የሰቡት ዋጋቸው ውድ ነው፤ የጉፋያዎቹን ንገሩን

 አንዳንድ ተረት ካልተደጋገመ የሚሰማ የለም፡፡ ይሄንንም በድጋሚ አቅርበነዋል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ትልቅ ዝሆን አንድ ትልቅ ገደል ውስጥ ወድቆ ይሞታል፡፡ ሌሊቱን የተራቡ ጅቦች ወደ ገደሉ አፋፍ መጥተው፣ ዞር ዞር ሲሉ ዝሆን እጅግ አዘቅት በሆነው ገደል ውስጥ ገብቶ መሞቱን አዩ፡፡
ከፊሎቹ ጅቦች፤
“እንዴት ግዙፍና የሰባ ዝሆን ነው?”
ኧረ እንግባና የተራበ አንጀታችንን እናርስ!” አሉ፡፡
አንዳንድ ብልህ ጅቦች ግን፤
“ኧረ ጐበዝ! እጅግ ሩቅ ወደሆነው ወደዚህ ጉድጓድ ገብተን፤ ኋላ ሆዳችን ሲሞላ ተመልሰን ወደ ገደሉ አፋፍ መውጣት የማይሞከር ነገር ነው” አሉ፡፡
ብዙዎቹ ጅቦች፤
“እቺን ዳገት ብላችሁ ታወራላችሁ? ተደጋግፈን ፉት እንላታለን፡፡ ይልቅ በረሃብ ሳንሞት ቶሎ እንወስን”
ጥቂቶቹ ጅቦች፤
“ኧረ ይሄ ገደል የዋዛ አደለም ጐበዝ! አንዴ ከገባን መመለሻም የለን”
ብዙዎቹ ጅቦችም፤
“የምትጨቃጨቁን ከሆነ፤ ያለው መፍትሔ ድምጽ እንስጥና አብላጫውን ድምጽ ያገኘው አሸናፊ ይሁን!”
ይሄው ዋናው የውሳኔ ሃሳብ ሆነና
“ድምፅ ይሰጥ” ተባለ፡፡
ድምጽ ተሰጠ፡፡
“ወደ ገደሉ ገብተን የሞተውን ዝሆን እንብላና ረሃባችንን እንመክት!” ያሉት አሸነፉ፡፡
ጅቦቹ ሁሉ ተንደርድረው፣ ተግተልትለው፣ ወደ ገደሉ ገቡ፡፡
ያን ድልብ ዝሆን ተያያዙት፡፡
ጠገቡ፡፡ ለጥ ብለው ተኙ፡፡ ነጋ፡፡
የተረፈውን ተቀራመቱ፡፡ ቀናት እየገፉ ሲሄዱ የዝሆኑ ስጋ ተመናመነና አለቀ፡፡
ቀና ብለው የገደሉን ጫፍ አዩት፡፡
በጭራሽ የሚሞከር ነገር አይደለም፡፡
“ኧረ እንዴት ነው ይሄን ገደል የምንወጣው?”  አለ አንዱ ጅብ፡፡
ብዙዎቹ ጅቦች፤
“እስቲ ማታውን አድረን እናስብበትና ጠዋት መላ እንመታለን” አሉ፡፡
ነገም መጥቶ አፈጠጠ፡፡ ዘዴ ግን ከቶ አልተገኘም፤ የዝሆኑ አይደለም ስጋው አጥንቱም አልቋል፡፡ ስለዚህ በራሳቸው በጅቦቹም መንደር ረሃብ ገባ፡፡ ረሀብ መጣ፡፡
አንድ ሌሊት ሁሉም ጅቦች ለጥ ብለው ባሉበት፤ አንድ ሁለት ጅቦች ነቁ፡፡
ምክር ጀመሩ፡፡ አንደኛው ጐኑ ላለው፤
“መቼም በረሃብ ከምንሞት እንቅልፍ የወሰደውን አንዱን ጅብ ብንበላ እሰየው ነው፡፡ ምን ይመስልሃል?”
ሁለተኛው፤
“ጐንህ ያለውን ቀስቅሰውና ሃሳቡን አካፍለው” አለው፡፡ ያም እንዳለው አደረገ፡፡
ደሞ ያኛውም ጐኑ ላለው ቀጠለ፡፡ የመጨረሻው፣ ዳር ላይ ያለው፣ እንዳንቀላፋ ተበላ!
ይሄ ሂደት ቀጠለ፡፡ በሚቀጥለው ሌሊት ዳር ላይ ያንቀላፋ ተበላ! እንዲህ እንዲህ እያለ ያ ሁሉ ጅብ ተራ በተራ ተበላ! በመጨረሻ ሁለት ብቻ ቀሩ፡፡ አንዱን በጣም ያንቀላፋ ጅብ፣ ሌት አንደኛው ቅርጭጭ አረገው!
አንድ ብቻውን የቀረውን፤ እንደፈረደበት ረሀብ ራሱ በላው!!
***
እርስ በርስ የመበላላት ባህል የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ ከታሪክ እስከ ዛሬ፡፡ ወይ በፖለቲካ ሽኩቻ፣ ወይ በኢኮኖሚ ድቀት አሳቻ፣ ወይ በባህል ልምሻ ዛቻ፣ ወይ በሶሻል ቀውስ ውድቀት አቻ፤ …አገር መበላላትን መቀበል ከጀመረችና ካመነች ቆይታለች፡፡ አያሌ የፖለቲካ ድርጅቶችን አይታለች፡፡
አስገራሚው ነገራችን፤ ትላንት የተበላውን ዛሬ በቦታው የተቀመጠው ጠንቅቆ ለማስተዋል አለመቻሉ! “የማስጠንቀቂያውን ደወል” እንኳን ሳያይ፣ ያለፈውን መራገምና ራሱን መልዐክ ማድረግ፣ ነው ፈሊጡ፡፡ አልፎም ተፈጥሮዬ ነው እስከማለት ደርሶ ወንበሩን ሙጥኝ ማለቱ፡፡ ቀጥሎም በራሱ ጊዜ “አወዳደቄን አሳምርልኝ!” ሳይል የቀደመው ባለስልጣን በወደቀበት መንገድ መንኮታኮቱ ነው፡፡ ስለ ምን አንዱ ካንዱ አይማርም? አካሄዱንስ ስለ ምን አይለውጥም? ኢ-ፍትሐዊነትን፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊነትን፣ ሙስናን እንቋቋማለን ተብሎ በተነገረ ማስትግ፣ እዚያው ጥፋት ውስጥ ተዘፍቆ መገኘት እጅግ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን እጅግ አናዳጅም ነው፡፡ በተለይ ስለመልካም አስተዳደር መበላሸት በሰፊው እየተወራ፣ እዚያው ብልሹነት ማጥ ውስጥ በፊት ለፊት ተውጠው የሚታዩ የበላይ ኃላፊዎች ለሀገርም ለህዝብም ጠንቅ መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ መነሳትም አለባቸው፡፡ ህዝብ በኃላፊነት በሰጣቸው ቦታ ላይ ነውና ምዝበራውን ያካሄዱት፣ በከፍተኛ ደረጃ ነው መጠየቅ ያለባቸው፡፡
“በልቼ ልሙት” የማለት ፈሊጥ፤ ተጠናውቶናል፡፡ የሸጥኩትን፣ የሸቀልኩትን በተለያየ ስም ያስቀመጥኩትን፣ ንብረትና ገንዘብ ብታሰርም እየበላሁ እኖራለሁ የሚለው አስተሳሰብ በሰፊው የተንሰራፋ ይመስላል፡፡ ገንዘብን በሺዎች መቁጠር ከቀረ ሰንብቷል፡፡ ምዝበራውን ለመከላከል የተወሰነ ክልል ባለስልጣናት ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን ሁሉንም ክልሎች መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ዕቅድና አፈፃፀምን ማስታረቅን የግድ ይላል፡፡ ይህ መደረግ ያለበት ነው!
ባሳለፍነው ሳምንት የነፃ ፕሬስ ቀንን አክብረናል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓሉ ሲከበር ትኩረት ይደረግባቸው ያላቸውን የፕሬስ ነፃነት መርሆዎች መከበርንና የሚዲያ ተቋማት ምን ያህል ነፃ ናቸው የሚሉ ጥያቄዎችን፣ ማውጠንጠን እጅግ ተገቢ ነው፡፡ አብሮም የዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ወቅታዊ ድባብ መፈተሸ ዋና ነገር ነው፡፡ ፈትሾ መቀመጥና የግምገማ ነጥቦችን መደርደር ብቻ ሳይሆን ሁነኛ የእርምት እርምጃ መውሰድ ወሳኝ ነው፡፡ አለበለዚያ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው የሚሆነው! ተገምግመው እርምጃ ያልተወሰደባቸው ሰዎች አያሌ ናቸው፡፡ አንድም “እሱን ነክተን ማ ይተርፋል” በሚል፤ አንድም “እጅግ ከፍ ያለ ቦታ” በመሆኑ ይዘለላልና ነው፡፡ የመጀመሪያው የሰንሰለት (Network) ጉዳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው አንቱ የተባሉ ሰዎች ተጠያቂ ያለመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ የህግ የበላይነት፣ ከህግ በላይ ያሉ ሰዎች እንደሌሉ የሚያረጋግጥ መርህ ነውና በተግባር መታየት አለበት፡፡ አለበለዚያ ህዝብ፤ “የሰቡት ዋጋቸው ውድ ነው፤ የጉፋያዎቹን ንገሩን” ሲል መኖሩ ነው፡፡

ምንጭ አዲስ አድማስ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa