መንግስት በደምቢ ዶሎ በታገቱ ተማሪዎች ዙሪያ የደረሰበትን መረጃ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገለጸ
Finfinnee Caamsaa 18/2012(TW) ታግተው የነበሩ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ በቅረቡ ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች መታገታቸው ይታወሳል።
እነዚህን ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ የሚገመግም በፌዴራል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከአሃዱ ቲቬ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልነው ነው ያሉት ሃላፊው፤ ጉዳዩን አስመልክቶ ለህብረተሰቡ መረጃውን ደረጃ በደረጃ መስጠት በሚገባ መልኩ ለመስጠት ቃል ብንገባም ሁኔታው ውስብስብ በመሆኑ ጊዜ ሊወስድ ችሏል ብለዋል።
ጉዳዩ ውስብስብ ከመሆኑም በላይ በጉዳዩ ዘንድ ቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት በመሆኑ ጊዜ ሊወስድ ችሏል ብለዋል አቶ ንግሱ። ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው 28 ሰዎች መያዛቸውንም በመግለጽ።
ለዚህም በማህበራዊ ድረ ገጽ የተሳሳተና ያልሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ እየደረሰው ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ “ታግቼ ነበር ተማሪ ነበርኩ ”ብለው በተለያየ መልኩ የቀረቡ ወደ 4 ያህል ተማሪዎች እንደተያዙ ጠቁመዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ለማድበስበስ የሞከሩም ተይዘዋል ብለዋል።
በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቋቋመው ግብረ ሃይል ስራውን ሌት ተቀን እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ዝርዝርና የተሟላ መረጃውን በቅርቡ ለህዝቡ ይፋ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ንጉሱ በማከልም “እገታው እንዲከሰት ያቀዱ፣ ያቀነባበሩ መረጃ የሰጡና ያሰማሩ የተለያዩ ወገኖች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገላቸው ነው” ብለዋል።
አሁንም ቢሆን ጉዳዩን በማድበስበስ ሌላ መልክ እንዲይዝ በማድረግ በሰፊው እየሰሩ ያሉ ሰዎችና ግለሰቦችም አሉ ብለዋል። ጉዳዩን በመደበኛ መረጃ ለመስጠት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ ሲጠናቀቅ ዝርዝሩ ለህብረተሰቡ ይሰጣል ብለዋል።
የፌዴራል ግብረ ሃይል፣ ከፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ 24ኛ ክፍለ ጦርና ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር በመሆን ቀደም ብለው በህዳር 25 ተይዘው የነበሩ የአካባቢው ወጣቶች፣ አንዳንድ አመራሮችና እነዚሁ 21 ተማሪዎች ተለቀው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና የከተማዋ ከንቲባ ባሉበት ወደ ዩኒቨርሲቲው መልሰው ከዚያ በኋላ ሌሎች ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተማሪዎች ወጥተው የነበረ መሆኑን እንደነበር በሰነድም በቦታው ተገኝተን አረጋግጠናል ብለዋል።
በጥቀሉ ሁኔታው የብዙ አካላት ዕጅ ያለበት መሆኑ፣ እጅግ ውስብስብ እንዲሁም በጉዳዩ የሚካሄደው ፍተሻ እንዳይሳካ እግር በእግር በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራበት ቢሆንም አስፈላጊውን መረጃ እየተሰበሰበ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በየጊዜው የሚመጡ መረጃዎች ልጆች ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚያሳይ አንዳችም መረጃ የለም ብለዋል አቶ ንጉሱ።
መንግስት መስራት ያለበትን ስራ እየሰራ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ መረጃዎች ተሰብስቦ ሲጠናቀቅ ለህዝቡ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል።
Source:ENA
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ