የዶ/ር ነጋሶ “የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ” መፅሐፍ

አንጋፋው የታሪክ ምሁርና ፖለቲከኛ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የፃፉትና በአዳዲስ የምርምር ውጤቶች ላይ ተመስርቶ እንደተዘጋጀ የተነገረለት “የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ” የተሰኘ አዲስ መፅሃፍ ዛሬ በገበያ ላይ ይውላል ተብሏል፡፡ መፅሃፉ የኦሮሞ ህዝብ አመጣጥ ታሪክ ላይ ከዚህ ቀደም የሚታወቁ እውነታዎችን የሚሞግት ሲሆን የኦሮሞ ታሪክ በኢትዮጵያ የሚጀምረው በ16ኛው ክ/ዘመን እንደሆነ ሲገለፅ የቆየው የተሳሳተ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ማስተማሪያ መፃህፍት ላይ ሳይቀር የኦሮሞ ህዝብ በ16ኛው ክ/ዘመን መነሻውን ከባሌ መደወላቡ አድርጎ ወደ ሰሜን መስፋፋቱ ተተርኳል የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ የኦሮሞ ህዝብ ከ16ኛው መቶ ክ/ዘመን በፊት፣ ከላሊበላ የስልጣኔ ዘመን ጀምሮ በሰሜኑና መካከለኛው የሀገሪቱ ክልል የኖረ ህዝብ ነው፤ ብለዋል፡፡

ማህበረሰቡ ከሰሜን ወደ ደቡብ የተስፋፋ እንጂ ከደቡብ ወደ ሰሜን የተስፋፋ አለመሆኑን ዶ/ር ነጋሶ በመጽሐፋቸው ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ውስጥ ሲማሩ፣ መምህራቸው ፕ/ር ዶ/ር ታደሰ ታምራት፤ “የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖትና የክርስቲያን ዐፄ አገዛዝ ወደ ደቡብ መስፋፋት” የሚለውን የታሪክ ክፍል ሲያስተምሯቸው፣ በ13ኛው ክ/ዘመን በሰሜን ሸዋ ገላና እና ያያ የሚባሉ ህዝቦች ቆርኬ ለሚባል አምላክ ይሰግዱ እንደነበር የነገሯቸውን መሰረት አድርገው ምርምር ማካሄዳቸውን ዶ/ር ነጋሶ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

በመፅሃፉ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ጎሳዎችን የትውልድ ሀረግ ቆጠራዎች እንዲሁም፣ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን በማጣቀስ፣ የኦሮሞ ህዝብ ፍሰት ከሰሜን ወደ ደቡብ እንደነበር ምሁሩ ማሳየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በተለይ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ያለው መስተጋብር በመጽሐፋቸው መዳሰሱን የጠቆሙት ዶ/ር ነጋሶ፤ ከ18ኛው ክ/ዘመን እስከ ዐፄ ምኒሊክ ዘመን ድረስ የተካሄዱ ጦርነቶችንና ውጤቶቻቸውንም በጥልቀት መመርመራቸውን አስረድተዋል፡፡

408 ገፆች ያሉት “የኦሮሞ ታሪክ” የተሰኘው መፅሃፍ፤ በዛሬው እለት ለገበያ የቀረበ ሲሆን መፅሀፉ ለአገር ውስጥ በ120 ብር፣ በውጭ አገራት  በ25 ዶላር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ በመፅሃፋቸው ያቀረቡትን የኦሮሞ ታሪክ አመጣጥ በተመለከተ የተጠየቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሞ ህዝብ በሰሜንና በመካከለኛው ኢትዮጵያ ከ13ኛው ክ/ዘመን በፊት ይኖር እንደነበር የሚያሳዩ የኦሮሞ ስሞችና ሌሎች የታሪክ ፍንጮች እየተገኙ መሆኑን መረዳታቸውን ጠቁመው፤ ፍንጮቹ የኦሮሞ ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ16ኛው ክ/ዘመን ነው የሚለው ታሪክ በድጋሚ ሊፈተሽ እንደሚገባ ያመላክታል ብለዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ መሠረት የሚያደርገው ማህበረሰብን ሳይሆን ነገስታትን ነው” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ይሄ አካሄድ የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሌላውም በተለይ የኩሽ ህዝቦች ታሪክ ላይ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል፡፡ በተለያዩ የታሪክ ሰነዶች ላይ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የነበሩት ህዝቦች የኩሽ ህዝቦች መሆናቸው ተጠቅሷል፤ ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ጐልቶ የሚነገረውና ተሰንዶ የሚገኘው ግን የሴም ህዝቦች ታሪክ ነው፤ ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ትልቁ የኩሽ ዘር እንደመሆኑ፣ በ16ኛው ክ/ዘመን የመጣ ነው የሚለው አያስኬድም በማለት፣ በማህበረሰቡ አመጣጥ ላይ ሠፋፊና ጥልቅ ጥናቶች ሊካሄዱ ይገባል፤ ብለዋል፡፡

ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa