የፓርላማ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እየጠበቁ ነው

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አገሪቱን ሥጋት ላይ በጣላት ብሔር ተኮር ግጭትና የፖለቲካ ቀውስ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማብራሪያ እንዲሰጧቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የምክር ቤቱ አባላት ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ እስኪገኙ ድረስ መደበኛ ስብሰባዎችን ማካሄድ ተገቢ አይደለም የሚል አቋም ይዘዋል፡፡
በርካታ መሆናቸው የተገለጸው የምክር ቤት አባላት ረቡዕ ታኅሳስ 4 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በየተወከሉባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት ማካሄዳቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የኦሕዴድና የብአዴን አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ተገኝተው ወቅታዊ ግጭቶችንና የፖለቲካ ቀውሱን አስመልክቶ እንዲያብራሩ፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎችም ዝርዝር ምላሽ እንዲሰጡ አቋም ይዘው ጥያቄ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አባላቱ ላቀረቡት ጥያቄ ከምክትል አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ምላሽ እየተጠበቀ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ሐሙስና ማክሰኞ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት የፓርላማው መደበኛ ስብሰባ አለመካሄዱ ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በፕሮግራማቸው መሠረት ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡
በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት የምክር ቤቱ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በወር አንድ ጊዜ ጠርተው ትኩረት ባደረጉበት የሥራ አፈጻጸማቸው ላይ ማብራሪያ መጠየቅ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓመት ሁለት ጊዜ ዝርዝር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለምክር ቤቱ እንዲያቀርቡ ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡
ከወር በፊት የምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ተገኝተው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀስቅሶ ስለነበረው ግጭትና የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም ከመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ስላቀረቡ ከፍተኛ አመራሮች መነሻ ምክንያት ማብራሪያ መጠየቃቸውና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት፣ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa