የአዲስ ተማሪዎች ምደባ ይፋ ሆነ
በ2008 ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ አዲስ ተማሪዎች ምደባ ዛሬ ይፋ ሆነ።
የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ እንዳስታወቀው፥ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ ተማሪዎች የተመደቡበትን ዩኒቨርሲቲ በኤጀንሲው ድረ ገጽ እና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት በነጻ መመልከት ይችላሉ።
በዚህም መሰረት ተማሪዎች በኤጀንሲው ድረ ገጽ www.nae.gov.et/ በመግባት እና 8181 ላይ rtw በማለት ክፍተት በመስጠት የፈተና መለያ ቁጥር በማስገባት መልዕክት በመላክ የተመደቡበትን ዩኒቨርሲቲ ማወቅ የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ከወሰዱት መካከል 124 ሺህ 227 ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማግኘታቸውን ያስታወቀው ኤጀንሲው፥ ማለፊያ ነጥብ ካገኙት መካከል 86 ሺህ 958 የሚሆኑት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ፤ 37 ሺህ 268 ተማሪዎች ደግሞ በህብረተሰብ ሳይንስ መመደባቸውን ጠቁሟል።
ምደባው 40 በመቶ በክልል ሲሆን 60 በመቶ ደግሞ ከክልል ውጪ መሆኑንም ኤጀንሲው አስታውቋል።
የሴቶች ተሳትፎም 42 በመቶ መሆኑንም ነው የገለጸው።
2 ሺህ 500 ተማሪዎች በሜዲስን የትምህርት ዘርፍ የተመደቡ ሲሆን፥ በዘርፉ ለመግባት ለወንዶች 504 ለሴቶች ደግሞ 484 እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 2 2007 ዓ.ም ድረስ የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና /የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ/ ፈተና ውጤት ሐምሌ 20 2007 ዓ.ም መለቀቁ ይታወሳል፡፡
ከተፈታኞቹ 45 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆኑት ማለትም ከ93 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎች 350 እና ከዚያ በላይ ማምጣታቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
የዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት ከፍተኛው ውጤትም 649 ሆኖ ተመዝግቧል።
57 ተማሪዎችም ከ600 በላይ ውጤት ያመጡ ሲሆን፥ ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በመደበኛ፣ በቀንና በማታ መግቢያ ነጥብ ፣ ለተፈጥሮ ሳይንስ ወንዶች 343 እና ከዚያ በላይ፣ ለሴቶች መግቢያ ነጥብ 320 እና ከዚያ በላይ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።
ለግል ተፈታኞች ደግሞ ለወንዶች 353 እና ከዚያ በላይ፣ ለሴቶች ደግሞ 331 እና ከዚያ በላይ መሆኑም አይዘነጋም።
ለታዳጊ ክልሎችና ለአርብቶ አደር አካባቢ ተማሪዎች ለወንዶች መግቢያ ነጥብ 332 እና ከዚያ በላይ ሲሆን፥ ለሴቶች ደግሞ 317 እና ከዚያ በላይ መሆኑም የሚታወስ ነው።
ባለፈው ሳምንት የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ተማሪዎችን ከመስከረም 21 እስከ 25፣ 2008 ዓ.ም ተቀብለው ወደ ቅድመ ማስተማር ዝግጅት እንዲያመሩ ጥሪ አቅርቧል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ