በኢትዮጵያ 16 በመቶው ህዝብ ጫት እንደሚቅም አንድ ጥናት አመላከተ

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሀገሪቱ በሲጋራ፣ አልኮል መጠጦች እና ጫት ሱሶች የተጠመዱ ሰዎች ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በጥናት ማረጋገጡን ገለፀ።
ኢንስቲትዩቱ በ2007 ዓ.ም ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከአዲስ አበባ እና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ባደረገው ጥናት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ ምክንያት እና ስርጭት ተዳሷል።

እድሜያቸው ከ15 እስከ 69 የሚደርሱ 9 ሺህ 801 ሰዎች በተካተቱበት ጥናት፥ የተሳታፊዎቹ የደም ግፊት፣ የልብ ምት፣ ቁመት፣ የሰውነት ክብደት እና ሌሎች የጤና ሁኔታዎች ተቃኝተዋል።
በዚህም ስር ለሰደዱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ ናቸው የተባሉ ባህርያት የተለዩ ሲሆን፥ የመጀመሪያው ሲጋራ ማጨስ መሆኑን በኢንስቲትዩቱ የስርዓተ ጤና እና ስነ ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክተሩ አቶ አበበ በቀለ ይገልፃሉ።
ሌላው በጥናቱ አጋላጭ ባህሪ ነው ተብሎ የተጠቀሰው አልኮል መጠጣት ሲሆን፥ በጥናቱ 41 በመቶው የሀገሪቱ ዜጋ አልኮል እንደሚጠጣ ተረጋገጧል፤ ይሁን እንጂ አሃዙ ከክልል ክልል እንደሚለያይ ነው ዳይሬክተሩ ያነሱት።
በሀገሪቱ 16 በመቶው ህዝብ ጫት እንደሚቅም ጥናቱ ያመላከተ ሲሆን፥ ይህ ሀገራዊ አማካዩ ቢሆንም በሀረር 61 በመቶው ህብረተሰብ ጫት ይቅማል።
በሌላ በኩል በትግራይ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጫት ቃሚዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል ነው ያሉት አቶ አበበ።
በዋናነት የሱስ ተጋላጭ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል መጨመሩን ያሳየው ጥናቱ መንግስት ሊወስዳቸው የሚገቡ የቤት ስራዎችንም በግልፅ አሳይቷል።
በአዲስ አበባ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የአደንዛዥ እፅ እና አልኮል ሱስ ማገገሚያ ማዕከል ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ታካሚዎች ሱስ ሲገቡበት ቀላል ቢሆንም ለመውጣት ግን አዳጋች ነው ብለዋል።
ጭንቀት ወይም ድብርት፣ ሰላም የራቀው እና የልጆቹን መዋያ የማይቆጣጠር ቤተሰብ፣ የጓደኞች ግፊት፣ የአደንዛዥ እፆች እና አልኮል መጠጦች በአቅራቢያ መገኘት እና ገንዘብ ሱስ አምጪ ነገሮችን ለመውሰድ ምክንያት እንደሚሆናቸውም ነው ታካሚዎቹ አስተያየታቸውን የሰጡን።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል የአዕምሮ ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ሰለሞን ተፈራ፥ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአዕምሮ ጤና ቡድን ቢኖርም የተደራጀ አይደለም ይላሉ።
በክልል ጤና ቢሮዎች እና ጤና ጣቢያዎችም ለአዕምሮ እና ሱስ ህክምና የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ከአዕምሮ ጤና ጋር የተያያዙ የጤና እክሎችን ለማከም፣ ለመከላከል እና የተሃድሶ አገልግሎት ለመስጠት ራሱን የቻለ ተቋም ሊኖር እንደሚገባ ነው ያነሱት።
የአደንዛዥ እፅ እና አልኮል ሱስ መከላከል ፐሮግራም ያልተቀረጨ ሲሆን፥ የህክምና ማዕከላት አለመስፋፋት፣ የባለሙያ እና የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትን ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት አስቀምጠዋል።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የዓለም ጤና ድርጀት ድጋፍ ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመው የአደንዛዥ እፅ እና አልኮል ሱስ ማገገሚያ ማዕከል በአልጋ ተኝተው የሚታከሙ እና በርካታ ተመላላሽ ታካሚዎችን እያስተናገደ ነው።
በሆስፒታሉ አቅራቢያ ከሚገኙ የጤና ተቋማት በሃኪም ትዕዛዝ የሚላኩ እና ማንኛውም አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሰዎችን የሚቀበለው ማዕከሉ፥ ከ7 እሰከ 10 ቀናት ውስጥ በመድሃኒት እርዳታ ሰውነትን ከሱስ የማፅዳት ስራ እየሰራ ነው።
በማዕከሉ ምንም እንኳን የግብዓት እጥረት ቢኖርም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸው ዘዴዎችን በመጠቀም ውጤታማ የሱስ ማስወገድ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ነው ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰለሞን የገለፁት።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያካሄደው እና ሌሎች ጥናቶች በሀገሪቱ ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን የሚጠቀሙ ዜጎች መበራከታቸውን ያሳያሉ ብሏል።
ሚኒስቴሩ የአደንዛዥ እፅ እና አልኮል ሱሰኝነት ስርጭትን ለመቆጣጠር ከኢትዮጵያ፣ ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ በ27 ሆስፒታሎች የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትን በተጓዳኝ በማቋቋም የህክምና አገልግሎቱን እንዲሰጡ ስልጠና ሰጥቷል።
ከእነዚህ ሆስፒታሎች ውስጥ በአሁኑ ስዓት አገልግሎተ እየሰጡ ያሉት በአዲስ አበባ 3 በክልሎች ደገሞ 7 ሆስፒታሎች ብቻ መሆኑን በሚኒሰቴሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የአዕምሮ ጤና ባለሙያ አቶ አበባው አየለ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ አዳዲስ ማዕከላትን ለመክፈት እና ነባሮቹን ለማጠናከር የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ባለሙያው፥ የሱስ ማገገሚያ ማዕከላት የሚያስተናግዱትን ታካሚዎች ቁጥር ከፍ ለማድረግ እና የመድሃኒት አቅርቦቱን ለመጨመር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ማዕከላቱን ከማስፋፋት ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት እንደሚሰሩም አቶ አበባው አንስተዋል።
ሀገሪቱ ለሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎቿ ቁጥር በየጊዜው እያደገ ቢመጣም ችግሩን ለመግታት እያከናወናቻቸው ያሉ ተግባራት በቂ አይደሉም።
ከሱስ ለማገገም የሚረዱ የህክምና ተቋማት እና መድሃኒቶች እጥረትም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወታቸውን ካቃወሰባቸው ሱስ ለመውጣት ለሚጥሩ ዜጎች ፈተና መሆኑ ተነግሯል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም የአደንዛዥ እፅ እና አልኮል ሱሰኞች የሚያገግሙባቸው ማዕከላት ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ገልፆ፤ ማዕከላቱን ከማስፋትና እና የመድሃኒት አቅርቦቱን ከመጨመር ባለፈ ለግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሰፊ ትኩረት ሰጥቼ እየሰራሁ ነው ብሏል።

Source:Fana Broadcasting Corporate(FBC)

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman