ወልቃይት፤ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት!




ወልቃይትና አካባቢውን ላወቀ ሰው፣ ቀጠናው የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት በመወሰን በኩል ምን ያክል አስተዋፅዖ እንዳለው ይገነዘባል። የአካባቢውን ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ በውል ያልተረዱ ወገኖች ደግሞ የወልቃይትና አካባቢውን ጉዳይ ተራ የመሬት ጉዳይ አድርገው ይመለከቱታል። አንዳንድ መሰሪዎች ደግሞ ከራሳቸው ዓላማ ተነስተው፤ የወልቃይትን አገራዊ ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ እንዳይገነዘበው ሆነ ብለው አቃልለው ያቀርቡታል፣ ሁነቱን ከአገራዊ አጀንዳነት አውርደው በአንድ አካባቢያዊ ጉዳይ ሊያጥሩት ይሞክራሉ። እነዚህ የትንሽነት ኃሎች አጀንዳው ከፍ ሲል የአማራ ዝቅ ሲል ደግሞ የጎንደር_በጌምድር እንደሆነ አድርገው በማቅረብ ኢትዮጵያዊያንና አለምን ለማሳሳት ሞክረዋል፤ ገናም ይሞክራሉ።
እውነታው ግን ወዲህ ነው። የወልቃይት ጉዳይ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ውስብስብ ፖለቲካ መናኸሪያ በመሆኑ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ህልውና በእጅጉ የሚፈትን ወሳኝ ብሔራዊ አጀንዳ ነው፡፡ ለዚህም ነው ደግመን ደጋግመን ‹የወልቃይት ጉዳይ ሁለመናውን ለኢትዮጵያ አሳልፎ የሰጠ ኃይል እስካልተቆጣጠረው ድረስ፣ ወልቃይት ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት መሰረት መሆኑ ቀርቶ ለኢትዮጵያ የተራዘመ መከራና አገራዊ መበተንም ምክንያት ሊሆን ይችላል› የምንለው።
ከልምዴ እንደተማርኩት ወያኔ ወልቃይትና አርማጭሆን ባይቆጣጠር ኖሮ ደርግን ለመጣል አይችልም ነበር፤ ካልሆነም ደርግ ሕዝባዊ ማዕበል ተነስቶበት እስኪገፋ ድረስ ወያኔ በደደቢት በረሃ ተወስኖ ለተራዘሙ አመታት መክረሙ የሚቀር አልነበረም። የመሀል አገር ጉዞውም እጅግ በተራዘመ ነበር። የወያኔን ድል ያፈጠነው በዋነኛነት ወልቃይትና አርማጭሆን በመቆጣጠሩ እንደነበር ቅንጣት ታክል መጠራጠር አይገባም።
ለዚህ ጥ ሩ ማሳያው አርማጭሆ ውስጥ "የወያኔ መንገድ" የሚባል አለ። ይህ የመኪና መንገድ ከሱዳን ተነስቶ የአርማጭሆን በረሀ አቆርጦ ወዲኑር፤ ቢፈኝ የተሰኙ ቀበሌዎችን አልፎ፤አንገረብ ወንዝን ተሻግሮ የግጨው በረሀን ሰንጥቆ አለፎ ወልቃይት ቤዙን ላደረገው ወያኔ ጦር የደምስር ሁኖ ያገለገለ መንገድ ነው።
ወያኔ ይሄን በር ተጠቅሞ ነበር ከሱዳን የፈለገውን ነገር እያስገባ አቅሙን ገንብቶ ደርግን የፈተነውና መጨረሻውንም እንዳያምር ያደረገው። ልብ በሉ ወያኔ ይሄን የሚያደርገው ደርግ ከነሙሉ አቅሙ በነበረበት ከ1980ዎቹ መግቢያ በፊት ጀምሮ ነበር። ያኔ በሁመራ በኩል ከሱዳን አይገናኝም ነበር። ዋነኛ የደምስሩ ከላይ ያነሳሁላችሁ በሰው ጉልበት የተሰራውና አርማጭሆን ሰንጥቆ ሱዳን የሚደርሰው መንገድ ነው።
ስለዚህ ዛሬ ላይ በሆነ አጋጣሚ የወልቃይት መሬት በወያኔ እጅ ወደቀ ማለት ለኢትዮጵያ ትርጉሙ ትልቅ ነው።
በእኔ እምነት ወያኔ ወልቃይትን በሁለት መንገዶች (በጦርነትና ድርድር) በጁ ማስገባት ከቻለ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማጣት ብቻ ሳይሆን ትፈርሳለች። ይህ ሟርት አይደለም። ትንሽ ልጨምርበት።
ተከተሉኝ፡፡
1ኛ) ወያኔ በጦርነት አሸንፎ ወልቃይትን ቢቆጣጠርና የሁመራን ኮሪደር ቢቆጣጠር ምን እንደሚፈጠር አስቡ። ጥቃቱ ወደ አስመራም የሚሻገር ከመሆኑም በላይ በዚህ ቀውስ የዓባይ ውሃ ታሪካዊ ብቸኛ የጥቅም መብት አለኝ የምትለው ግብጽ ወልቃይት ላይ የጦር ሰፈር እንድታገኝ በወያኔ ዕድሉ ሊመቻችላት ይችላል (በዚህ ዙሪያ ከዓባይ ፖለቲካ ጋር ተያይዞ ግብጾች ቀጠናው እንዳይረጋጋ በውስብስብ ፖለቲካ ሲታመስ እንዲኖር በሰፊው እየሰሩ ስለመሆኑ በቀጣይ እመለስበታለሁ፡፡ ለጊዜው ግን ወልቃይትን የጦር ሜዳ በማድረግ የኢትዮጵያ 70 በመቶ የውሃ ምንጭ የሆነውን ምዕራብ ኢትዮጵያን የማተራመስ ብርቱ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ወያኔ ወልቃይትን ቢቆጣጠር ራስ-ገዝም ሆነ የትግራይ ሪፐብሊክ ከማወጁ በፊት ግብጽ ወልቃይት ላይ የጦር ሰፈር እንዲኖራት የማድረግ ፍላጎት አለው)፡፡
የሆነው ሆኖ፣ ዛሬ ላይ ወያኔ ወልቃይትን የመቆጣጣር ዕድል ቢቀናው የሚጠብቀው የያኔው የድሮው የአርማጭሆ የበረሀ መንገድ ሳይሆን የተንጣለለው የሉግዲ_ሱዳን አስፓልት ነው፡፡ አካባቢው በሰፊው በመንገድ ልማት የተሳሰረ መሆኑ ዕድልም ፈተናም ነው፡፡ የዚህ መንገድ መኖር ወያኔ የፈለገውን ለመስራት ዕድል ይሰጠዋል። እዛው እንዳለ የውጭ ወዳጆቹ ድጋፍ ይጎርፍለታል። በዚህም ታአምራዊ አቅም ይገነባል። የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ጎትቶ በማምጣት ለሀገረ-መንግሥቱ ከባድ ፈተና ይደቅናል። በዚህ የአማራ ሕዝብ ግንባር ቀደሙ የወላፈኑ ተጋላጭ ይሆናል። በዚህ መልኩ አገሪቱ በጦርነት ውስጥ ሆና ትቀጥላለች።
ይህ ጦርነት ግን ለወያኔ እንደደርጉ ዘመን አጭር አይሆንለትም። ምክንያቱም ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል። በተለይም አማራ ነገሩ ሁሉ ተቀይሯል። ምሬቱም አድጓል፡፡ እንኳንስ ለወያኔ ለቀጠናውም አደጋ ጣይ ኃይል ከአማራ ይነሳል፡፡ በመሆኑም ወያኔ በዚህ ወልቃይትን የመቆጣጠር ዕድል ቢኖረው አገራችን ለተራዛሚና ደም አፋሳሽ ጦርነት ትጋለጣለች። አማራም የዚህ ተራዛሚና ደም አፋሳሽ ጦርነት ዋነኛና ግንባር ቀደም ተጠቂ፣ ተጋፋጭ፣ ሆኖ ይቀጥላል። በቀጠናው በግብጽ የሚመሩ የመካከለኛው ምስራቅ አረብ አገራት ተጽዕኖ የሰፋ የሚሆን በመሆኑ የአማራንም የኢትዮጵያንም ፈተና ያከብደዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ወልቃይት በወያኔ እጅ ዳግም ከወደቀ ሲሆን፤ ወልቃይትና አርማጭሆን በአሁናዊ ሁኔታቸው ኃላፊነት በሚሰማው አካል እጅ ከቀጠሉ ኢትዮጵያ ከሰሜን ምስራቅ አፍሪካ የሚነሳባትን ቀጠናዊ ስጋትና የዓባይ ፖለቲካ መዘዞችን መቋቋም ትችላለች፡፡
2ኛ) በሌላ በኩል ወያኔ በተጀመረው ድርድር መሰረት በለስ ቀንቶት ወልቃይት ጠገዴን አገኘ የሚለውን ምኞት ደግሞ እንመልከት። በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ ቢከሰት ሁለት ውጤቶችን ያስከትላል።
ሀ. ወያኔ ብዙም ሳይቆይ ወልቃይትን እስካገኘ ድረስ ነፃ የትግራይ መንግሥትን ያውጃል። ሰዎች ሞኝ እንዳትሆኑ ወያኔ ወልቃይትን ካገኘ ጠንካራ የትግራይ መንግሥትን ይፈጥራል። በተለይም የኢትዮጵያን መፍረስ የሚሹ አገራት ጉልበተኛ የትግራይ መንግሥት እንዲፈጠር ሙሉ ድጋፍ ያደርጋሉ። የወዳጅነት ትኩረቱ ካርቱምና ካይሮ እንጅ አዲስ አበባን ዘላቂ ጠላቱ አድርጎ መመልከቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ በኩል ብዥታ ሊኖር አይገባም። ጥያቄው በዚህ መልኩ የምትፈጠር ‹‹ነፃ ሀገረ-ትግራይ›› ለኢትዮጵያ በተለይም ለአማራ ምን ይዛ ትመጣለች? የሚለው ነው። ለኤርትራስ?
ለ. ወያኔ ድርድሩ ቀንቶት ወልቃይትን አገኘ ቢባል ሌላው መታየት ያለበት ‹ትግራይና አማራ እንዴት ይቀጥላሉ?› የሚለው ነው። በተደጋጋሚ እንደምለው የወልቃይት ሕዝብና መሬት በጦርነትም ይሁን በድርድር ስም ዳግም በወያኔ እጅ ከገባ፣ ምክንያቱ የአመራር ድክመት እንጅ ሌላ አይሆንም። ምክንያቱም ወልቃይት ህዝቡም ሆነ መሬቱ በታሪክም ሆነ በህግ እንዲሁም በሥነልቦናው አማራ ነው። ወልቃይትን ከበጌምድር ታሪክ ለይቶ ማየት የሚቻል አይደለም፡፡ በጌምድር ደግሞ የአማራ መንበር ነው፡፡
ታሪክ ማጣቀስ ካለብን እነሆ፡- የጥንታዊት ኢትዮጵያ ነገዶች ታሪክ ፀሐፊ አለቃ ታዬ ወልደማርያም “የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፡ ባጭር ቃል የወጣ” በሚል ርዕስ በ 1919 ባሳተሙት መፅሐፍ ውስጥ፡- ‹‹ከለው ከሳባ ወደ ምዕራብ ወደ ደቡብ ያለ የአማራ የወልቃይት-ጠገዴ አባት ነው።›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ በረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአማራ ነገድ እያደገና እየሰፋ ስለመምጣቱ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ወልቃይት-ጠገዴ የከለው ልጅ፤ የአማራ የዘር ግንድ መነሻ ነው ስንል የታሪክ ማስረጃ ይዘን ነው፡፡ ወልቃይት-ጠገዴ፤ የአማራ ሕዝብ ዕትብት የተቀበረበት ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች የዛሬና የነገ የጋራ ህልውና ታሪካቸው፣ የአገራዊ ጀብዱ እና የሉዓላዊነት ኩራት መነሻ አስኳላቸው ነች-ወልቃይት፡፡ የዓባይ ፖለቲካ ቋጠሮ የሚፈታው፣ የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የሚከበረው ወልቃይት ኃላፊነት በሚሰማው አካል ስር ሆኖ ሲቀጥል ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም ይህ እውነታ የሚነግረን ወልቃይት በጦርነትም ሆነ በድርድር ዳግም በወያኔ እጅ ወድቋል ቢባል አርፎ የሚቀመጥ ሕዝብ የለም ማለት ነዉ፡፡ ይሄም ማለት የአማራ ሕዝብ ያላግባብ ያጣውን እውነት መልሶ ለማግኘት ሲል ፍትህን ፍለጋ ብረት ማንሳቱ አይቀሬ ነው። የዚህ ውጤት ደግሞ ከባድ ነው፡፡ በትርምስ ውስጥ ለኖረው የአፍሪካ ቀንድ በጎ ዜና አይሆንም፡፡ በትንሹ የወልቃይት ጉዳይ ቢያንስ የአማራና የትግራይን ህዝቦች የትውልድ ጦርነት ውስጥ ይዘፍቃቸዋል፡፡ ከአማራ ሱዳን ይቀርበናል ሲል የኖረው ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ የክፍለ ዘመን መከራ አስታቅፎት ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ሀገረ-ኤርትራን ስለሚኖራት ዉሳኔና ሚና ነ አትርሱ፡፡
መውጫ!
ከፖለቲካ ልምድ ተሞክሮየ በላይ፣ የሕዝብ አስተዳደር ተማሪ ነኝ። ሰለሆነም ስለመንግሥት ምንነት፣ አሰራርና ፍላጎት ወዘተ... ግንዛቤውን አላጣውም። በዚህም መሰረት በዓለም ላይ በሕዝብ እንዲጠላና የያዘውን ሥልጣን በሌሎች በጉልበት እንዲነጠቅ የሚፈልግ መንግሥት አልታየም ለወደፊቱም አይጠበቅም። እነ ሂትለርም ያን ሁሉ በደል የሰሩት በሕዝብ ዘንድ የበለጠ የሚወደዱና በሥልጣን ለመሰንበት ከነበራቸው የተሳሳተ ስሌት ተነስተው ነው። እንጅማ እንዲህ ዓለም እንደሚጠላቸውና ሥልጣናቸውንም እንደሚያሳጣቸው፣ ሲከፋም ሕይወታቸውን እንደሚያሳጣቸው ቢያውቁ ኖሮ ያንን የዕብደት ውሳኔ ወሰነው፣ አገራቸውን አሰወድመው እነሱም ከአለም ባልተሰናበቱ ነበር።
ይሄን ነገር ወደ አገሬ ኢትዮጵያ ልመልሰው። መቼም ቢሆን ጠ/ር ዐቢይ አህመድን በአንዳንድ ጉዳዮች ሂስና ትችት ያረብኩባቸው ቢሆንም አገራቸውን ይጠላሉ፤ በሕዝብ ድምፅ ካገኙት ወንበር በጉልበተኛ ተገፍትሮ ለመውደቅ ይወስናሉ ብየ አልገምትም፡፡ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች አይደራደሩም የሚል ተስፋ አለኝ። ይሄም ማለት እነዚህን ሁለት ነገሮች አደጋ ላይ ለሚጥሉ ማናቸውም ጉዳዮች አይደራደሩም (ውጤቱን መገመት አይጠፋቸውምና)። በመሆኑም ጠ/ር ዐቢይ ወልቃይትን በተለይም በኃይል ወልቃይት ወያኔ እጅ እንዲወድቅ በማድረግ፤ አገራቸው እንድትፈርስ ወይም በተራዘመ ጦርነት ውስጥ እንድትኖር፤ ከፍ ሲልም እንደ መንግሥቱ ኃይለማርያም በሴራ ከወንበራቸው እንዲለቁ ይፈቅዳሉ ብየ አላስብም።
ሰለሆነም ጠ/ር ዐቢይ ለአገራቸው፣ ለመንግሥታቸውና ለራሳቸው ክብር ሲሉ ወልቃይትን ቢያንስ በኃይል ለመውሰድ ለሚከጅል በራቸው ዝግ እንደሚሆን አልጠራጠርም። ከዚህም በተጨማሪ የወልቃይትን ጉዳይ ስለሚያውቁት ጉዳዩ በሕግና ፖለቲካ አግባብ ታይቶ የወልቃይት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ መንግሥታዊና ሕጋዊ ድጋፋቸውን እንደሚያረጋግጡ እንጠብቃለን። ሀገር እንዲኖረን ስለምንፈልግ ‹Benefit of the doubt› አለን፡፡ ምክንያቱም ለታሪክና ለልጆቻቸው ሲሉ ግን ቢያንስ እውነቱን እንደሚናገሩ መረጃውም አለንና፡፡ (በዚህ በኩል ከምዕራባውያን እስከ ውስጠ-ፓርቲ ያለባቸውን ጫናና ሴራ ብናውቅም) ይህ ማለት ግን እርሳቸዉም ሰዉ ናቸዉና ስለነገ አቋማቸው 100% እርግጠኛ ነን ማለት አይደለም፡፡ እንደመሪ በኃላፊነት ስሜት ጉዳዩን እስከመጨረሻው እንዲመሩት ግን መልካም ምኞት አለኝ፡፡
ከአማራ ክልል መንግስት አንፃር ደግሞ ማለት የምፈልገው፡- ወልቃይት በጉልበትም ሆነ በይስሙላ ‹‹ድርድር›› ሥም ዳግም በወያኔ እጅ ከወደቀ፣ መለኮታዊ ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር፣ አማራ እና ትግሬ ወደተራዘመ የትውልድ ጦርነት የማምራት ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ፤ የትውልዶች ጦርነት ሊኖር እንደሚችል አሰቦ በሁኔታዎች ልክ መሰራት ይመከራል። ሟርት አይደለም።
በተለይም ሁሉም የአማራ ወጣት ትምህርቱን እንደጨረሰ ወደቤቱ ሳይገባ ወደወታደራዊ ስልጠናዎች የሚገባበት ፕሮግራም ከወዲሁ መታሰብ አለበት። በነገራችን ላይ አማራ ከቀሪው ዓለም ጋር የሚገናኝበት መስመር ከሁመራ እስከ ቋራ ባለው መስመር ነው፡፡ ይህንንም ልብ ማለት ይገባል፡፡ የአማራ ሕዝብ የእስራኤልንና ኤርትራን ሞዴል ከራሱ አንፃር አይቶና አዳፕት አድርጎ መገኘት ጊዜው የሚጠይቀው ሆኖ ይሰማኛል። አማራ ይሄን ማድረግ ከቻለ አይደለም ራሱን ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን መደገፍ ይችላል። በወንድድማማችነት ስሜት ሀገረ-መንግሥቱን ማጽናት ይችላል፡፡ በአንፃሩ አማራ ይሄን ማድረግ ካልቻለ ግን...
በመጨረሻም የአማራ ክልል መንግስት እንደአጠቃላይ በተለይም ደግሞ የሰ/ምዕራብ ጎንደር አመራር የወልቃይት-ጠገዴ- ጠለምት እና እራያ ጉዳይ በማናቸዉም መንገድ ሴኪዩርድ ማድረግ የቀዳሚ -ቀዳሚ አጀንዳዉ መሆን አለበት። በተለይም ደግሞ በወያኔ የተራዘመ ወረራ ከቀያቸዉ በገፍ የተፈናቀሉትን ከ500,000 በላይ ወልቃይቴዎች ወደ ትዉልድ ቦታቸዉ እንዲመለሱ ከልብ መስራት። ይሄን አለማድረግና ሰበብ በመፍጠር የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መከራ ማራዘም ያልተጠበቀ ህዝባዊ ቁጣ ሊወልድ ይችላል።
እየተደማመጥን !

በቹቹ አለባቸው

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa