ቤተ መንግሥት ድረስ ገብተው ጉድ ሊሰሩን የነበሩ የሠራዊቱ አባላት መኖራቸውን ካሰብን......

ቤተ መንግሥት ድረስ ገብተው ጉድ ሊሰሩን የነበሩ የሠራዊቱ አባላት መኖራቸውን ካሰብን፤ በሕዝብ ላይ ተኩሶ ሀገር ወደ ትርምስ የሚከት አምስትም አስርም የሠራዊት አባል እንደሚኖር አስበን፤ በሥርዓት ስለማሸነፍ እናስብ፤
በመተማ የተፈጸመው ድርጊት የሚኮነን ነው፡፡ መተኮስን እንደ አማራጭ ማየት አልፈልግም በሚል መከላከያ ሠራዊታችን ውስጥ ዛሬም ቃታ ስበው ሀገር ማተራመስ የሚፈልጉ ድብቅ ዓላማ ያላቸው አባላት እንዳሉ አሳይቶናል፡፡ መፍትሔው ግን ተረጋግተን ማሰብ ነው፡፡ ተረጋግተን መጠየቅ ነው፡፡ ተረጋግተን ማሸነፍ ነው፡፡
በቅርቡ ወደ ቤተ መንግሥት ገስግሰው ጠቅላዩን ለመጠቅለል ያሰቡ የሠራዊቱ አባላት በጦር ፍርድ ቤቱ የተፈረደባቸውን ሰምተናል፡፡ ቤተ መንግሥት ድረስ ሄዶ እድሉን መሞከር የሚፈልግ የሠራዊት አባል ካለ ህዝብ ማሃል ሆኖ የሚያበጣብጥ ነገር ቢፈጽም አይገረመን፡፡ ይልቁንስ ሁሌም ንቁ ሆነን ችግሩ ብሶ እንዳይጎዳን እንተባበር፡፡
የመተማን ችግር በተመለከተ አማራ ብዙሃን በዘገበው ዘገባ ላይ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ የሱር መኪኖች ተፈትሸው እንዲወጡ በነበረው ስምምነት ከህዝቡ ጋር እየተካሄደ ያለው ውይይት ሳያልቅ መኪኖቹ በመውጣታቸው ለማስቆም በፈለጉት ሰዎች እና በመከላከያ መካከል በተነሳ ግጭት ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሱር ኮንስትራክሽን በአካባቢው በድብቅ ሲፈጽመው የኖረው ሴራ እንዲህ ባሉ ወገን የሚረግፍባቸው ግጭቶች መንስኤም መሆኑ ያሳዝናል፡፡ የህግ አለመከበር ችግር ውሎ አድሮ አሁንም በሱር ምክንያት ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡
አሁንም በሱር ምክንያት መተማ ለብጥብጥ ተዳርጋለች፡፡ በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥም ግን ተረጋግቶ መፍትሔ መፈለግና መደማመጥ ያስፈልገናል፡፡
ቀጠናው መከላከያ ይውጣ የሚባልበት ቀጠና አይደለም፡፡ የተቀበሩ ፈንጂዎች የተደበቁ ሴራዎች የበዙበት ምድር ነው፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዳይነሳ ተው ባይ በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት መከላከያ ይውጣ የሚለውን የሚቀሰቅሰው ማን ነው ብሎ መጠየቅ ይገባል?
ከመከላከያ ሠራዊቱ መካከል ዛሬም ህዝብ ላይ ቃታ ስቦ የምናየውን ተስፋ ለማጨለም የሚባትል እንደማይጠፋ ካመንን በዘዴ እንዲህ ያለውን አረም ለይተን ማስወገድ እንጂ በጅምላ ግብ ግብ ውስጥ በመግባት ሀገር እንዲፈርስ ሥርዓት እንዲጠፋ ምክንያት መሆን የለብንም፡፡ ተደራጅተን ከሰራን ተመካክረን ችግሩን እንደርስበታል፡፡ የደረስንበትን ችግር በህብረት እንቀርፈዋለን፡፡ እርግጥ እንዲህ እናድርግ ስንል አሁንም ዜጎች ይሞታሉ፡፡ ግን መታገስ ካቃተን ደግሞ ከሞተብን በላይ ይሞትብናል፡፡ ሞተንም የምንፈልግውን ውጤት አናመጣውም፡፡ ያልተቀናጀ ትግል ሁሉንም ወገን ያከስራል፡፡
ሀገር ለውጥ ላይ ናት፡፡ ለውጡ አሁንም የሰው ህይወት እየጠየቀ ነው፡፡ ሰው እየሞተ ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የሞት ምክንያት የሆኑ መንስኤዎችን ለማስቀረት መሞከር ነው፡፡ ሞትን በመኖር ድል መንሳት ነው፡፡ በሚከፈለው ዋጋ ሀገርን ማስቀጠል ነው፡፡
የለውጡ መንግስት ደግሞ እንዲህ ያሉ ውስጡ የተሰገሰጉ እንቅፋቶቹን ማስወገድ አለበት፡፡ ከስር ከስር ችግር የሚፈጥሩ ገዳዮችን መመንጠር አለበት፡፡ መግደልና መሞት የማናይባትን ኢትዮጵያ እውን እናድርግ፤
Source:( ከስናፍቅሽ አዲስ)

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman