የጡረታ ዕድሜን ጣራ ወደ 60 ዓመት ከፍ ያደረገው አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የመንግሥት እና የግል ሠራተኞች ጡረታን ለመደንገግ በቀረበው አዋጅ ላይ በመወያየት አፀደቀ።
የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ለማህበራዊ ፍትህ፣ ለኢንደስትሪ ሰላም፣ ለድህነት ቅነሳ፣ ለምርታማነትና ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው የማኅበራዊ መድን ስርአትን ለማስፋፋት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተመላክቷል፡፡
የስርዓት ተጠናክሮ መቀጠል በሥራ ላይ ያለው የመንግሥት አገልግሎት የጡረታ ዕቅድ አቅም በፈቀደ መጠን ማጠናከር፣ አዋጆቹን በማሻሻል ማጠቃለልና ለሥራው አፈጻጸም ምቹ ሁኔታን መፍጠር በማስፈለጉ አዋጁ ሊሻሻል መቻሉም ነው የተጠቆመው፡፡
በዚሁ መሠረት የተሻሻለው የጡረታ ዐዋጅ የጡረታ ዕድሜን ጣራ 60 ዓመት እንዲሆን እንዲሁም ጡረተኛው በሕይወት ሳለ የሚያገኘው የጡረታ መጠን ሲያልፍ ለትዳር አጋር 50 በመቶ የጡረታው ተጠቃሚ እንዲሆን ይፈቅዳል።
በተመሳሳይ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ዛሬ በምክር ቤቱ የጸደቀ ሲሆን፥ ይኸውም በድርጅቶች ምክንያት ሳይዋጣ የቀረን ገንዘብ በሦስት ወር ውስጥ ገቢ ካልተደረገ በቀጥታ ድርጅቱ ካለው ማንኛውም የባንክ አካውንት ገቢ እንዲደረግበት የሚያስገድድ ነው።
የግል ድርጅት ባለቤቶች በድርጅቱ ሠራተኛ ሆነው በጡረታ ማዕቀፉ ውስጥ እንዳይገቡም አዋጁ አግዷል።
ከ10 ዓመት በላይ ያገለገለ ሠራተኛ ዕድሜው ለጡረታ በሚደርስበት ጊዜ የዕድሜ ልክ ጡረታ ተከፋይ እንዲሆንም አዋጁ ይፈቅዳል።
የሚሰበሰበው የጡረታ መዋጮም ወደ ኢንቨስትመንት በማስገባት ገቢን ማሳደግ ለጡረተኞች የክፍያ ማሻሻያ የሚያደርግበትን እድልም የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
አንድ አሰሪ የግል ድርጅት ፍቃዱን በሚያድስበት ጊዜ የሠራተኞቹን መዋጮ ካላስገባ ፍቃዱ የማይታደስበት አስገዳጅ አንቀጽም ተካቷል።
Source:FBC
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ