በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በሰልፍ ምክንያት ተፈጠሮ የነበረው ሁከት በቁጥጥር ስር ዋለ
በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በሰልፍ ምክንያት ተፈጠሮ የነበረው ሁከት በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታወቁ።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ሲደረጉ የነበሩ ሰልፎች ወደ ሁከት እና ብጥብጥ አምርተው በሰዎች ህይወት አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ሃላፊው አስታውሰው።
በአሁኑ ወቅት የየወረዳዎቹ ህዝቦች፣ የክልሉ የፀጥታ አካላት እና የሀገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ርብርብ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ስር ውሎ በአካባቢው መረጋጋት ተፈጥሯል ብለዋል።
በሁከቱ የተሳተፉ እና በሰው ህይወት አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት በማሰድረስ የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በአካባቢው ዘላቂ መረጋጋት እንዲፈጠር ተመሳሳይ ችግሮች በድጋሚ እንዳይከሰቱ ለማድረግ ጠንክሮ በመስራት እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የሁከቱን ተከትሎ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመፍራት ወደ 1 ሺህ 500 የሚጠጉ ዜጎች በጮራ፣ ዴጋ እና በደሌ ከተሞች ተጠልለው እንደሚገኙም ገልፀዋል።
ህዝቡም ለእነዚህ ዜጎቻችን ምግብ፣ ውሃ እና አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ አዲሱ፥ በአሁኑ ወቅት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጸጥታ አካላት እና የመንግስት አመራሮች ከህዝቡ ጋር በመረባረብ ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
አቶ አዲሱ አረጋ በትናንትው እለት እንደተናገሩት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፥ ፀረ ሰላም ሀይሎች ሰሞኑን በሁለቱ ወረዳዎች ሲደረግ የነበረዉ ሰልፍ ወደ ሁከት እና ብጥብጥ እንዲያመራ በማድርግ በሰዎች ህይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል።
በጮራ እና በዴጋ ወረዳዎች በኦሮሞ እና በአማራ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ባቀናበሩት ሴራ 14 ሰዎች ህይወታችውን ማጣታቸውን ነው ሀላፊው የተናገሩት።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ