ከአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የድርጅታችን አዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰኔ 15/ቀን 2011 ዓ.ም በክልላችን መንግስት ላይ ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ በከሸፈው መፈንቅለ-መንግስት እና በከፍተኛ አመራሮቻችን ላይ በተፈፀመው የግፍ ግድያ ምክንያት የማዕከላዊ ኮሚቴያችን ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ተመስርቶ በወቅታዊ ጉዳይ እና ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎች ግምገማ ለማድረግ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም እየመከረ ባለበት፣ የአማራ ህዝብና የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከጥልቅ ሃዘናችን ባልተላቀቅንበት በዚህ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታ ውስጥ ሆነን “በሰው ቁስል እንጨት ቢሰዱበት” እንዲሉ፣ የትህነግ/ህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የትህነግ/ህወሓትን የነበረና እየቀጠለ ያለ አሳፋሪ የሴራ ፖለቲካ እርቃኑን በአደባባይ ያጋለጠ የአቋም መግለጫ ማውጣቱ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል እንዲሉ” አገራችን አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት እራሱ ዋና ተጠያቂ ሆኖ ሳለ፣ የአማራን ህዝብ ህልውናና ክብር የማይመጥን መግለጫ አውጥቷል፡፡ 
ምንም እንኳን የድርጅታችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለስብሰባ የተቀመጠው ካጋጠመን ወቅታዊ ችግር በፍጥነት እንዴት መውጣት እንዳለብን እና የለውጡን ቀጣይነት ጠብቀን መዝለቅ እንደሚገባን ለመምከር ቢሆንም፣ የትህነግ/ሕወሓት መግለጫ ከሐዘን ባልወጣንበት ሁኔታ ከአንድ እህት ፓርቲ የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት በመሆኑ፣ ድርጊቱን ለማውገዝና ለአብሮነትና ለትግራይ ህዝብ ባለን ክብር እያየን እንዳለየን የታገስነውና እና ያለፍነውን ነገር ሁሉ፣ ትህነግ/ሕወሓት በመግለጫው “እራሱ ነካሽ፣ እራሱ ከሳሽ” ሆኖ በመቅረቡ ይህ የአዴፓ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ አስፈላጊና ወቅታዊ ሆኖ አገኝተነዋል፡፡ 
የትህነግ/ሕወሓትን መሠሪ እና አሻጥር የተሞላበት የዘመናት ባህሪውን በማጋለጥ፣ የአማራ ህዝብን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባደረጉት ቆራጥ ትግል የተገኘውን ህዝባዊ ድል ደግሞ ደጋግሞ በማንኳሰስ እና ፈፅሞ አክብሮት የማያውቀውንና እራሱ ሲጥሰው የነበረውን ህገ-መንግስታዊና የፌዴራል ስርዓት ጠበቃ በመምሰል፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ጭቁን ህዝቦችን በማደናገር ለዳግም ሰቆቃ እንዲዳረጉ እያደረገ ባለበት፣ በፀረ-ለውጥ እንቅስቃሴው አገራዊና ክልላዊ ለውጡ በጥርጣሬ እንዲታይ ከጥፋት ሃይሎች ጀርባ መሽጐ አመራር እየሰጠ ባለበት ሁኔታ፣ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የለውጥ ፍላጐት መነሻ ተደርገው የተወሰዱ አሳሪና ደብዳቢ ፀረ-ዴሞክራቶችን፣ ህዝብና አገር በድፍረት የዘረፉ ሌቦችን፣ በብሄር፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች ልጆቹ ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አቅፎና ደብቆ በያዘበት ሁኔታ የትህነግ/ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ የዘመናት አስመሳይነቱን ያጋለጠ፣ እራሱን ብቸኛ የኢትዮጵያ ጠበቃ አስመስሎ መቅረቡ የሞራል እና የተግባር ብቃት የሌለው ድርጅት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

ትህነግ/ሕወሓት ከምስረታው ጀምሮ በ1968 ማኒፌስቶው የአማራን ህዝብ በጠላትነት የፈረጀ፣ ከሌሎች ወንድምና እህት ህዝቦች ጋር ተከባብሮና ተሰናስሎ በፍቅር እንዳይኖር “ትምክህተኛና ሌሎች አግላይ ስያሜዎችን እየሰጠ ለዘመናት የፈፀመው ግፍና በደል ሳያንሰው ዛሬም ከለውጥ ማግስት በአደባባይ ተሸንፎ ህዝባዊ እርቃኑ በተጋለጠበት በዚህ ሰዓት፣ አጠቃላይ ትግሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች የትህነግ/ህወሓትንና የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ድርጊት መፋለም ሆኖ ሳለ ትግሉ በትህነግ/ህወሓትና በአዴፓ መካከል የሚካሄድ በማስመሰል፣ ወቅታዊ ጉዳታችንን እንደ ዘላቂ ሽንፈትና ውድቀት በመቁጠር፣ ዛሬም የአማራን ህዝብ አንገት ለማስደፋት “የተቀበረውን የትምክህት ትርክቱን ዳግም ይዞ ብቅ ማለቱ ድርጅቱ መቼም ቢሆን መፈወስ የማይችል በሽታ ያለበት መሆኑን ያጋለጠ ተግባር ነው፡፡ በእርግጥም ትህነግ/ሕወሓት በዚህ ባህሪው ይታወቃል፡፡ በፅናት የሚታገሉትንና ከኔ ጎን አይሰለፉም የሚላቸውን ኃይሎች ሲሻው ትምክህተኛ፣ ሲሻው ጠባብና አሸባሪ በማለት ታርጋ እየለጠፈ የሚያሸማቅቅ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መሆኑ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀዋል፡፡ በመሆኑም የትህነግ/ሕወሓት መግለጫ አዲስ ነገር ይዞ የመጣ ሣይሆን የተለመደ ፖለቲካዊ ሴራ ማሳያ ነው፡፡ 
ትህነግ/ህወሓት ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሁለት አገረ-መንግስት እይታ ያለው፣ አንድም ቀን ለህዝቦች አንድነት የማይጨነቅ፣ በስልጣን ላይ እስከቆየና ዕላፊ ጥቅም እስካገኘ ድረስ ብቻ አስመሳይ የአንድነት ኃይል ሆኖ መቀጠል የሚፈልግ፣ ነገር ግን እንደዛሬው በስልጣን ላይ ሆኖ በአድራጊ ፈጣሪነት ሁሉንም ማሳካት ሳይችል ሲቀር፣ በቁም ቅዥትና ከትግራይ ህዝብ ስነ-ልቦና ባፋነገጠ መልኩ “የዥዋዥዌ ፖለቲካን” የሙጥኝ ያለ እምነት የማይጣልበት ድርጅት ነው፡፡

የአማራ ህዝብና መሪ ድርጅታችን አዴፓ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ለሐቀኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት፣ ለእውነተኛ ህገ-መንግስታዊ ስርዓትና ለእውነተኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት ፅኑ እምነት ይዞ የሚታገል ህዝብና ድርጅት እንጂ ትህነግ/ሕወሓት ደጋግሞ እንደሚከሰው ሳይሆን ለአገር አንድነት የሚተጋ፣፣ በሌሎች ጉዳት ላይ የተመሠረተ ተናጠላዊ ጥቅምን ማረጋገጥ የማይፈልግ፣ ሐቀኛና ህዝባዊ ድርጅት ነው፡፡
አሁን በምንገኝበት የለውጥ መድረክም የአማራ ህዝብና ድርጅታችን አዴፓ ሆን ተብሎ የተበላሸውን አገራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታችን እንዲታረም፣ ከሌሎች የለውጥ ሃይሎች ጋር ሆኖ ፊት ለፊት የተፋለመና የለውጡን ውጤቶች ጠብቆ ለመዝለቅ ሌት ከቀን የሚታትር ድርጅት እንጂ እንደ ትህነግ/ሕወሓት በከፋፋይት በሽታ የተጠመደ ድርጅት አይደለም፡፡ 
ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በክልላችን ከፍተኛ አመራሮች እና የኢትዮጵያን አንድነት መስዋዕትነት እየከፈለ ለማስቀጠል በሚተጋው የመከላከያ ሀይላችን የጦር ጄኔራሎች ላይ ያነጣጠረው ግድያ እና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በድርጅታችን አዴፓ፣ በአማራ ህዝብና በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የተፈጸመ ጥቃትና የለውጣችን ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በመሆኑም የጥፋት ድርጊቱን ከህዝባችንና ከፀጥታ መዋቅራችን ጐን ተሰልፈን በፅናት የተፋለምነውና ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለንበት ነው ብለን እናምናለን፡፡ በሂደቱም ለኢትዮጵያ አንድነት ያለንን ቁርጠኝነት ዳግም ያሣየንበትን ታሪካዊ ወቅትና የትግላችን አንድ አካል የሆነውን ጥረታችንን እንደሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መሪ ድርጅቶች መደገፍና ማገዝ ሲገባ ትህነግ/ሕወሓት ድርጊቱን ለራሱ በሚጠቅመው መንገድ በመረዳት ይቅርታ እንድንጠይቅበት መግለጫ ማውጣቱ ተደማሪ ታሪካዊ ስህተት ከመሆኑም በላይ የተከበረውን የትግራይ ህዝብ ባህልና እሴት የማይመጥን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያሣዘነ መግለጫ ነው ብለን እናምናለን፡፡ 
በእርግጥም ትህነግ/ሕወሓት ይህንን ወቅታዊ ሁኔታ የራሱን የዘመናት ወንጀሎች ለመሸፋፈን ተጠቅሞበታል፡፡ እውነትና ፍትህ ቢኖር ኖሮ ባለፉት ዘመናት በትህነግ/ሕወሓት የሴራ ፖለቲካ ምክንያት ለተለያየ ጥፋት እና እንግልት በተዳረገው መላው የኢትዮጵያ ህዝብና ቅርቃር ውስጥ በወደቀው አገራዊ አንድነታችን ምክንያት ከወገቡ ዝቅ ብሎና ከልቡ ተፀፅቶ የተበደለውን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት ዋነኛው ተጠያቂ ትህነግ/ህወሓት መሆኑን እንረዳለን፡፡ በተጨማሪም ትህነግ/ህወሓት ድርጅታችን አዴፓን በዚህ ደረጃ ጥርስ ውስጥ ያስገባበት መሰረታዊ መነሻ ለዘመናት ሲሰራው የነበረውን ጸረ - ህዝብና ጸረ - ዴሞክራሲያዊ ተግባር ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች ጋር ሆነን በግንባር - ቀደምትነት አምርረን በመታገላችንና ጥፋቱ በኢትዮጵያ ህዝቦች ፊት በመጋለጡ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ድርጅታችን አዴፓ በኢህአዴግ ግንባር ውስጥ ከትህነግ/ህወሓት ጋር አብሮ እየታገለ መቆየቱን የመረጠው ለትግራይ ህዝብ ካለን ክብር እንዲሁም ትህነግ/ሕወሓትም እራሱ ተፀፅቶ እራሱን ያርማል በሚል ተስፋ ቢሆንም ትህነግ/ሕወሓት በነበረበት ተቸክሎ የሚዳክር ድርጅት በመሆኑ ድርጅታችን አዴፓን ይቅርታ እንዲጠይቅና ከአዴፓ ጋር አብሮ ለመሥራትም የሚቸገር እንደሆነ አድርጐ መቅረቡ "ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ" የድርጅቱ የሴራ ፖለቲካ መገለጫ ነው፡፡

ትህነግ/ሕወሓት መቼም ቢሆን ከብልሹ ፖለቲካ የማይፈወስ ድርጅት በመሆኑ በተደጋጋሚ የህዝባችን የጐን ውጋት ሆኖ በተለያዩ የክልላችን አካባቢዎች እና አጐራባች ክልሎች ከግጭቶች ጀርባ መሽጐ እንደሚያዋጋ እያወቅንም፣ ለዚህም በርካታ ማስረጃዎች በእጃችን ላይ እያሉ ለህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነትና ለኢትዮጵያ አንድነት ስንል በሆደ-ሰፊነት ብንመለከተውም፣ ዛሬም እንደ ትላንቱ የትግራይ ህዝብ እንደሌሎች ወንድምና እህት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከችግር እና ሰቆቃ ባልተላቀቁበት ነባራዊ ሁኔታ ፣ የራሱን እኩይ ወንጀል ለመሸፋፈን፣ በትግራይ ህዝብ ሲምልና ሲገዘት የሚውል ህዝቡን ለጥቃት በሚያጋልጡ ተንኮሎች የተጠመደ የማይማር እና የማይድን ድርጅት ነው፡፡ በመሆኑም ትህነግ/ሕወሓት ጥርሱን ነቅሎ ባደገበት የሴራ ፖለቲካ እየተመራ፣ ከልክ በላይ በእብሪተኝነት ተወጥሮ በየአካባቢው ጦር እየሰበቀ እና በበሬ ወለደ አሉባልታ ወንድም የሆነውን የትግራይ ህዝብ በተለይም ወጣቱን ለጥፋት እያነሳሳ ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ እንዲሆን እየገፋፋው ይገኛል፡፡ 
በአጠቃላይ ድርጅታችን አዴፓ እና የአማራ ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለህዝቦች እኩልነት እንዲሁም ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ለእውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓትና ለእውነተኛ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት በፅናት የሚታገል እንጂ ተንኳሽ እና ጦር ሰባቂ እንዳልሆነ እየታወቀ በተሣሣተ መረጃ ጭቁኑን የትግራይ ህዝብ እና የኢትዮጵያን ብሄር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሌለ ስጋት በመፍጠር አዴፓንና የአማራን ህዝብ ተጠርጣሪ ለማድረግ የሚያደርገው ተከታታይ ቅስቀሳ መወገዝ ያለበት መሆኑን በፅኑ በማመን የሚከተሉትን የአብሮነትና የአጋርነት ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

1. ለመላው የድርጅታችን አዴፓ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ 
አዴፓ ህዝባዊነቱን እንደያዘ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እና ለብሔር፣ ብሔረሰቦች እኩልነት የታገለና የሚታገል የዛሬና የነገ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው፡፡ በመሆኑም ለዓላማዎቹ ግብ መሣካት መስዋዕትነት የከፈሉትን ጓዶች ዓላማ ዳር ለማድረስ በፅናት የሚታገል የአማራ ህዝብ ፓርቲ እንጂ እንደ ትህነግ/ሕወሓት ላሉ የሴራ ሃይሎች የሚያጐበድድ ፓርቲ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው በሰኔ 15/2011 ዓ.ም በደረሰብን አደጋ ጉዳታችን ጥልቅ ቢሆንም መላ መዋቅራችንን፣ ህዝቡንና የፀጥታ ሀይሉን ከጐናችን አሠልፈን እኩይ ሴራውን መቆጣጠራችንና እና ማክሸፋችን የሚታወቅ ነው፡፡ ክልላችን ከደረሰብን አደጋና ችግር ፈጥኖ እንዲወጣ ሰፊ የማረጋጋት ሥራ በመስራት አሁን ከመቸውም ጊዜ በላይ ወደ-ላቀ ጥንካሬያችን እየተመለስን ሲሆን፣ በወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፉ አካላትን ለህግ በማቅረብ ላይ ስንሆን፣ የምርመራ ሥራውም በጥብቅ ዲሲፕሊንና በተቀናጀ አግባብ እየተመራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም አጠቃላይ የምርመራ ሥራውንና የህግ ተጠያቂነትን የማረጋገጡን ተግባር በቁርጠኝነት ዳር የምናደርሰው ሲሆን በዚህ ወቅት አደጋውን ለመቀልበስ ከጎናችን ተሰልፎ ሊታገል የሚገባው እህት ድርጅት ትህነግ/ሕወሓት በድርጅታችን እና በአማራ ህዝብ ላይ የከፈተውን የጥፋት ዘመቻ በፅናት በመመከት ለአማራ ክልል ህዝቦች እኩል ተጠቃሚነትና ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት የጀመርነውን አገራዊ ለውጥ አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

2. ለክልላችን ህዝቦች እንዲሁም በኢትዮጵያና በመላው አለም የምትገኙ የአማራ ተወላጆች 
አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን ጠብቀንና ህብረታችንን አጠናክረን፣ የቀደመ ታሪካችንን ሣንሸራርፍ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ለብሔር፣ ብሔረሰቦች እኩልነት፣ በአብሮነት መንፈስ በፅናት የምንታገልበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆናችን፣ የበለጠ የሚያስተሳስረንና የሚያዋህደን እንጂ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሚሸረብ ሴራ የማንለያይና የማንነጣጠል በመሆናችን፣ የትላንት እኩይ ሴራቸውን ዛሬም ሣይረሱ ወቅታዊ ችግሮቻችን እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም አንገት ሊያስደፉን ከሚፈልጉ ትህነግ/ሕወሓትና መሰል የጥፋት ሃይሎች የማንበገር መሆናችንን በፅናት እየገለፅን ከድርጅታችን አዴፓ ጐን ተሰልፋችሁ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም፣ ቀጣይነት ለሚኖረው ልማትና ዋስትና ላለው ዴሞክራሲ በአንድነት እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

3. ለተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ 
ድርጅታችን አዴፓ እና የአማራ ህዝብ ባጋጠመው ፈተና ሁሉ ከጐናችን በመሰለፍ አጋርነታችሁን ስላረጋገጣችሁልን በዚህ አጋጣሚ ምስጋናችንን እያቀረብን ዛሬም እንደትላንቱ ለኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት፣ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የፌዴራሊዝም ስርዓት፣ እንዲሁም ለሃቀኛ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ከጐናችሁ ሆነን በፅናት የምንታገል መሆኑን እያረጋገጥን፣ ትህነግ/ሕወሓት የዘመናት ወንጀሎቹን ለመሸፈን እና ድርጅታችን አዴፓና የአማራ ህዝብን የሌሎች ህዝቦች ጠላት በሚያደርግ የተሳሳተ አስተምህሮ ዛሬም በጥርጣሬ እንድንተያይ የሚነዛውን የማደናገሪያ ትርክት መሰረተ ቢስ መሆኑን እንደምትገነዘቡ ጽኑ እምነት ያለን ሲሆን ይህን ጸረ ዴሞክራሲና አስመሳይነት ከጐናችን ተሰልፋችሁ በፅናት እንድትታገሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

4. ለተከበርከው የትግራይ ህዝብ 
የአማራና የትግራይ ህዝቦች ታሪካዊ አንድነትና ውህደት ያላቸው፣ ባህላዊና ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚጋሩ፣ በጋብቻና በደም የተሳሰሩ፣ በፀረ-ጭቆና ትግል ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሆነው በአንድ ጉድጓድ ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አሁን ላለንበት የአገረ-መንግስት ምስረታ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ህዝቦች ናቸው፡፡ ሆኖም ትህነግ/ሕወሓትና መሠል እኩይ ድርጅቶች በህዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ፣ በትግራይ ህዝብ ስም እየነገዱ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀውን የአብሮነት ታሪካችንን በአራት አስርት አመታት የበሬ ወለደ ትርክቶች ለመሸርሸርና ህዝባዊ አንድነታችንን አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉት ሴራ መሆኑን አውቃችሁ ከአማራ ህዝብ ጋር ያላችሁ ወንድማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነታችሁ ሳይቋረጥ ሁለቱን ህዝቦች የሚያለያዩ ሙከራዎችን በፅናት እንድትታገሉ የከበረ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡

5. ለእህትና ለአጋር የፖለቲካ ድርጅቶች
እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን ኢትዮጵያ ካሏት ዘርፈ ብዙ ጸጋዎችና እሴቶች መካከል ብዝሀነታችን የምንደምቅበት ጌጣችን መሆኑ ለአፍታም ቢሆን አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ትህነግ/ህወሓት ይህን የብዝሀነት ጸጋ ጠብቆ ለማስቀጠል ብቸኛ ተቆርቋሪ በመምሰል ሲያሻው ደግሞ በህዝቦች መካከል የጥርጣሬ አጥር በመፍጠር ህዝባዊ አንድታችንን ለማላላት የከፋፋይነት ፖለቲካውን ሲያራምድበት በመቆየቱ ምክንያት በለውጥ መድረካችን በአንድነት የረገምነው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ዛሬም እንደትላንቱ ለብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ የተለየ ትኩረት የሰጠ በመምሰል ይህንኑ የአስመሳይነት ድራማውን በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ሲተውን የሚስተዋል ስለሆነ ይህን መሰል እኩይ ተግባር በአንድነትና በጽናት በመፋለም ህዝባዊና አገራዊ አንድነታችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ አጠናክረን እንድናስቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

6. ለኢፌዴሪ የአገር-መከላከያ ሠራዊትና ለክልላችን የፀጥታ ሃይሎች 
ድርጅታችን አዴፓ እና የአማራ ህዝብ የአገር መከላከያ ሠራዊታችንና የክልላችን የፀጥታ ሃይሎች ህዝባዊነታችሁን ጠብቃችሁ ለአንዲት ሉአላዊት አገር መከበርና ቀጣይነት ክቡር መስዋዕትነት በመክፈል ላይ መሆናችሁን እንገነዘባለን፡፡ ጥንትም ቢሆን ኢትዮጵያ የተመሰረተችውና ጸንታ የቆየችው በጀግኖች አርበኞቻችን ተጋድሎና መስዋዕትነት በመሆኑ፣ በቅርቡም አጋጥሞን በነበረው አደጋ ፈጥኖ ደራሽነታችሁን በማረጋገጥ ክልላችንና አገራችንን ከጥፋት በመታደጋችሁ ምስጋናችንን እያቀረብን ወደፊትም የአገራችንን ሉአላዊነትና የክልላችንን ሁለንተናዊ ደህንነት በማስጠበቅ ሂደት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ በፅናት በማለፍ ህዝባዊነታችሁን እንድታረጋግጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም በክልላችንም ሆነ ከክልላችን ውጪ በአማራና በክልሉ ህዝቦች ስም የምትንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች እየሰፋና እየጠነከረ በመጣው የፖለቲካ ምህዳር አዎንታዊ ሚና እድትጫወቱ ጥሪያችንን እያቀረብን በሌላ በኩል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የትህነግ/ሕወሓትን የፖለቲካ ደባ የምታስፈፅሙ ተላላኪ የፖለቲካ ሃይሎችና ቡድኖች ከዕኩይ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ በጥብቅ እያሳሰብን ድርጅታችን አዴፓም ሆነ የአማራ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔሰቦች ጋር ሆነን ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እና ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የሚደረገውን ትግል አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡
የአዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ 
ሐምሌ 4/2011 ዓ.ም

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa