በአማራ ክልል የተሻለ እና አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ
በአማራ ክልል የተሻለ እና አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ሕጋዊ ትጥቅን ‹‹የማስፈታት ሥራ እንደተጀመረ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ከእዉነት የራቀ ነዉ›› ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን እና ሚዲያ ልማት ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሰኢድ አህመድ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት በተለይ በተያዘው ሳምንት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ይፈፀም የነበረው መደበኛ ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡ የፀጥታ መዋቅሩ ሕግና ሥርዓትን በማስከበር አስተማማኝ ሠላም ለማስፈን በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ የተፈጠረውን ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወንጀል አድራጊዎች ሊበራከቱ እንደሚችሉ ሕብረተሰቡ ቀድሞ በመረዳት በየአካባቢው ጠንካራ ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ እና ለፖሊስ ጥቆማ በማድረስ በክልሉ አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ነው ምክትል ኮሚሽነር ሰኢድ ያስታወቁት፡፡ በፀጥታ መዋቅሩ እና በሕብረተሰቡ ትብብር የተገኘውን የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን በመናገር ኅብረተሰቡም የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክልሉ የጦር መሣሪያ የማስፈታት እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ውዥምብር ውስጥ እንዳይገባም ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡ መመሪያዉ በሚፈቅደው መሠረት በ2011 ዓ.ም ሕብረተሰቡ የግል ትጥቁን ሕጋዊ አድርጎ እንዲንቀሳቀስ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ‹‹ሕጋዊ ትጥቅ እንዲኖር የፈቀደ መንግሥት ትጥቅን የሚያስፈታበት ምንም ምክንያት የለውም›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ በሕገ-ወጥ ትጥቅ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ግን የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለሕዝብ ደኅንነት እና አስተማማኝ ሠላም ሲባል በሕገ-ወጥ መንገድ ከአጎራባች ሀገራት ወደ ክልሉ የሚገቡትንም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚዘዋወሩ የጦር መሣሪያዎችን ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ቁጥጥር እየተደረገባው እንደሆነም አመላክተዋል፡፡ ቁጥጥሩ ያለሕጋዊ ፈቃድ የጦር መሣሪያ የታጠቁ አካላት ላይም ተግባራዊ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡ ይህንን ተከትሎ ሕጋዊ ትጥቅ ያላቸውን የማስፈታት ሥራ እንደተጀመረ ተደርጎ የሚሰራጨው ሀሰተኛ መረጃ የክልሉን ሕዝብ ወደ ብጥብጥ እንዲገባ ለማነሳሳት ታስቦ የሚሠራጭ የአሉባልታ ወሬ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ሊጠነቀቅ እንደሚገባም ነው ምክትል ኮሚሽነር ሰኢድ ያስታወቁት፡፡
ምንጭ፡- Amhara Mass Media Agency
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ