በአዲስ አበባ ከተማ እና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ወሰን ማካለል ላይ ውይይት ተካሄደ
በአዲስ አበባ ከተማ እና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለልን በተመለከተ በሁለቱ ወገኖች የተደረሰ ስምምነት ላይ የሕዝብ ውይይት ተካሄደ።
ውይይቱ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የተካሄደው።
ከአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተውጣጡ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የነዋሪዎች ተወካዮች በመድረኩ መሳተፋቸውን በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት በትጋትና በቁርጠኝነት፣ ከሕዝባችን ጋር ስንሠራበትና ስንመክርበት ቆይተን በስኬት አጠናቀናል ብለዋል፡፡
በጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሠራበት የቆየውና ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሲመከርበት የቆየው የአስተዳደራዊ ወሰን ጉዳይ÷ በሕገ መንግስትና በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሰረት የወሰን ጉዳይ በሁለቱ አስተዳደር አካላት ይፈታሉ ብሎ በሚያስቀምጠው መሰረት ስምምነት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት፡፡
በዚህ ታሪካዊ ውሳኔ የኦሮሚያ ክልል በሚያስተዳድርበት፣ አዲስ አበባም ስታስተዳድርበት በነበረው ቦታ እንድትቀጥል የተስማማን ሲሆን÷ በኦሮሚያ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ውስጥ በመግባት በርቀት በአዲስ አበባ የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞች ለአብነትም ኮየፈጨ፣ ቱሉዲምቱ በከፊልና ጀሞ ቁጥር ሁለት የሚገኙበትን ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲካለሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የገነባውን የቆጣሪ ኮንዶሚኒየም ወይም ለቡ አካባቢ ከፉሪ ሃናና የኦሮሚያ ኮንዶሚኒየሞች ጨምሮ እስከ ቀርሳ ወንዝ ያለውን ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲካለሉ ስምምነት ላይ መደረሱን ነው ያስረዱት።
ከዚያ ውጪ ሁሉም ባለበት ቦታ እንዲያስተዳድር ታሪካዊ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመው፥ ውሳኔው ከግብ እንዲደርስ የሁሉም አስተዋፅዖ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ይህ የአስተዳደር ወሰን በሚነካባቸው አካባቢዎች፥በአካባቢዎቹ የትኛውም አይነት መንግስታዊ አገልግሎት እንደማይቋረጥ፣ የአገልግሎትና የፀጥታ ሥራዎች በሁለቱም ወገን በጋራ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሠራ፣ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች እንደማይቆሙ እና ይልቁንም በፍጥነት የሚጠናቀቁበት ሁኔታ ልዩ ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
እንዲሁም የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱና የተማሪዎች የቋንቋ ጉዳይ በነበረበት እንደሚቀጥል እና የሚሰጡ መንግስታዊ አገልግሎቶች ላይ ቋንቋ ምንም አይነት ተፅእኖ እንዳያሳርፍ እንደሚደረግም ነው የገለጹት፡፡
የውይይቱ ዋና ዓላማ፥ የተደረሰው ስምምነት የሕዝቦችን አንድነትና አብሮ ማደግን በሚያጠናክርና ዘለቂ መፍትሔ በሚሰጥ መልኩ እንዲተገበር ለማድረግ መሆኑ ተመልክቷል።
በሕዝባዊ መድረኩ ጥናትን መሰረት አድርጎ ስምምነት የተደረሰበት የአስተዳደራዊ ወሰኑ አከላለል ለተሳታፊዎች ቀርቧል።
ጥናቱንና የጥናቱን መነሻ አድርጎ የተደረሰው ውሳኔ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ የወደፊት የአተገባበር አቅጣጫም ተቀምጧል።
በአዲስ አበባ እና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን የማካለል ስራ መዘግየቱ ነዋሪው ማግኘት የሚገባውን አስተዳደራዊ አገልግሎት አሳጥቶ ቆይቷል።
ይህም በመሆኑ ቅሬታ የተሰማቸው ነዋሪዎች መንግስት የአስተዳደር ወሰኑን በፍጥነት እንዲያካልል ሲጠይቁ ነበር።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ