንዲፈጥሩ እና በዚህ ውደትም አጋር ድርጅቶች ጋር ያለን ስትራቴጂካዊ ግንኙነትም በጥናት ላይ ተመስርቶ ምላሽ እንዲሰጠው መወሰኑ የሚታው ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ድርጅቱን ከግንባር ወደ አንድ ድርጅት ውህደት መፍጠር መነሻው ድርጅታዊ ጉባኤው ያስመጠው አቅጣጫ በመሆኑ ተፈፃሚ እንዲሆን በድርጅታዊ ዲሲፒሊን ሁሉም ሊያከናውነው የሚገባ ጉዳይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡
7. ለቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግ በአዲስ መልክ ራሱን ሪበራንድ በማድረግ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
አንድ የፖለቲካ ድርጅት በህዝብ ምርጫ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚሰራ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በምርጫ ለማሸነፍ ፖለቲካ ድርጅቶች የተለያዩ ስልቶችን የሚጠሙ ሲሆን ይህም የህዝብን ይሁንታ ለማግኘት ጥቅም ላይ የሚያውሉት ነው፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ኢህአዴግ የሰራቸው እጅግ አበረታች እና አመርቂ ለውጦችን ማምጣት የመቻሉን ያህል በህዝቡ ዘንድ እንዲጠላ የሚያደርጉ ከሰብዓዊ መብቶችና ፍትሃዊ ልማት ከማረጋገጥ አንፃር ብሎም ኪራይ ሰብሳቢነትን አለመድፈቅ ችግር እንዳለ በለውጡ ዋዜማ መገምገማችን የሚታወቅና ህዝቡም በተለያየ ሁኔታ መግለፁ የሚታወስና ሀገራችንን ምን ያህል አደጋ ተፈጥሮባት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
ስለሆነም በባለፈው አንድ ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ባስመዘገብነው ለውጥ ህዝቡ ጋር መግባባትን እየፈጠርን ሲሆን ይህን የድርጅታችንን ስያሜ እና ማኒፌስቶ ለውጥ በማድረግ በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማማጣት የሚሰራ ድርጅት መሆኑን በማስገንዘብ ሪብራንድ በማድረግ የበለጠ ህዝባዊ ቅቡልነታችንን ያስረግጥልናል፡፡ ይህ ህዝባዊ ቅቡልነታችን ደግሞ በምርጫ 2012 የምንፈልገውን ግብ ለማሳካት የሚኖረው አወንታዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ውህደት መፍጠሩ ለሪብራንዲን አንዱ ማሳያ ሆኖ ሊታይ የሚችል በመሆኑ አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡
8. የውህደቱ ጊዜው አሁን መሆኑ
በሀገራችን በተፈጠረው ለውጥ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ተከትሎ የተለያዩ ፖለቲካ ሃይሎች በመሰባሰብ ጠንካራ ፓርቲ ለማቀቀም እየተንቀሳቀሱ የሚገኙበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
በዚህ ሂደት ኢህአዴግም አደረጃጀቱን ፈትሾ ተጠናክሮ ካልወጣ ስተቀር የመሪነት ሚናውን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎችም እየተፈጠሩ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ድርጅታችን ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማየት እራሱን አጠናክሮ ለመምጣት ያለው ዕድል ከላይ በዝርዝር እንዳየነው አንድ ውህድ ፓርቲ ሆኖ መገኘት በእጁ ላይ የሚገኝ ትልቅ ዕድል ሆኖ ይገኛል፡፡ ውህድ ፓርቲ ሆኖ መምጣትን እንደትልቅ ዕድል ከታየ ደግሞ ጊዜው ነገ ወይም ወደፊት ሳይሆን አሁን ነው፡፡
9. ሚዛናዊ ውክልና ፣
አንድ ውህድ ፓርቲ መሆኑ ከሚያስገኘው ጥቅም መካከል አንዱ የሆነው በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ያለምንም ክልከላ በአደረጃጀቱ የሚሳተፉበት አካታችና ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖር የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡ ይህም በአንድ አካባቢ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ በዚህ ውህድ ድርጅት የእከሌ ብሄር ካልሆነ የሚል ክልከላ ሳይኖርበት በሚኖርበት አካባቢ መደራጀት የሚችልበት ሁሉን አካታች ፍትሃዊ ውክልናም እንዲኖር የሚያስችል ይሆናል፡፡
10. የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን የማጠናከር አስፈላጊነት፣
ድርጅታችን ኢህአዴግ በየጊዜው በውስጡ በሚፈጠሩ ከመስመር መውጣት ምክንያት ለከፍተኛ ችግሮች ራሱንና አገሪቱን ሲያጋልጥ መቆቱ የሚታወስ ነው፡፡
በተጨማሪም ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል መጠራጠር፤ መገፋፋት፤ መቃረን እየበረታ መምጣቱና እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት እና አመራሩ በሚሰራቸው ስህተቶች ከመታረም ፈንታ ወደ ብሄራዊ ድርጅቶች ጉያ እየተወሸቁ ጥፋትን ሰበሰብ እየሰጡ መጓዝ፤ ድርጀቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የክሰተት መሪ እንጂ አርቆ አሳቢነት እየራቁት መምጣታቸው በብሔራዊ ድርጅቶች መካከል እርስ በርስ የመጠራጠርና ለተሟላ ትግል የማያመች በመሆኑ ሁሉም በድርጅታዊ ነፃነት ሽፋን የብሔር ምሽግ እየጠነከረ የሚሄድበት ዝንባሌ ስለሚታይ ይህንን በማስቀረት በመርህና በድርጅት ዓላማ መሠረት በማድርግ ለመተራረም እና ወጥ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን ለማረጋገጥ ወደ ውህደት ማሸጋገር ተፈላጊ ያደርገዋል፡፡
ይህ ውህደት ሲፈጠር አባል ድርጅቶች ውህደቱን የሚፈጥሩት በፕሮግራም ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆኑ የሚፈጠሩ ችግሮችን ትግል ለማድረግ እና በብሄራዊ ድርጅት የመታጠርን ካባ የሚያወልቅ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚስችል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነትን በማስጠበቅ ጠንካራ ፓርቲ እንዲሆን ያስችላል፡፡
Source:EPRDF Official
Source:EPRDF Official
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ