ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ
የድርጅታችን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ ላለፉት 17 ቀናት አገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ሰፊና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ አካሂዷል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ስብሰባ ቀደም ሲል የተጀመረው የመታደስ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም በአገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዘር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን ፈጥሯል፡፡ ችግሮቹን በመቅረፍ በእስካሁን ትግላችን የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ቁርጠኝነትና ጠንካራ መግባባትን አረጋግጦ ወጥቷል፡፡ የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች ድርጅታችን ኢህአዴግ አገራችንን በለውጥ ጎዳና መምራት ከጀመረበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የህይወት መስኮች መሰረታዊና ተስፋ ሰጭ ለውጥ ሲመዘገብ የቆየ ቢሆንም፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ለውጡን በተጀመረው ስፋትና ግለት ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት የሚፈታተኑ ችግሮች እየታዩ መምጣታቸውን ይገነዘባል፡፡ አገራችን በአንድ በኩል በተከተልነው መሰረታዊና ትክክለኛ አቅጣጫ በተገኙ መልካም ውጤቶች እጅግ የሚያስጎመዥ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፈፀምናቸው ስህተቶችና ከእድገታችን ጋር ተያይዘው በተከሰቱ አዳዲስ ለውጦችና ፍላጎቶች ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን በአሳሳቢ ወቅታዊ ችግሮች ተወጥራ የቆየችበት ሁኔታ መፈጠሩን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በትኩረት ገምግሟል፡፡ ለሁሉም የአገራችን ህዝቦች ግልፅ እንደሚሆነው ለበርካታ ዘመናት በማሽቆልቆል ሂደት ውስጥ ለማለፍ የተገደደችው አገራችን ለ25 አመታት ቀና ብላ ስትጓዝ ቆይታለች፡፡ ይህም በሁሉም አገር ወዳድ ዜጎች የሚታመንበት...