የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ተሻጋሪ ግንኙነት ሕግ እየተበጀለት ነው
ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚጋሯቸውን ድንበሮች ለማቋረጥ ሕጋዊ ሰነድ መያዝ እንዲቻል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየሠራ እንደሆነ ታወቀ፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዕርቅ ከተደረገ በኋላ የሁለቱ አገሮች ዜጎች እንዳሻቸው ድንበር እየተሻገሩ ዘመድ ሲጠይቁ፣ ሲጎበኙና ሲነግዱ የነበረ ቢሆንም፣ ይኼንን ግንኙነት ፈር ለማስያዝ ሁለቱ አገሮች ለሚፈራረሟቸው ስምምነቶች በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ሪፖርተር ከምንጮች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
በዚህም መሠረት አዲስ የተከፈተውን የኦምናሃጀር ሁመራ ድንበር ጨምሮ የዲባይሲማ-ቡሬ፣ የሰርሐ-ዛላምበሳና የአዲኳላ-ራማ ድንበሮችን ለማቋረጥ ሕጋዊ ሰነድ መያዝ እንደሚያስፈልግ ተነግሯል፡፡
ቅዳሜ ታኅሳስ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ መምህራንን ባወያዩበት ወቅት ባሉት መሠረት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚኖሩ ግንኙነቶችን የሚገዙ ስምምነቶች በቅርቡ ይፈረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ምንጮች አክለዋል፡፡
በራማ-ዛላምበሳና በሌሎች ድንበሮች አካባቢ ተጀምሮ የነበረው ግንኙነት እነዚህ የጉዞ ሰነዶች ሳይኖሩ እንዳይደረግ በመባሉ መቋረጡ የሚታወስ ሲሆን፣ ካሁን ቀደም ከተከፈቱት ድንበሮች በተጨማሪ ሰኞ ታኅሳስ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ተጨማሪ ሁለቱን አገሮች የሚያገናኛቸው የኦምናሃጀር-ሁመራ ድንበር በይፋ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በይፋ ተከፍቷል፡፡
ድንበሩ በይፋ በተከፈተበት ወቅት በኢትዮጵያ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኰንን የተገኙ ሲሆን፣ በኤርትራ በኩል የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ፣ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አማካሪ አቶ የማነ ገብረ አብና የኤርትራ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተክሌ ክፍላይ ተገኝተዋል፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል በመተላለፊያነት የሚያገለግሉ አምስት የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበሮች ከተከፈቱ በኋላ፣ በየቀኑ ለንግድና ለተለያዩ ምክንያቶች ከ1,000 እስከ 2,000 ተሽከርካሪዎች ድንበር አቋርጠው ይገቡ እንደነበርና ከድንበሩ መከፈት ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥገኝነትን በይፋ የሚጠይቁ 27,000 ኤርትራውያን እንደሚገኙ ካሁን ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ዘላቂ ሊያደርጉ የሚችሉ ውይይቶች ፍሬያማ ሆነው ተጠናቀው ወደ ስምምነት ዝግጅት እንደተገባ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሪፖርተር ያቀረበላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
Source:Reporter
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ