ድርጊቱንም ዜናውንም የመሥራት አባዜ
ድሮ ያነበብኩት አንድ መጽሐፍ ነበር፡፡ ሰውዬው አንድ ታዋቂ ጋዜጣ ማዘጋጀት ፈለገ፡፡ ጋዜጣው ማንም ያላገኘውን ዜና ማግኘትና ቀድሞ ዜናውን ማግኘት አለበት ብሎ ወሰነ፡፡ ይሄንን ለማድረግ የተከተለው ስልት ‹ተግባሩንም ዜናውንም መሥራት› የሚል ነበር፡፡ መኪና ለመጥለፍ ያቅዳል፤ ዜናውን ሠርቶ ወደ ማተሚያ ቤት ይልክና ሊወጣ ሲል መኪናው ይጠልፈዋል፡፡ ተግባሩንም ዜናውንም ስለሚሠራው ማንም አይቀድመውም፤ ማንም አያገኘውም፡፡ አውሮፕላን ጠልፏል፣ ፋብሪካ አቃጥሏል፣ ባንክ አስዘርፏል፤ ሰዎች አስገድሏል፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ዜናውን አስቀድሞ እንደ ፊልም ስክሪፕት ራሱ ይጽፍና ጋዜጣውን ካዘጋጀ በኋላ ነበር ድርጊቱንም ራሱ ይፈጽመዋል፡፡
መጀመሪያ አካባቢ ሰዎች ሁሉ በአድናቆት የሚያነቡት ጋዜጣ ሆነ፡፡ ሌሎች ሚዲያዎች ሪፖርተሮቻቸውን ወቀሱ፡፡ የሌሎች ጋዜጣ ደንበኞችም እየፈለሱ ወደዚህ ጋዜጣ ሄዱ፡፡ ነገሩ ግን ከዚህም በላይ አስደናቂ መሆን ጀመረ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ድርጊቱና ጋዜጣው በተመሳሳይ ሰዓት መውጣትና መፈጸም ጀመሩ፡፡ ይባስ ብሎም ጋዜጣው ከድርጊቱ ቀድሞ መውጣት ጀመረ፡፡ ይሄን ጊዜ ብልሆች ተጠራጠሩ፡፡
የተወሰኑ አካላት ምርመራ ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም ደረሱበት፡፡ የጋዜጣው ቀዳሚነትና ብቸኛ የዜና ምንጭነት ምክንያት፣ ድርጊቱንም ዜናውንም አንድ ሰው ስለሚሠራው መሆኑ ታወቀ፡፡ ያው ዘብጥያው ይመቻችለታል እንግዲህ፡፡
ሕወሐት ተነካሁ፣ ተመታሁ፤ ተጠቃሁ ማለት ጀምሯል፡፡ ለዚህ ኡኡታው መቅድም ነበረው፡፡ መጀመሪያ ድርድሩ አይሳካም አለ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠ፡፡ ቀጠለና በምዕራብ በኩል ተጠቃሁ አለ፡፡ ከዚያ የተናጠል የተኩስ አቁሙ ፈርሷል አለ፡፡ አስከትሎ ደግሞ በየሀገሩ ያሉ ተከፋይ የነጭ ሠራዊቱን ማንጫጫት ጀመረ፡፡ የበጋ ስንዴን ከመቃወም ጀምረው የኢትዮጵያ አየር መንገድን እስከ ማሳጣት ተረባረቡ፡፡ በመጨረሻም ዛሬ ጦርነት ተከፈተብኝ አለ፡፡ እስክስታው ቀድሞ ስለመጣ፣ ዘፈኑ እንደሚከተል ይጠበቅ ነበር፡፡
ለመሆኑ ሕወሐት ለምን ቀድሞ ጮኸ? መልሱ ቀላል ነው፡፡ ድርጊቱንም ዜናውንም ራሱ ስለሠራው ነው፡፡ እንደ ፊልም ጽሑፍ አስቀድሞ ዜናውን አዘጋጀ፡፡ ከዚያ የተለመደ ትንኮሳውን ጀመረ፡፡ በዚህ የተነሣ ዜናውና ትንኮሳው በተመሳሳይ ሰዓት ተፈጸመ፡፡ አንዳንዶች ምሥጢር መጠበቅ ያቃታቸው ወዳጆቹ ደግሞ፣ ከተግባሩ በፊት ዜናውን ለቀቁት፡፡ ተጠቃሁ ከማለቱ በፊት ገደልን ብለው ፕሮፓጋንዳውን አበላሹበት፡፡
ከዚህ በፊትኮ ‹ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች ጋር እየተገናኘን ነው› ብሎ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ ታድያ በድብቅ ተገናኘን ካላችሁ በይፋ ለመገናኘት ለምን ከበዳችሁ? ለምን የድርድሩን መንገድ ፈራችሁት? ‹በሽታው እንዲታወቅ የማይፈልግ ሰው ሐኪም ቤት አይሄድም› ሆኖባችሁ ካልሆነ በቀር፡፡ ሕዝቡስ አያሳዝናችሁም? ትግራይን ያለ ትውልድ ማስቀረት አያሳዝናችሁም? ሁለት ጊዜ ያደረጋችሁት ጦርነት መጨረሻው ‹እንትን ይግባ፣ እንትን ይለቀቅ፣ እንትን ይሰጠን› ብሎ ከመለመን የዘለለ ምን አመጣላችሁ? ይልቅ ወደ ድርድሩ ጠረጲዛ ወርዳችሁ ለሕዝቡ አገልግሎት ስለሚለቀቅበት መንገድ፣ ርዳታው ያለ እንከን ስለሚቀርብበት መንድ፣ ሕዝቡ ከሌላው ወገኑ ጋር ስለሚገናኝበት መንገድ አትመክሩም?
‹የአገልግሎቶች ጉዳይ ፖለቲካዊ ሳይሆን የአፈጻጸም ችግር ነው? እንዴት እንፈጽመው በሚለው ላይ እንምከር› ስትባሉ፣ ለሕዝብ ስትሉ ሲኦልስ ድረስ መሄድ አልነበረባችሁም? መቀሌ የተቀመጡ ፕሮፓጋንዲስቶቻችሁን ‹አንተ ከቆቦ፣ አንተ ከወልድያ፣ አንተ ከራያ፣ አንተ ከወልቃይት ነኝ ብለህ ተናገር› እያላቸሁ ለውጭ ሚዲያ ስላስተላለፋችሁ መሬት ላይ ያለው ነገር ይቀየራል?
እነዚህ ሚዲያዎችኮ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ስትለብስ አታሳዩኝ፣ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ስትጥለቀለቅ አትጥሩኝ፣ ኢትዮጵያ ድል ስታደርግ አትንገሩኝ፣ ኢትዮጵያ ግድቧን ስትሞላ አትቀስቅሱኝ ሲሉ ነበር፡፡ ሁለታችሁም ከጦርነት ብቻ ስለምታተርፉ የአጋምና ቀጋ ወዳጅነት ፈጥራችሁ፣ የሕዝቡን መከራ አበዛችሁበት፡፡ ችግሩንም ዜናውንም አብራችሁ እየሠራችሁ የጅራፉን ነገር ደገማችሁት፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ትንኮሳዎች ተፈጽመዋል፡፡ ነገር ግን ትንኮሳዎቹን ከመመከት ባለፈ መከላከያው ከምንም ነገር ታቅቦ ሲጠብቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ዋናው የመፍትሔ አማራጩ የሰላሙ መንገድ መሆኑን ዐቋም ስለያዘ፡፡ አሁንም እንኳን ይሄንን አቋሙን አልቀየረም፡፡ ‹ጥላቻ ሕይወቴ፣ ጦርነት ርስቴ፣ ውሸት እስትንፋሴ፣ ዕብሪት ደመ ነፍሴ› ብሎ የሚያምነው ሕወሐት ግን፣ አጉራ ጠናኝ ብሏል፡፡
ለሰላም የተዘረጉ እጆች አሁንም አልታጠፉም፤ አይታጠፉም፡፡ እነዚህን እጆች ደጋግሞ መውጋት ግን፣ የሰላም እጆች ሌላ ነገር እንዲጨብጡ ያስገድዳቸዋል፡፡
VIA:Dire Tube(ይነገር እውነቱ)
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ