በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መካከል ለተፈጠረው ግጭት ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጡ ህዝባዊ ጉባኤዎች ሊካሄዱ ነው

በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች ለተነሳው ግጭት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች የሚመሩ ህዝባዊ ጉባዔዎች እንደሚካሄዱ መንግሥት አስታወቀ።
በሁለቱ ክልሎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሪነት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራልና የሁለቱ ክልሎች አመራር አባላትና የፀጥታ አካላት የተካፈሉበት የውይይት መድረክ ትናንት ተካሂዷል።
ውይይቱን የተከታተሉት የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደገለጹት፥ ግጭቱ ያለበትን ደረጃ የሚያመለክት ሪፖርት በውይይት መድረኩ ላይ ቀርቦ ለጉዳዩ ፈጣንና ዘላቂ እልባት ለመስጠት የሚያስችል አቅጣጫም ተቀምጧል።


በዚሁ መሰረት በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች የሚመሩ የሁለቱም ክልሎች ህዝቦች የሚሳተፉባቸው ህዝባዊ ጉባዔዎች እንዲደረጉ አቅጣጫ መቀመጡንም ነው የገለጹት።
የሁለቱም ክልሎች አመራር አባላት ለግጭቱ መንስኤ የሆኑ አካላትን በማጋለጥ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ግጭቱን የሚያባብስና ህዝብን የሚያጋጭ መረጃ በማንኛውም መገናኛ ብዙሃን ሆነ ግለሰብ እንዳይተላለፍ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀው፤ መመሪያውን ተላልፈው ግጭቱን የብሔር ግጭት አስመስለው የሚያናፍሱ የኮምዩኒኬሽን አካላትና መገናኛ ብዙሃን ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አመልክተዋል።
የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የተቀራረቡና በፍቅር የኖሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ "ግጭቱ የህዝቦችንም ሆነ የተገነባውን ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማይወክል መሆኑ" በውይይቱ መነሳቱንም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።
በግጭቶቹ አካባቢዎች ኬላዎች መኖራቸውንና ተሽከርካሪዎች በመቆማቸው የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ችግር መፈጠሩን አስታውሰው፤ ከአሁን በኋላ የየትኛውም ክልል የፍትሕም ሆነ የጸጥታ አካል ኬላ አቁሞ እንዳይፈትሽ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
ይህን ሥራ የመቆጣጠሩ ተግባር የፌደራል የፀጥታ አካላት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተም ጊዜያዊና ዘላቂ አቅጣጫ መቀመጡን ዶክተር ነገሪ ገልጸው፤ ዜጎች በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢዎች ተዘዋውረው የመስራት ህገ መንግስታዊ መብት እንዳላቸውም አስረድተዋል።
በግጭቱ የቆሰሉ አካላት አስፈላጊው ህክምና እንደተደረገላቸውና እንደሚደረግላቸው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የተፈናቀሉ ዜጎች ከመሰረታዊ ፍላጎትና ከጤና ጋር የተያያዙ ድጋፎች በክልሎችና በፌደራል መንግስት እንደሚቀርብላቸው አብራርተዋል።
ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ተፈናቃዮች ወደነበሩበት ስፍራ እንዲመለሱ፣ የተዘረፈ ንብረታቸው እንዲመለስ ካልተመለሰም ካሳ እንዲከፈላቸው እንደሚደረግ አብራርተዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም እና አስፈላጊውን ከለላ የመስጠት ኃላፊነቱም ዜጎች የተፈናቀሉባቸው ክልሎች እንዲሆን ተደርጓል፤ አመራር አባላት አቅጣጫውን በተግባር ለመፈጸም ተስማምተው ቃል ገብተዋል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል የሁለቱ ብሔር ተወላጅ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ለመሄድ ለደህንነታቸው ስጋት እንዳደረባቸው ቅሬታ ማሰማታቸውን ጠቁመዋል።
ነገር ግን የሁለቱ ክልሎች አመራር አባላት ከዩኒቨርሲቲዎቹ አመራር አባላት ጋር በመነጋገርና ተማሪዎችን በቅርበት በማነጋገር "ተማሪዎች እንደማንኛውም ዜጋ ጥበቃ እንደሚደረግላቸውና ለደህንነታቸው ስጋት እንደማይገባቸው ግንዛቤ ሊወሰዱ ይገባል" ብለዋል።
በተማሪዎች ላይ ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር ትምህርት ሚኒስቴር የጀመረው ስራ መኖሩን ጠቁመው ተማሪዎች ያለምንም ስጋት ወደ ትምህርት ገበታቸው መሄድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa