ድርጊቱንም ዜናውንም የመሥራት አባዜ
ድሮ ያነበብኩት አንድ መጽሐፍ ነበር፡፡ ሰውዬው አንድ ታዋቂ ጋዜጣ ማዘጋጀት ፈለገ፡፡ ጋዜጣው ማንም ያላገኘውን ዜና ማግኘትና ቀድሞ ዜናውን ማግኘት አለበት ብሎ ወሰነ፡፡ ይሄንን ለማድረግ የተከተለው ስልት ‹ተግባሩንም ዜናውንም መሥራት› የሚል ነበር፡፡ መኪና ለመጥለፍ ያቅዳል፤ ዜናውን ሠርቶ ወደ ማተሚያ ቤት ይልክና ሊወጣ ሲል መኪናው ይጠልፈዋል፡፡ ተግባሩንም ዜናውንም ስለሚሠራው ማንም አይቀድመውም፤ ማንም አያገኘውም፡፡ አውሮፕላን ጠልፏል፣ ፋብሪካ አቃጥሏል፣ ባንክ አስዘርፏል፤ ሰዎች አስገድሏል፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ዜናውን አስቀድሞ እንደ ፊልም ስክሪፕት ራሱ ይጽፍና ጋዜጣውን ካዘጋጀ በኋላ ነበር ድርጊቱንም ራሱ ይፈጽመዋል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ሰዎች ሁሉ በአድናቆት የሚያነቡት ጋዜጣ ሆነ፡፡ ሌሎች ሚዲያዎች ሪፖርተሮቻቸውን ወቀሱ፡፡ የሌሎች ጋዜጣ ደንበኞችም እየፈለሱ ወደዚህ ጋዜጣ ሄዱ፡፡ ነገሩ ግን ከዚህም በላይ አስደናቂ መሆን ጀመረ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ድርጊቱና ጋዜጣው በተመሳሳይ ሰዓት መውጣትና መፈጸም ጀመሩ፡፡ ይባስ ብሎም ጋዜጣው ከድርጊቱ ቀድሞ መውጣት ጀመረ፡፡ ይሄን ጊዜ ብልሆች ተጠራጠሩ፡፡ የተወሰኑ አካላት ምርመራ ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም ደረሱበት፡፡ የጋዜጣው ቀዳሚነትና ብቸኛ የዜና ምንጭነት ምክንያት፣ ድርጊቱንም ዜናውንም አንድ ሰው ስለሚሠራው መሆኑ ታወቀ፡፡ ያው ዘብጥያው ይመቻችለታል እንግዲህ፡፡ ሕወሐት ተነካሁ፣ ተመታሁ፤ ተጠቃሁ ማለት ጀምሯል፡፡ ለዚህ ኡኡታው መቅድም ነበረው፡፡ መጀመሪያ ድርድሩ አይሳካም አለ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠ፡፡ ቀጠለና በምዕራብ በኩል ተጠቃሁ አለ፡፡ ከዚያ የተናጠል የተኩስ አቁሙ ፈርሷል አለ፡፡ አስከትሎ ደግሞ በየሀገሩ ያሉ ተከፋይ የነጭ ሠራዊቱን ማንጫጫት ጀመረ፡፡ የበጋ ስንዴን ከመቃወም ጀምረው የኢትዮጵያ አየር መ...