የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ

የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ።
የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "በትምህርት ተቋማት የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ግንባታና ዴሞክራሲያዊነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች" በሚል ርዕስ የተካሄደ ጥናት ዛሬ ውይይት ተደርጎበታል።

የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ባካሄደው ጥናት ግኝት መሰረት፥ ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት በአመራር ድክመት የሚጠበቅውን ውጤት አላስገኘም ተብሏል።
የትምህርት ዘርፉ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መምራት አለመቻሉን ያመላከተው ጥናቱ፥ የመማሪያ መፅሐፉ ይዘት የተደጋገመ መሆን፣ አቀራረቡ ከዓላማው ጋር መቃረኑ እና የትምህርቱ መርሀ ግብር የሚመራበት በቂ አደረጃጀትና አሰራር አለመኖርን በቁልፍ ችግርነት አንስቷል።
የተማሪዎችን ስነ ምግባር ለመከታተል የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት እስካሁን አለመዘርጋቱንም ጥናቱ ይፋ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም የስነ ምግባር ትምህርትን ጉዳይ የመምህራን ኃላፊነት ብቻ አድርጎ መቁጠር፣ በመምህራን፣ በተማሪዎችና ወላጆች መካከል ያለው ግንኙነት የላላ መሆኑም ተገልጿል።
የስነ ዜጋና ስነ ምግባር አስተማሪዎች የብቃትና የአቀጣጠር ችግር መኖሩ በጥናቱ የተጠቆመ ሲሆን፥ ትምህርቱን ለሚሰጡ መምህራን ከፍተኛ ትኩረት መስጠትና ማብቃት እንደሚያስፈልግም ነው የተመለከተው።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሀዬ፥ ለትምህርቱ ለውጥ አለማምጣት የአመራሩ ድክመት ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ በረከት ስምዖንም ችግሩ የአመራር መሆኑን ጠቅሰው፥ የማስተካከል ፈጣን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣም ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው፥ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ስርዓተ ትምህርትን በማሻሻል በሚቀጥለው ዓመት ወደ ተግባር እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በጥናቱ ውይይት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፥ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት በአመራር ድክመት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም የሚለው የጥናቱ ውጤት ተቀባይነት እንዳለው አንስተዋል።
ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የተቀናጀ ስራ ባለመሰራቱ የሚፈለገው ውጤት ያለመምጣቱንም ነው ያነሱት።
በጥናቱ የቀረበው ችግር በስነ ዜጋና ስነ ምግባር የታየ ችግር ብቻ ሳይሆን በትምህርት ጥራት ላይም ችግር እየፈጠረ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ጥናቱ የሸፈናቸው አካባቢዎች የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ሶማሌ ክልል እና አዲስ አበባ አስተዳደር ናቸው።
የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት ባካሄደው እንቅስቃሴ በተለያዩ ዘርፎች ወደ 14 የሚጠጉ ጥናቶችን አካሂዷል።

 ምንጭ፦ ኢዜአ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman