የአዲስ አበባ አስተዳደር መጠነ ሰፊ መዋቅራዊ ለውጥ ሊያደርግ ነው

- አምስት ምክትል ከንቲባዎች ይኖራሉ

- የመሬት ልማት ኮርፖሬሽን ይቋቋማል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደር ችግርና እየበረታ ለመጣው የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት፣ በከተማው ታሪክ ከ14 ዓመታት በኋላ ትልቅ የተባለ የመዋቅር ለውጥ ሊያደርግ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር በከተማው መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ጥናት እንዲያካሄድ ያቋቋመው፣ የአደረጃጀትና የመዋቅር ለውጥ ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጥናቱን አጠናቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለከፍተኛ ባለሥልጣናትና ለመስኩ ባለሙያዎች ለውይይት የቀረበው ይኼ ጥናት፣ በፖለቲከኞችና በባለሙያዎች የሚያዙ ዘርፎችን ለይቶ አስቀምጧል፡፡

በጥናቱ መሠረት በፖለቲከኞች የሚመሩት ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ሲሆኑ፣ ሥራዎቹም ክትትልና ግምገማ ናቸው፡፡ በባለሙያዎች የሚመሩት ደግሞ ማዘጋጃ ቤታዊ ሥራዎች ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት ከተማው አንድ ከንቲባና አምስት ምክትል ከንቲባዎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ምክትል ከንቲባዎቹ የኢኮኖሚ ዘርፍ፣ የመሬት፣ የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ የትራንስፖርት መሠረተ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ዘርፍ፣ የማኅበራዊ ዘርፍ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕና የደኅንነት ዘርፍ ናቸው፡፡

ከንቲባውና አምስቱ ምክትል ከንቲባዎች ብቻ የከተማው ካቢኔ አባል ይሆናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ 22 የካቢኔ አባል ቢሮዎች አሉት፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት ቢሮዎቹ ከካቢኔ አባልነት ውጪ ተደርገዋል፡፡

በአዲሱ አደረጃጀት ቢሮዎች፣ ኤጀንሲዎች፣ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች፣ ጽሕፈት ቤቶችና በሥራቸው ያሉ ተቋማት የከተማ አገልግሎት ደረጃ ማውጣት፣ ተፈጻሚነታቸውን መከታተል፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

‹‹የካቢኔው ድርሻ በግልጽ ተለይቷል፡፡ ሁሉንም የዕለት ተዕለት ሥራዎች ሳይሆን አጠቃላይ ግብን መሠረት ያደረገ ስኬት እንዲመጣ መሥራት በሚችሉበት ደረጃ ድንበር ተበጅቶላቸዋል፤›› ሲሉ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አደረጃጀትና መዋቅር ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይፈ ፈቃደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዎቹ በሚከታተሏቸው ዘርፎች ሥር የኦፕሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጆች ይኖሯቸዋል ተብሏል፡፡

ይኼ ዘርፍ ከተለየ በኋላ ሌላው እስካሁን በፖለቲከኞች በመመራቱ ለውጥ ያልመጣበትና የሕዝብ ቅሬታ ሲቀርብባቸው የቆዩት ማዘጋጃ ቤታዊ ሥራዎች ናቸው፡፡

የከተማው ሥራ አስኪያጅና በሥሩ ያሉ ተቋማት፣ የውኃ አቅርቦት፣ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ፣ የፅዳትና ውበትና የመሳሰሉ ማዘጋጃ ቤታዊ ሥራዎች በባለሙያዎች  ይመራሉ ተብሏል፡፡

በዚህ መሠረት በከተማው ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ መሠረት ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት መስጠትና የልማት ሥራዎችን ማከናወን ከእነዚህ ባለሙያዎች ይጠበቃል፡፡

በዚሁ አዲስ መዋቅራዊ ለውጥ ጥናት በርካታ ኮርፖሬሽኖች እንደሚቋቋሙ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የመሬት ልማት ኮርፖሬሽን፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የገበያ ማዕከላትና ልማት ኮርፖሬሽን ይገኙበታል፡፡

የመሬት ልማት ኮርፖሬሽን እንዲያከናውናቸው የሚሰጡት ኃላፊነቶች የመሬት ዝግጅት፣ የካሳ ክፍያ፣ የምትክ ቤቶችና የቦታ አቅርቦት፣ ቦታ ማፅዳትና ወሰን ማስከበር፣ የለማ መሬት አቅርቦት፣ የመሬት ማስተላለፍ (ጨረታና ምደባ)፣ የሊዝ ክፍያ አፈጻጸምና ክትትል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ተቆጣጣሪ (ፌጉላቶሪ) ሆኖ ይቀጥላል፡፡

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ከመውጣቱ በፊት፣ የመሬት ጉዳዮች የሚወሰኑት በሊዝ ቦርድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከሊዝ አዋጁ በኋላ ይኼንን ሥራ ካቢኔው ተረክቦታል፡፡

ነገር ግን ካቢኔው ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መመርያ ከመስጠት ይልቅ፣ የባለሀብቶችን ጉዳይ በስም ደረጃ እየነጣጠለ በመመልከት ጊዜውን ሲያጠፋ የቆየ በመሆኑ በአዲሱ አሠራር ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ብቻ እንዲያይ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በመሬት ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ በሚሰጠው አካል እስካሁን አንድ ውሳኔ ላይ አልተደረሰም፤›› ሲሉ አቶ ሰይፈ ገልጸዋል፡፡

ይኼ አዲስ ስትራቴጂ በርካታ የመዋቅር ለውጥና መጠነ ሰፊ ሹም ሽር፣ እንዲሁም የሠራተኞች የሥራ ሽግሽግ ያስከትላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የዚህ ዓይነት ከፍተኛ የመዋቅር ለውጥና የሠራተኞች ቅነሳ የተደረገው፣ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በ1995 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ ሆነው በመጡበት ወቅት ነበር፡፡

በወቅቱ አሥር ክፍላተ ከተሞች የተፈጠሩ ሲሆን፣ በማዕከል የነበሩ በርካታ ሥራዎች ወደ ክፍላተ ከተሞች ተዘዋውረው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በርካታ ሠራተኞች ከመቀነሳቸውም በላይ ሽግሽግም መካሄዱ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላ በአዲስ አበባ በአነስተኛ ደረጃ በርካታ ለውጦች ቢደረጉም፣ በአሁን ወቅት የተካሄደው ጥናት በርካታ ለውጦችን በማምጣት በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ጊዜ ከነበረው ለውጥ ጋር የሚቀራረብ እንደሚሆን እየተገለጸ ነው፡፡


Source:reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman