ግጭት ተከስቶባቸው የነበረባቸው የቡኖ በደሌ ዞን ሁለት ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ወደ መረጋጋትና ሰላም ተመልሰዋል
በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ሁለት ወረዳዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለፀ።
የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ትናንት ማምሻውን በስጡት መግለጫ፥ ግጭቱ ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የፌደራል ፖሊስና የሃገር መከላከያ ስራዊት መግባታቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናት በደረሰው ግጭትም የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፥ “መንግስት በድርጊቱ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል፤ ለሟች እና ለተጎጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ይመኛል” ብለዋል።
በግጭቱ 1 ሺህ 500 ሰዎች መፈናቀላቸውን የተናገሩት ዶክተር ነገሪ፥ የአካባቢው ህብረተሰብ፣ የፌደራል እና የክልል መንግስታት ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው ብለዋል።
የሀገሪቱን ህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸር በሚፈልጉ እና የመንግስት እና የህዝብን ሀብት ሲመዘብሩ በነበሩ አካላት የተቀነባበረ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ሃይሎች ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት
ማድረጋቸውን እና በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው የፌደራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ሁኔታውን
ለማረጋጋት በስፍራው እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የሰው ህይወት ሳይጠፋ እና የንብረት ጉዳት ሳይደርስ ግጭቱን መቆጣጠር ያልተቻለውም የግጭቱ ፈጣሪዎች የተደራጁ ሃይሎች በመሆናቸው ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።
በአሁኑ ወቅት በደረሰው ጉዳት እጃቸው አለበት በሚል የተጠረጠሩ 43 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን እርምጃው እንደሚቀጥል እና በአሁኑ ወቅት አካባቢው በተሻለ ሰላም ላይ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።
በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችም ንብረታቸውን የአካባቢው ህብረተሰብ እየጠበቀላቸው ሲሆን፥ ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም ግጭቱ ያን ያህል ጉዳት እስኪያደርስ የፀጥታ ሃይሎች
የት ነበሩ ለሚለው ጥያቄ ዶክተር ነገሪ ሲመልሱ እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችን የሚፈጥሩ አካላት የሚመርጡት ቦታ ራቅ
ያለ እና መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸውን አካባቢዎች በመሆኑ ነው የከፋ ጉዳት የደረሰው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አካባቢውን ለማረጋጋት እና የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት አጠናክሮ ለማስቀጠል ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ምክክር መደረጉን ገልፀዋል።
መንግስት የህዝብን አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸር እና ሀገርን ለማተራመስ የተነሱ አካላትን ዓላማ ለማክሸፍ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ከነገ ጀምር በአካባቢው በመገኘት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መመልከት እና መዘገብ እንደሚችሉም ነው ዶክተር ነገሪ የተናገሩት።
Source:Fana Broadcasting Corporate(FBC)
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ