ቅድሚያ ለአገር!

ከስምንት ዓመት በፊት በ‹‹አረብ አብዮት›› ብሂል በአንዳንድ አረብ አገራት የተጀመረው ውል አልባ ሁከትና ግጭት ዛሬም መቋጫ ሳያገኝ ህዝብና አገርን እያነደደ ቀጥሏል፡፡ እነ ሊቢያ፣ የመንና ሶርያም የጦርነት ቀጣና ሆነዋል፡፡ በተለያዩ ዘመናት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠራቸውን ታሪክና ባህል የሸከፉት እነዚህ አገራት አሁን የጦርነት አውድማ ናቸው፡፡
የእነዚህ አገራት ህዝቦች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ስደትን ምርጫቸው ካደረጉ ውለው አድረዋል፡፡ የስደት ጎዳና ካሰቡበት ሳይደርሱ በየበረሃው ያስቀራቸውም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ምንም የማያውቁ ጨቅላዎች ከመጡባት ዓለም ጋር ሳይተዋወቁ ተለያይተዋል፡፡ ለህዝብና አገር የሚጠቅሙ ምክረ ሃሳቦችን የሚያፈልቁ ምሁራን ለሞት፣ አካል ጉዳትና ስደት ተዳርገዋል፡፡
ከአጠቃላይ ህዝቧ ግማሽ ያህሉን(11 ሚሊዮን) የሚሆነውን በሞትና በስደት ያጣችው ሶርያ ዕጣ ፈንታዋ አስከሬን ከመቁጠር ያለፈ እንዳልሆነ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ከአንድ ሺ ቀናት በላይ በግጭትና ጦርነት ለማሳለፍ የተገደደችው የመንም ከ50ሺ በላይ ዜጎቿን በሞት ከመነጠቅ ውጭ ያገኘችው ትርፍ የለም፡፡ በሃምሳ ዓመት ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ የተባለውንና ከ18 ሚሊዮን በላይ ህዝቧ ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የተዳረገበትን የታሪክ ምዕራፍ ለማንበብና ለማስነበብ በቅታለች፡፡ የሊቢያ ግጭትም አገርን ከማዳከም፣ ልማቶችን ከማውደምና ህዝብን ከማጎሳቆል ያለፈ ትርፍ አላስገኘም፡፡
የአገራቱ ሁከትና ግጭት ከመብረድና ከመቀነስ ይልቅ እንዲባባስና እንዲቀጣጠል የውጭ አካላት ግፊትና ጣልቃ ገብነት መኖሩ ገሀድ የወጣ ሀቅ ነው፡፡ ግጭቱ እንዳይበርድ የሚፈልጉት ኃይሎች ዛሬም ሲያስፈልግ በስውር፣ ሲሻቸው በገሀድ በ‹‹በለው፣በለው…››ፉከራና ቀረርቶ ገፍተውበታል፡፡ ህዝቡ ለገዛ አገሩ ባዳ ሆኖ የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፍቶት ግራ እንደተጋባ አስከፊ ህይወትን ይገፋል፡፡
የእነዚህ አገራት የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሚያሳየው ግጭትና ሁከትን ለመጀመር ቀላል፣ለማቆም ግን እጅጉን ከባድ መሆኑን ነው፡፡ የሁከቱን የሩጫ ዙር ያከረሩት ጥቂቶች በብዙዎቹ ስቃይና ኃዘን ሲደሰቱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በእነዚሀ አገራት ጉዳይ አስተያየት የሚሰጡ ገለልተኛ ፖለቲከኞችና ምሁራን እንደሚሉት አብዛኛዎቹ የግጭት አቀጣጣዮች ከወላፈኑ በብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች ርቀው በቅርብ ያለውን ነገን ናፋቂውን ህልመኛ በእሳት ይማግዱታል፡፡
ይህን እውነታ መረዳትና መገንዘብ የሠላምን አስፈላጊነት ከልቡ እንዲቀበል ያስገድደዋል፡፡ የሠላም ዋጋው ሊተመን እንደማይችልም በደንብ ይገባዋል፡፡ ለመተቸት፣ ለመቃወምና ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ ለማግኘት ሠላም ወሳኝ ነው፡፡ ሠላም በሌለበት እንኳን ጥያቄ ለማቅረብ ለማሰብም ይከብዳል፡፡
መንግስት ያልመለሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ህዝቡ ጥያቄ ማቅረቡ ተገቢም ጤናማም ነው፡፡ ጥያቄ የቀረበለት አካልም ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፤ግዴታውም ነው፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም ታዲያ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ሁከትና ግጭት በመፍጠር ሠላማዊው ህዝብ እንዲታወክና እንዲጨነቅ የሚያደርጉ ያልተገቡ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍና ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ የአፈፃፀም መመሪያውም ይፋ ተደርጓል፡፡ በተሳሳተ መረጃና የፕሮፓጋንዳ ዲስኩር ተታለው የዕኩይ ድርጊቱ ተባባሪና ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በዚህም የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማወክ፣ የህዝብ አገልግሎትን ማቋረጥ፣ መሰረተ ልማቶችን ማውደም፣ የመሰረታዊ ፍጆታ ዕቃ አቅርቦትን ማወክ፣ ያልተፈቀዱ ሰልፎችና የአደባባይ ስብሰባዎችን ማድረግ፣ የህግ አስከባሪ አካላት ስራዎችን ማወክና በነሱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም መሞከር አዋጁ ጥብቅ ክልከላ ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። እነዚህንና መሰል በአዋጁ ክልከላ የተደረገባቸውን ድርጊቶች መፈፀም ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡
ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበርና ለተፈፃሚነቱ መተባበር እነዚህን ክስተቶች በመግታት በተለመደው ሰላማዊ የህይወት መስመር ውስጥ መግባት ነውና ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ግድ ይለዋል፡፡ “መጀመሪያ መቀመጫዬን” እንዳለችው እንስሳ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለአዋጁ ስኬት መተባበር አለበት።
መቃወም፣መደገፍ፤ ማዘን፣ መደሰት የሚቻለው አገር ሠላም ሲሆን ነው፡፡ ሰርቶ ለመብላት ብቻ ሳይሆን ለምኖ ለመብላትም ሠላም ያስፈልጋል፡፡የአገርን ሠላም የመጠበቅና የማረጋገጥ ኃላፊነት ደግሞ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሩን በማስቀደም ለሠላሟ መትጋት ይኖርበታል፡፡ ሌላው ጉዳይ ሁሉ ከአገር ሠላምና መረጋጋት በኋላ የሚከተል ነው፡፡ የደፈረሰውን የሠላም አየር ለማጥራት የወጣውን አዋጅ አክብሮ መንቀሳቀስ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ የጥቂት ጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ላለመሆንም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
የአገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች የሠላምን አስፈላጊነት በየአካባቢያቸው መስበክ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም የሃይማኖት አባቶች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በተሳሳተ ጎዳና የሚጓዙትን የህብረተሰብ ክፍሎች ማስተማር፣ መገሰፅና መምከር አለባቸው፡፡ ከማንምና ከምንም ነገር በላይ አገር ይቀድማል፡፡

Source:አዲስ ዘመን፣ ርዕሰ አንቀፅ- የካቲት 28/2010

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman