“ቆንጥርነት”

 

ከብርሃኑ ተሰማ

‘’ከአጋም የተጠጋ ቁልቋልነትን ለመቀየር፣ ቁልቋልም እንዳያለቅስ፣ አጋምም እንዳይወጋ ቆንጥርነት ብቸኛ መንገድ ነው።’’ የሚለን ዘሪሁን አበበ የተባለ ወጣት ዲፕሎማት በትዊተር ገጹ ሰሞኑን ባሰፈረው መልዕክት ነው። አጋም እሾህማ ነው።ቁልቋል ደግሞ ስስ በመሆኑ በቀላሉ ይደማል።ስለዚህ አጋምን ታክኮ የሚያድግ ቁልቋል ሲደማ ይኖራል።

አጋም ትንሽ ፍሬው በሙሉ ጥቁር፣ የበሠለና ጣፋጭ ሲሆን ሊበላ ይችላል። ያልበሠለ (አረንጓዴው) ፍሬ፣ ወይም የተክሉ ፈሳሾች፣መርዛማ ናቸው ይላል ውክፔዲያ ነጻው መዝገበ ቃላት ትርጉሙን አስቀምጦታል። ቆንጥር ወይም ቀንጠፋ (Pterolobium stellatum) ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ተክል ነው።ተክሉ ለቁጥቋጦ-አጥር ይስማማል። ቡቃያዎቹም ለከብት መኖ ይሰበሰባሉ።’’በማለት ጥቅሙን ያስረዳል።

ቆንጥር እሾህማ ነው። ቆንጥጦ ይይዛል።ቆንጥር አጥር ከሆነ ደግሞ በዚያ በኩል ማለፍ አይቻልም።ማለፍም የግድ ከሆነብን በሾሁ እንዳንወጋና እንዳንያዝ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ስለዚህ ነው ዘሪሁን ኢትዮጵያውያን ቆንጥር እንድንሆን የፈለገው። ቆንጥር የምንሆነውን ለማንና ለምንድነው የሚለው ግን ወሳኝነት አለው።

እንዳይቆነጣጠር

መተማመን የሚቆረቁረው፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማራመድ የሚቸገር፣ ቅንነትና በጎ አሳቢነትን እንደ ድክመት ቆጥሮ በላይህ ላይ ለመረማመድ ለሚሞክር ኃይል ቆንጥር መሆን የግድ ይላል።

በገዛ አገርህ ለመንቀሳቀስ እንቅፋት የሚፈጥርብህን ኃይል ቆንጥር ሆኖ መውጋት ይገባሃል። መውጫና መግቢያ አሳጥቶህ ወደ ውስጥም እንዳይገባ፤ ከገባም እንዳይወጣ ለማድረግ ቆንጥር ከመሆን ውጭ አማራጭ የለም። ተከብረህ ሌሎችንም ለማክበር ቆንጥር መሆን መልካም ዘዴ ነው። ሄደህ ሳይሆን፤ከመጡብህ ቆንጥር ሆነህ መገኘትን አትጥላው።

ለ’’ውሃ መዋኛ’’ ይመስል

ዘንድሮ የመሰረት ድንጋዩን ካስቀመጥን 10ኛ ዓመቱን በሚያከብረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ‘’ቆንጥር’’ን እንድንሆን የሚያደርጉን ተግባራት ተፈጽመውብናል ሴራ፣ደባ፣ተንኮል፣ሸር ብንል ድርጊቱን የማይገልጹ ተራ ቃላት ይሆኑብናል።

ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ማልማቷ መብቷ መሆኑን በአደባባይ አምነው፤ ግንባታውን እንዳናከናውን እንቅፋት የሚሆኑብንን ኃይሎች ቆንጥር ሆነን ጨምድደን ማስቀረት እንድንችል ተገፋፍተናል። ለአንድ አስርት በተለይም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ፋታ አላገኘንም።

የጋራ ተጠቃሚነት መርሃችን በጋራ ልማት በሩን ክፍት እናድርገው ብለን፤በውሃ ባለሙያዎች፣ በዲፕሎማቶች፣በከፍተኛ ባለሥልጣናትና በመሪዎች ጭምር ታዛቢዎች ባሉበት አድርገንም መተማመንን ሳይሆን፤ ተናካሽነትን የሚመርጡ መንግሥታት ገጥመውናል።

መጀመሪያ ግድቡን ለመገንባት አቅም እንደሌለን አድርገው የገመቱ ኃይሎች፣ቀጥለው ‘’ኢትዮጵያውያን ግንባታውን ለማጠናቀቅ አይችሉም’’ ብለው ተሳልቀውብናል።እርግጥ ነው ብድርና ዕርዳታ የሚሰጡን አካላት ስላልነበሩ አቅማችንን ቢጠራጠሩ አይደንቅም።በራስ አቅም ይከናወናል ብለው ስላልገመቱ።

ግድቡ አምና ውሃ መያዝ ይጀምራል ብለው ያላሰቡት የታችኛው ተፋሰስ አገሮች፣ ውሃ መያዝ ሲጀምር፤ድንጋጤና ግራ መጋባት ዋነኛ መለያቸው ሆኗል።ግድቡ በውሃ እየተሞላ ያለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የውሃ ዋና ስፖርት ማዘውተሪያ እጥረት ለማሟላት የተገነባ ይመስል?

ጊዜው ደረሰ!!!

ግድቡ በዚህ ክረምት 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ እንደሚይዝ ሁለቱ የዓባይ አገሮች አስቀድመው ቢያውቁም፤ ጊዜው እየተቃረበ ሲመጣ በአንድ በኩል መደነባበር በሌላ በኩል ደግሞ መተባበር ይዘዋል።

የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ዘንድሮን እንደማያልፍ ሲያውቁ ካለ እነሱ በጎ ፈቃድ ወይም ስምምነት እንዳይሞላ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።ሙሌቱ እንደማይቀር ሲያውቁ ደግሞ መደነባበር ይዘዋል።

መደነባበርን ወደ ትብብር ለመቀየር ደግሞ በዚህ አንድ ወር የካርቱም -ካይሮ ፣የካይሮ-ካርቱም ጉዞዎች ተበራክተውባቸዋል። የመሪዎች የጉብኝት ልውውጦች በር መክፈቻ ሆነው፣ ሌሎች በየደረጃው እየተመላለሱ ነው።

በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ላይ የዲፕሎማሲ ጫና እንዲያርፍ እየተሰራ ነው። ወታደራዊ ዝግጅት ደግሞ ሌላው የትብብር መስክ ሆኗል።የጦር ኃይሎች ግንኙነት ማጠናከርና ልምምድ ደግሞ የትብብሩ ማሳያዎች ሆነው ቀርበዋል። ቆንጥር ሆነን እንደምንመክተው ባያጠራጥርም።

ሱዳን በትግራይ ክልል የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በፈጠረላት አጋጣሚ ተጠቅማ ከኢትዮጵያ መሬት መቁረስ ችላለች። እስከ መቼ? መልሱን ጊዜ ይሰጠናል። መከላከያ ሰራዊታችንን ወደዚያ ስናዞር የሚፈጠረውን ነገር ለማወቅ ወታደር መሆን አይጠይቅንም።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን ሰላምን ለማደፍረስ የተደረገው ጥረት በጉባ ወረዳ ማንነትን መሰረት አድርጎ የተከሰተው ግጭት ከበስተጀርባው የግድቡን ግንባታ ማደናቀፍን ዒላማው አድርጓል። እነማን ይዘውሩታል ግልጽ ነው።

ብሔር ተኮር ጥቃት በኦሮሚያ ክልል በማስፋፋት አገርን የመበታተን ሚና እየተጫወቱ ያሉት እነማን እንደሆኑ የማያውቅ ዜጋ በዚህች አገር አለ ለማለት ይቸግራል።

የብሄር ዘውግ አቀንቃኞችና የኢትዮጵያን አንድነት በሚያስጠብቁ ዜጎች መካከል ግጭት መፍጠርን ስራው ያደረገ ወገን ምንጩ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥልቅ ምርምር አያስፈልገውም።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ቀውስ ለመፍጠር ሴራን የዕለት ሥራው ያደረገ አካል ከኢትዮጵያ ድንበር ባሻገር ወደሚገኙ ወገኖች መጠቆም ለአገሬ ሰው አይከብደውም።

በአጠቃላይ የአገሪቱን ሰላም በማናጋት ቢቻል አገሪቱን ማፈራረስ የውጭና የውስጥ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ የሚያካሂዱት ተግባር ሆኗል።የግድቡን ግንባታ ወደ 80 በመቶ በተጠናቀቀበት የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተቃረበበት ወቅት ምን ሊከተል እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።

መግባባትና መተማመን በመፍጠር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ተመስርተን ሱዳንና ግብፅን ሳንጎዳ የምንገነባው ግድብ ዋጋ ሊያስከፍለን ባልተገባ ነበር።እንዲያውም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንዳሉት’’ኢትዮጵያ 50 በመቶ፣ሱዳን 30 በመቶና ግብፅ ደግሞ 20 በመቶ ማዋጣት አለባቸው’’ያሉት መፈጸም ነበረበት።

አራተኛው አደራዳሪ?

ግብፅና ሱዳን ለአንድ ዓመት ያህል በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በግድቡ ላይ ያደረጉት ድርድር አላዋጣቸውም። በዚህ ላይ አደራዳሪው ተለውጧል።ዘመን ሲለወጥ ለውጥ ማምጣት ከጃጀሉና ሌሎች ሶስት አካላት ካልተጨመሩ ኢትዮጵያን ከግድቡ ግንባታ የሚገታት ኃይል አይገኝም በማለት ጫና የሚያሳድሩ አካላትን ለማግኘት እየተፍጨረጨሩ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣የአሜሪካ መንግሥት፣ የአውሮፓ ህብረት የታከሉበት ድርድር በአዲስ መልክ ለማስቀጠል ወጥነዋል።በዓባይ ጉዳይ ምንም ቢመጣ ፍንክች የማትለውና ሌሎችን መጉዳት የማትፈልገው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ባለፈው ዓመት ጋር በመርህ ላይ ከተመሰረተው ድርድር ውጭ ማንንም መጨመር እንዳማይገባ ገልጻለች።

ከሶስቱ አካላት ጋር ባላት መልካም ግንኙነት አደራዳሪነት እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይናገራሉ። ይሁንና ሁለቱ የተፋሰሱ አገሮች ሐሳባቸውን ለኢትዮጵያ እንዳላቀረቡት ተናግረዋል።

መላ ምትና እውነቱ

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ የግብፅ መንግሥት ከሚያቀርባቸው መላ ምቶች አንዱ ‘’ኢትዮጵያ እኛን ለመጉዳት አስባ እንጂ፤ ኃይል የምታመንጭባቸው ወንዞች ሞልተዋታል’’ የሚል ነው። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የውሃ ሀብታም ናት።ነገር ግን ወንዞቿ ገባር የሚያመነጩት ኃይልም ትንሽ ይሆናል።ትናንሽ ግድቦች በላያቸው ላይ መገንባት ይሻላል ወይስ ገባሮቹ በፈጠሩት ታላቅ ወንዝ ከፍተኛ ኃይል ማመንጫ መገደብ?

ግብጻውያን ሊረዱት የሚገባቸው ገባሮቹ ከሚሰጡት አነስተኛ ኃይል ላይ እየቀናነሱ መውሰድ ይሻላል ወይም ከገባሮቹ ከተጠራቀመው ኃይል ትንሽ ኃይል ወስዶ ኤሌክትሪክ ማመንጨት? ከዓባይ በጭልፋ መውሰድ ወይስ ከዓባይ ገባሮች በጭልፋ መውሰድ?

ከገባሮቹ ወንዞች የሚፈሰው ውሃ ሲቀንስ፣ ወደ ታችኛው አገሮች የሚፈሰው የውሃ መጠንም ይቀንሳል። ዓባይም በዚያው መጠን ውሃ ሊያመነጭ አይችልም። ጠርቀም ካለው ወንዝ መጠኑ ከፍ ያለ ውሃ በመያዝ ነው እንግዲህ 6ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት እየተሰራ ያለው።

የዓባይን ፍሰት መግታት አይቻልም።ፍሰቱ ተፈጥሯዊ በመሆኑ።ኢትዮጵያ የቻለችው የፍሰቱን አቅጣጫ በመቀየር ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ማዋል ነው።በግድቡ የሚያዘው ውሃ ኃይል ካመነጨ በኋላ ይሄዳል።ከዚያ በላይ ግድቡ በአንድ ጊዜ አይሞላም።በተፋሰስ አገሮች ጋር በሚደረስ ስምምነት በሂደት ይሞላል።

በዚህ ላይ ከ65 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ኤሌክትሪክ አያገኙም።የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዕድገትም ቀጭጯል።የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በኃይል አቅርቦት እጥረት የሚፈለገውን ያህል አላደገም።

እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የከተሜነት መስፋፋትም ኤሌክትሪክን መጠቀም የግድ ያደርጉታል።ግብፅ 100 በመቶ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እያገኘች፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 35 በመቶ ብቻ የኤሌከትሪክ አገልግሎት የሚያገኘው እስከ መቼ ነው?

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት መልስ እውነታውን ገላጭ ነው።

‘’ለሕዳሴው ግድብ የአባይን ውሀ ሳይሆን ዝናብ አትገድቡ ተብለን ነው የተከለከልነው። ከጣና ምንጭ ተነስቶ የሚፈስሰው ውሀ መፍሰሱን አላቋረጠም። ዕቅዳችን እኛ ለምተን ጎረቤቶቻችንን ማልማት ነው። ሕዳሴ ፈተናው ቢበዛም ቃል እንደ ገባነው ማሳካታችን አይቀርም። ውሀ አሞላሉን በተመለከተ ተደራድረን ስናበቃ እንሙላ ካልን ክረምቱ ያልፍና በዓመት አንድ ቢሊየን ዶላር ሀገራችን ታጣለች። ወንድሞቻችን ሳይጎዱ ውሀ የምንይዝበትን መንገድ ማመቻችት ግን ወድደን የምናደርገው ነው። የግብጽ እና የሱዳን ወንድሞቻችንም ይህንን በሰላም እንዲያዩልን ያስፈልጋል።’’ ብለዋል የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በግድቡ ላይ ያለውን አቋም ሲገልጹ።

ሸርታታዋ

ለግድቡ ግንባታ ከአጋርነት ወደ አደናቃፊነት የሚመስል አቋም የያዘችው፣ ለግንባታ የተሽከርካሪዎችና የማሽነሪዎች ድጋፍ ያደረገችው፣ ግድቡ እንደማይጎዳትና እንዲያውም የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንደሚኖራት ስታስታውቅ የኖረችው አገር አሁን ሸርተት ማለት ይዛለች።

ግድቡ የተመጣጠነ ውሃ በመያዝ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ስትናገር የነበረችው ባለፈው ክረምት በውሃ ተጥለቅልቃ የደረሰባትን የሕይወትና የንብረት ጉዳት ረስታ ይሆን? ያሰኛል።

ግድቡ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የሚጠጋ ውሃ ባይዝ ኖሮ፤ የሚያደርስባትን ጉዳት በራሱ አስተዛዛቢ ነው።

የሱዳን ወላዋይ አቋም ደራሲና ጋዜጠኛ ጌታቸው ወልዩ በዚህ ወር በታተመው በ’’አዲስ ጊዜ’’ መጽሔት እንደሚከተለው አቅርቦታል።

’’ጊዜው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጁን 2011 ወይም ሰኔ 2003 ዓመተ ምህረት ነበር። የሱዳን ሪፐብሊክ የኤሌክትሪክና ግድቦች ሚኒስትር ሚስተር ኦሳማ አብዱላህ፤ የአገሪቱን ዋና ዋና መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሰበሰቡና ‘’በሱዳን ሮይሴረስ ግድብ ዙሪያ 22ሺ ዜጎችን እንደገና ለማስፈር ብናቅድም፤ የዓባይ(ናይል)ወገን በሚፈጥረው ወቅታዊ ጎርፍና ደለል ለአደጋ እያጋለጠ ችግር ፈጥሮብናል።’’ በማለት ቅሬታቸውን አሰሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሰኔ 17 ቀን 2012 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የጻፉት ደብዳቤ ደግሞ ተቃራኒውንና ወላዋይ አቋም ያንጸባርቃል።ከ11 ዓመታት በኋላ የተጻፈው ደብዳቤ ምን ያህል የአቋም መዋዠቅ እንዳለ ያሳያል።

‘’የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ አንድ አሥረኛ እጅ ብቻ የሚሆነው አነስተኛው የሱዳን ሮሴይረስ ግድብ ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ብቻ የሚገኝ በመሆኑም ድርድሩ (የኢትዮጵያ፣ግብፅና ሱዳን)ቀጥሎ ስምምነት ላይ ሳይደረስ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በተናጠል የውሃ መሙላት ሂደት መጀመር የሮሴይረስ ግድብንና በተፋሰስ ዙሪያ ኑሯቸውን የመሰረቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ ያጋልጣል’’ ይላል።

በአሜሪካዋ የፍሎሪዳ ክልል የታምፓ ውሃ ምርምር ተቋም የሚሰሩ ሳይንቲስት ዶክተር ጥሩሰው አሰፋ የሱዳን ዓመታዊ የውሃ መያዝ አቅም 20 ቢሊዮን ኩዩብ ሜትር መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም ዓባይ ወደ ታችኛው ተፋሰስ አገሮች ከሚያደርሰው የውሃ መጠን እጅግ አነስተኛው መሆኑን ይገልጻሉ። ሱዳን መጨነቅ ያለባት በክረምት ወቅት ስለሚደርስባት ጎርፍ እንጂ፤ በውሃ መጠኗ መቀነስ እንዳልሆነ ምሁሩ በትዊተር ገጻቸው ያሰራጩት ጽሁፍ ያመለክታል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በዚሁ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ’’ የግብፅና ሱዳን ፍራቻ ለብቻ ለመጠቀም ባላቸው ፍላጎት የቅኝ ገዢያቸውን አሰራር በመከተል የሚመነጭ ነው።ሱዳን ውስጥ የተሰሩት ግድቦች የግብፅን ፍላጎት ሊነኩ በማይችሉ መልኩ የተሰሩ ናቸው።ዋናው ተጠቃሚና ውሃውን የምትቆጣጠረው ግብፅ ነች።’’

አንድነት

‘’በሀገርና በጋራ ጥቅም ላይ አንድ ዓይነት ራዕይ፣አንድ ዓይነት አስተሳሰብ፤አንድ ዓይነት ሥነ ልቡና ማሳረፍ ያስፈልጋል።ይሄ ካለ ማንም የውጭ ኃይል ጥቃት ሊያደርስብን አይችልም። ቁልፉ ነገር በአገር ጉዳይ ወይም በግል ጥቅም መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ አውቆ በጋራ ስትራቴጂ መንደፍ፣ማስተባበርና መተግበር ነው።ተባብሮ መቆም ይገባል።’’በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ያስገነዝባሉ።

ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ናቸው። በዓባይ ጉዳይ ተመራማሪነታቸውም ይታወቃሉ።

“የኢትዮጵያ ተጻራሪዎች እንዳይጠናከሩ ከውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ ከውጭም በጣም ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል። ይሄ ወዳጆቿ አጠገቧ እንዲሆኑ ይጠቅማል።ወዳጅነት እንዲጠናከር በንግድም፤ በኢንቨስትመንትም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ ይገባል። ጠላቶቿ እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ ኢትዮጵያን ለመጫን ፍላጎትና አቅም እንዳይኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል።’’

‘’በክረምት ካልጣለ ብቻ’’

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የተጀመረው ድርድርን ከማስቀጠል ውጭ ሌሎች አደራዳሪዎችን አትቀበልም ይላሉ።

‘’ይህንን አቋም መያዝ የሚያስከትለው አሉታዊ ጎን ቢኖርም ተባብረን እንወጣዋለን፤ ይህን አቋም በመያዛችን ከሚገጥሙን ፈተናዎች አንዱ የእጅ አዙር ግጭት ነው። ይኸውም በመተከል በኩል ተጀምሮ አይተነዋል’’ ብለዋል። የመተከል ግጭት እልባት እየተደረገለት ቢሆንም፣ጨርሶ ያልተጠበቀው የሱዳን ወረራ መከተሉንም ተናግረዋል።

‘’የሱዳን መንግሥት ድንበር መውረር ቀጥታ ግንኙነት ባይኖረውም፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ግን፣ በግድብ ድርድር ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ብለን እናምናለን’’ ማለታቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

በመጪው ክረምት የሚካሄደው የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት የማይካሄደው ዝናብ ካልጣለ ብቻ ሲሉ በቅርቡ የተካሄደውን ዌቢናር የጠቀሰው ዘገባ ያመለክታል።

የግድቡን ሁለተኛው ዙር ሙሌት ማከናወን የህልውና ጥያቄ መሆኑን የህልውና ጥያቄ መረዳት የዜግነት ግዴታ መሆኑን ማወቅ ከሚገባን ጊዜ ላይ ነን።


ግብፅና ሱዳን ፍላጎታቸው ሙሌቱን በአስገዳጅ ስምምነት ጠልፎ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር ማቅረብና ፍላጎታቸውን ማስፈጸም ነው።የአራትዮሽ ድርድር በሚል አዲስ ፋሽን ብቅ ያሉትም የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ባይችሉ እንኳን፤ለማዘግየት ነው።ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በጋራ እንጠቀም ማለትን ትክክለኛ ትርጉም ሳይረዱት ቀርተው አይደለም።

ስለዚህ የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር ጠላቶቻችንን በማሳፈር ታሪክ ማስመዝገብ ይጠበቅብናል። ዛሬም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንደምንመራ በማሳየት ድርድሮችን በተያዘው መንገድ መቀጠል ይገባናል።

ምስጋና

ከሥራም በላይ ሥራ፣ ለአገር ካለ ፍቅር በላይ ለሆነው የዕውቀትና የጉልበት አስተዋጽኦ ላደረጉ የግድቡ ሰራተኞች፣ የጥበቃ ተግባራቸውን ለሚያከናውኑ የፌዴራልና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ምስጋና ይድረሳቸው።

ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ ላደረጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም ይመሰገናሉ።

በግድቡ ዙሪያ በአገር ፍቅር ስሜት እየተንገበገቡ፣ ከመጋረጃው በስተጀርባ ያሉትን ጉዳዮች እየገላለጡ የዜግነትና ሙያዊ አስተዋጽኦቸውን ላበረከቱ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ምስጋና ይገባቸዋል።

በግድቡ ግንባታ ሂደት ከፍተኛ ድጋፍ ለሰጡት ሶስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮቻችን፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የግድቡን ግንባታ አመራር ለሰጡ፣ ላስተባበሩና ላስፈጸሙ አካላት ወደር የሌለው ገለታ ይድረስ።

የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅ ዕድገታችን እናረጋግጣለን!!!

Source:አዲስ ዘመን መጋቢት 27/ 2013 ዓ.ም

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa