ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠራ

ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹የአገራችን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታና የፓርቲያችን ርዕዮተ ዓለም›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ፣ በመጪው እሑድ ጥቅምት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክበብ አዳራሽ ሕዝባዊ ስብሰባ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ይህን ያስታወቀው ማክሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽሕፈት ቤት፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡
ሕዝባዊ ስብሰባውን ለማከናወን አስፈላጊውን ሒደት ማሟላታቸውንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትም ለሕዝባዊ ስብሰባው ዕውቅና መስጠቱን፣ የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹በዕለቱም ምሁራንንና አንጋፋ ፖለቲከኞችን ጋብዘናል፡፡ ለዚህች አገር በጋራ ተወያይተን ምን ማድረግ ይቻላል የሚለውን ነገር የምናነሳ ሲሆን፣ ሕዝቡም ከሰላማዊ ትግሉ ጎን እንዲቆምና ተስፋ እንዳይቆርጥ፣ እንዲሁም ሕዝቡን ማንቃትና ማደራጀት የሚያስፈልግ በመሆኑ ነው ይህን ስብሰባ የጠራነው፤›› በማለት፣ አጠቃላይ የሕዝባዊ ስብሰባው መንፈስ ምን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹ከሕዝቡ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በሰፊውና በሚገባ እንወያያለን፡፡ ከሕዝቡ ጋር እንዲህ ባለ መድረክ የምንገናኘው ከስንት ዓመታት በኋላ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል፤›› በማለት፣ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ለመወያየት መዘጋጀታቸውን አክለዋል፡፡
ፓርቲው አስፈላጊውን ዝግጅትና እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረ መሆኑን ጠቁመው፣ ከረቡዕ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በከተማው የተለያዩ ሥፍራዎች በመኪና በመዘዋወር ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝባዊ ስብሰባውን ባከናወነ በሳምንቱ ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ በማቀድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የዕውቅና ደብዳቤ ማስገባቱን አስታውቋል፡፡
‹‹መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ሥርዓት በሰላማዊ ትግል ለመቀየር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን አጠናክሮ ይንቀሳቀስ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤›› በማለት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman