የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ 1ኛ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የብልጽግና ፓርቲ አባል ሴቶችን በአደረጃጀት አቅፎ የሚመራ ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚታገልና የሚያታግል የፓርቲ ክንፍ ነው፡፡ ለዚሁ አላማው መሳካት የራሱ የሆነ ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ ኖሮት በጉባኤ በሚወከሉ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚመራና በየሁለት አመት ተኩል ጉባኤ የሚያካሄድ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ በአይነቱና በሂደቱ ታሪካዊና ከውህደት በኃላ እና ከፓርቲያችን አንደኛ ጉባኤ ማግስት የተካሄደው ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ በደመቀ እና በወሳኝ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ የመከረ ነው። በቀጣይም የሊጉን አደረጃጀት ማጠናከር በሚቻልባቸው እና በሰላም ጉዳዮች ላይ የጉባኤው ተሳታፊዎች ጥልቅ ውይይትን አድርገዋል። የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተኛዊ ብልጽግና በሚል መሪ ቃል በእህትማማችነት መንፈስ ጎልብቶ ሊጋችን የመጀመሪያውን ታሪካዊ ጉባኤ አካሂዶ ለቀጣይ ሊጉን ሊመሩ እና ሊያሻግሩ የሚችሉ አመራሮችን በመምረጥ በስኬት ተጠናቋል፡፡
መድረኩ ላይ ይንጸባረቁ የነበሩ ጥልቅ የፍቅርና የአንድነት መንፈሶች፤ የህብረ ብሄራዊ አንድነት ገጽታ ደምቆ የታየበት ይህ ታሪካዊ ጉባኤ፤ የመላውን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ አለባበስ እና የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን ጨምሮ የነበሩት የእህትማማችነት መስተጋብሮች ተደማምረው ለጉባኤው ታላቅ ድምቀት ነበሩ፡፡
ሃገራችን ባለፉት ጥቂት አመታት ያለፈችባቸውና ሁለንተናዊ ለውጥን ባመጡ ታሪካዊ ክስተቶች ውስጥ ሁሉ ሴቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆነው በጠንካራ ህብረብሄራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ብዙ ሰርተዋል።
ሴቶች ለብልጽግና ፓርቲ እውን መሆንና ለለውጡ መሳካት፣ ለሃገራዊ ምርጫ ስኬት፣ በህልውና ዘመቻው በግምባር ከመሰለፍ አልፎ የሰራዊቱ ደጀን በመሆን፤ ከውጭም ከውስጥም በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ሲጋረጡብን የነበሩትን ተግዳሮቶች በጽናት መወጣት እንዲቻልና በማእበል ውስጥ ጸንታ የምትቆምና ፈተና የሚያጠነክራት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያበረከቱት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ከፓርቲው ውህደት ዋዜማና ማግስት እስካሁንም ድረስ የሚታዩትን አንዳንድ አለመረጋጋቶችን በማከም በዜጎች ላይ ሊደርስ ይችል የነበረን ጉዳት ለመቀነስ ጭምር የነበራቸው ሚና በመመልከት ወደፊትም የተረጋጋች፤ ሰላማዊና ብልጽግናዋ የተረጋገጠባት ሃገርን ለመፍጠር የሴቶች ተሳትፎ መተኪያ የሌለው መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ሴት የማህበረሰብ መስተጋብር ምሰሶ ናት። ግማሹን የህዝብ ቁጥርንም ይዛለች። ሆኖም ግን ለኢትዮጵያዊነት ማህበራዊ መስተጋብር፤ ለምጣኔ ሃብትና ለጠቅላላ ሃገራዊ ቁመና ሴት ያላትን ተገቢ ቦታ ሳታገኝ፤ የሚገባትንም ያህል ሳትጠቀም እንደውም በብዙ ኋላቀር አስተሳሰቦች ማነቆነት ሳቢያ ለብዙ ችግር ተጋላጭ ሆናለች።
ብልጽግና ከጽንሰቱ ጀምሮ እስከ ውልደቱና ዛሬ ላይ እስከደረሰበት ደረጃ ድረስ ሴት ለሃገር ሰላምና ብልጽግና የምታበረክተውን የማይተካ ሚና በመረዳት በእውነትና በእውቀትላይ ተመስርቶ የሴቶች መብት መከበር ከንግግር ባለፈ መተግበር እንዲጀምር ያደረገ ፓርቲ ነው። የብልጽግና ሴቶች ሊግ የመጀመሪያው የሴቶች ሊግ ጉባኤ በዚሁ እሳቤ ውስጥ የተካሄደ መሆኑ የፈጠረው ስሜት ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ኢትዮጵያ የትናንቱን አድሎአዊነት በሴቶች ከፍተኛ ተጋድሎና መስዋዕትነት ከመላው ዜጎች ጋር በመሆን አሽቀንጥራ ጥላ የነገን ተስፋም በከፍተኛ ደረጃ ሰንቃ እየተንቀሳቀሰች ባለችበት ሂደት ውስጥ ከባድ የሚባሉ የውጭና የውስጥ ተግዳሮቶች ወደፊት እንዳትራመድ ለማድረግ እጅና አግሯን ሊያስሯት በብዙ ይጥራሉ።
ታሪካዊው ጉባኤያችን ሃገራችን የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች ልክ እንደ ትናንቱ በራሷ በህዝቦቿ የተባበረ ክንድ እንደምትፈታ በመፍትሄው ሂደትም የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የይስሙላ ሳይሆን የሚታይ ተጨባጭ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ግብአት የተገኘበት ጉባኤ ነው።
ኢትዮጵያውያን ሴቶች በብልሃት ብዙዎችን ያስደመሙ ውሳኔዎቸን ሲሰጡ፤ ባሉበትም ደረጃ የላቀ የአመራርነት ጥበብንም ሲያሳዩ እንደመኖራቸው የዛሬውም ትውልድ ያለ ማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ችግሮቻችንን በራሳችን ልንፈታበት የሚያስችል ጥበብና አቅም አለን በሚል ጽኑ አቋም ጉባአኤው የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት አቅም ማጠናከር ለሃገር ብልጽግና እውን መሆን ያለውን ፋይዳ በግልጽ አመላክቷል።
በሃዋሳ ከተማ የተካሄደውና ታሪካዊው የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ አንደኛ መደበኛ ጉባኤም ከዚህ ቀጥሎ የቀረበውን ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማዉጣት ተጠናቋል።
1ኛ) ኢትዮጵያ በየወቅቱ ከፍተኛ የሚባሉ ተግዳሮቶች እያጋጠሟት የመጣች ሆኖም እያንዳንዱን ችግር ወደ እድል በመቀየር ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ምቹ ሆና ለመገኘት እየታተረች ያለች ታላቅ ሀገር ናት፡፡ የእኛ ፍትሀዊ የሆነ የእድገት እና የልማት እንቅስቃሴያችን አልዋጥላቸው ያሉ የውጭ ጠላቶቻችንና የውስጥ ተላላኪዎቻቸው የሀገራችንን አንድነት ለመበተን ሌት ከቀን እየሰሩ ባሉበት ወሳኝ የታሪክ ምእራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያ ለሁላችንም በቂና ታላቅ ሀገር፤ ሀይማኖቶች በፍቅርና በመተጋገዝ የሚኖሩባት፤ ድንቅ ምድር እንደሆነች ለማህበራዊ መስተጋብር ምሰሶ የሆንነው እኛ ሴቶች ይበልጡን እንረዳለን።
ሆኖም መላ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የኖሩበትን የእለት ተእለት እውነታ በመሻር በፍቅር አብሮ መኖር ለኛ እንግዳና አዲስ እንደሆን ለማስመሰል ብዙዎች በሚደክሙበት ፈታኝ መንገድ ላይ እንገኛለን።
በቅርቡም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እምነትን፣ ማንነትንና መሰል ልዩ ልዩ መገለጫዎችን እንደ ግጭት መነሻ ሊያደርጉ የመጨረሻ አቅማቸውን የተጠቀሙ ሀይሎች የነበሩ ቢሆንም አስተዋይ በሆነው ህዝባችን ትብብር አሳፋሪ ሽንፈት ሲያጋጠማቸው ተመልክተናል፡፡
በመሆኑም ሴቶች እንደማንኛውም ዜጋ ከሚደርስብን በደል በተጨማሪ በሀገር አንድነት አደጋ ውስጥ መውደቅ እና ሰላም መታጣት የሚሰማን ስሜት ፍጹም መራር ነው። በመሆኑም በምንኖርበት አካባቢ ሰላማችንን እና አንድነታችንን ከሚሸረሽሩ ሀይሎች ራሳችንን በማራቅ የበለጠውን ጊዜያችንን ለጋራ ሀገራችን አንድነትና ለሰላማችን መጠበቅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሁሉም መስክ ለመሰለፍ ቃል እንገባለን!!
2ኛ) ለዘመናት የታየው የመገፋፋት እና የአግላይነት ስሜት ያለው የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ ተቀርፎ ሀገራችንን በጋራ የምናስተዳድርበት ሁኔታ እየተፈጠረ ባለበት ሁኔታ ዛሬም እኩልነትና ፍትሀዊነት በደል ሆኖ የሚሰማቸው ሀይሎች እየሰሩት ያለው ደባ በከፍተኛ ትኩረት ክትትል ሊደረግበት የሚገባ ነው፡፡ ከማንም በላይ እኛ ሴቶች የሚበጀንን መርጠን መንግስት መስርተን እየተንቀሳቀስን ባለንበት በአሁኑ ሰዓት በእጃችን የገባውን የነጻነት እና የአንድነት ስሜት የሚያደበዝዙ በርካታ አስነዋሪ ድርጊቶች እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ ፈተናው ሊበዛ ቢችልም ብልጽግናን እውን ከመሆን የሚያግደው ነገር ባለመኖሩ የተጀመረውን ለውጥ በማንኛውም መስዋዕትነት ማስቀጠል ለኛ ለሴቶች ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ለዘመናት ሲሸጋገሩ የመጡ በርካታ ችግሮችም የተጠራቀሙባት ምድር ናት፡፡ እኛ ሴቶች ደግሞ የትውልድ ቀራጮች ነን። በስነምግባር የታነጸ ከምንም በላይ ሃገሩንና ህዝቡን ያስቀደመ ምክንያታዊ ትውልድን ለመገንባት ደግሞ የኛ ሃላፊነት እጅግ ከፍተኛ ነውና ይህንን የሃገር ሃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል አብሮነት ያስፈልገናል። በሃገር ግንባታ ውስጥ ተገቢውን ሚና መጫወት እንድንችል የተሻለ የፖለቲካ ተሳትፎና ውክልና እንዲኖረን እንዲሁም የውሳኔ ሰጪነት አቅማችንን ለማጎልበት ለማጎልበት የምናደርገውን ሁለንተናዊ ትግል አጠናክረን መቀጠል ይገባናል።
የሊግ አደረጃጀታችንን ይበልጥ በማጠናከርና አንድነታችንን በህብረ ብሔራዊ እህትማማችነት በማድመቅ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል እኛ ሴቶች ቃል እንገባለን!!
3ኛ) ሌብነትና ጽንፈኝነት ለሀገራችን እድገትም ይሁን ለአጠቃላይ ብልጽግናችን ዋነኛ ጠንቆች ናቸው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገራችን እያየነው ያለውን አጠቃላይ ብልሽት ማረም የህልውና ጥያቄያችን መሆኑን ሁሉም ሰው ሊገነዘበው ይገባል።
ሌብነትን አምርረን መታገል ካልቻልን ጥፋቱ ገደብ የለውም፡፡ የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ በእርዳታ ጭምር ተለምኖ ከሚመጣ ቁሳቁስ ጀምሮ በሞትና በህይወት መካከል እያተጣጣሩ ያሉ ሰዎችን ለመታደግ ከሚሰጥ ምግብ ላይ ጭምር ቀንሶ የሚያስበላ፤ ህሊናን ፈጽሞ የሚያሸጥ የሞራል ዝቅጠት መገለጫ ነው፡፡ ሌብነት በሀገራችን ይጥፋ ከተባለ ለዚህ ስኬት የኛ የሴቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ሴቶች ጓደኞቻችን ፤ባሎቻችን፣ ልጆቻችን አጠቃላይ ቤተሰባችንና መላው ማህበረሰብም የኛ የስነምግባር ልህቀት ማሳያ መነጽሮቻችን ናቸው። እኛን ጨምሮ ምድራችንን የሞላው ሀይልም በእጃችን ላይ ነው፡፡ በመሆኑም በቅርባችን ካሉት ጀምረን እያሰፋን በመሄድ የሌብነትን ሰንኮፍ ከሀገራችን ለመንቀል አምርረን ከተነሳን የሚሳነን ነገር ሊኖር አይችልም፡፡
የአክራሪነት መንፈስንም ስንመለከት ከራስ ወዳድነት የሚነሳ፤ ለእኔ የሚያስፈልገኝ ለእህቴም ሆነ ለወንድሜ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ካለማሰብ የሚመነጭ የግለኝነት በሽታ ነው፡፡ በመሆኑም የእኔ ማንነት፣ እምነትና ሌሎች መገለጫዎቼ ታላቅ እንደሆኑ ማመን፤ የእኔ ማንነትና መገለጫዎቼ እንዲከበሩልኝ የመፈለጌን ያክል ለሌላውም እኩል ከበሬታ ሊኖረኝ እንደሚገባ ትውልዱን በተገቢው መንገድ ማስተማር ማሳወቅና ትክክለኛውን መንገድ የመምራት ሃላፊነት እንዳለብን እንረዳለን። በመሆኑም ለእኛ ለሴቶችም ይሁኑ ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ ጠንቅ የሆኑትን የሌብነትና የጽንፈኝነት በሽታዎችን አምርረን ለመታገል ቃል እንገባለን፡፡
4ኛ) ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ ክፉ ዜጎች አጠቃላይ ማህበረሰቡን በተዘዋዋሪም ቤተሰቦቻቸውን የሚያሰቃዩበት አንደኛው የብልጽግናችን እንቅፋት የመልካም አስተዳደር እጦት ነው። ዜጎች ኑሯቸውን እንዲጠሉ በማድረግ ወደ ምሬት እንዲገቡም ያደርጋቸዋል፡፡ ህዝብ መርጦ ባስቀመጠን ወንበር በአገኘነው አጋጣሚ በሙሉ ሰዎችን የምናሰቃይ በርካቶች መሆናችንን በየቢሯችን በር ውሎውን ያደረገው ህዝባችን ህያው ምስክር ነው፡፡
መጪው ጊዜ ለሴቶች ይዞ የሚመጣውን በርካታ መልካም ነገር በፍትሃዊነት እንዳንካፈል ጋሬጣ ሆኖ እያስቸገረ ያለውን የመልካም አስተዳደር ማነቆ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጣጥሰን እንደ ሀገር ለመነሳት በጋራ ርብርብ ለማድረግ ቃል እንገባለን!!
5ኛ) የማህበራዊ ተቋማት መበልጸግ ከሚገባቸው ዘርፎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ተቋማቱ ለሁሉም ዜጋ የሚሰጡት አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ ለሴቶች ደግሞ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
ሴት ስትማርም ሆነ ጤናዋ ሲጠበቅ የአንድ ግለሰብ ተጠቃሚነት አይደለም ጎልቶ የሚወጣው። ይልቁንም የቤተሰብ አለፍ ሲልም የማህበረሰብ እንጂ። በተፈጥሮና በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ሴቶች ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ተያይዘው ለሚመጡ ጫናዎች ተጋላጭ ሆነው ኖረዋል። ይህንን መራር እውነታ በጠንካራ ማህበረሰባዊ ንቅናቄ፤ በመዋቅራዊ አደረጃጀትና ባለን አቅም ሁሉ በመታገል፤ ከዛሬ የተሻለ ነገን ለልጆቻችን የማውረስ ሃላፊነትን የምንወጣው እኛ የዛሬዎቹ ከፊት ተሰላፊ ሴቶች ነን።
የሴቶችን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ግብአት የሆኑትን የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከተደራሽነት ጀምሮ እስከ አገልግሎት ጥራት ድረስ የምንለምነው ጉዳይ ሳይሆን ሊሟላልን የሚገባው መሰረታዊ መብታችን እንደሆነ በመገንዘብ ለተሻለ ተጠቃሚነት አብዝተን ልንታገል ቃል እንገባለን!!
6ኛ) ሴቶች በህይወታቸው ሊጋፈጡ የሚገደዷቸው አብዛኞቹ ችግሮች የሚፈልቁት ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነው፡፡ ሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኝነትን ከነአስተሳሰቡ ነቅለን በመጣል ሴት ብርቱ፤ በራሷ መቆም የምትችል፤ ከራሷም አልፋ ለሌሎች የምትተርፍ ፅኑ መሆኗን የምንገነዘብበትና የምንተገብርበት ወቅት አሁን ነው።
በመሆኑም ቀጣዩ የብልጽግና ጉዟችን እንዲሳካ ካስፈለገ የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደ መጀመሪያ አጀንዳ ተደርጎ የሚሰራበት ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ጠባቂዎች ሳንሆን ገቢ ፈጣሪዎች እንደሆን አምነን አዳዲስ ሀሳቦችን ከማፍለቅ ጀምሮ የራሳችንን ገቢ በራሳችን የምናፈልቅበት የአስተሳሰብ ከፍታ ላይ ልንደርስ ይገባል፡፡
በዙሪያችን ያለውን ምቹ ሁኔታ አንድም በመለየትና በማወቅ ቀጥለንም ለኛም ሆነ ለቤተሰባችን ሊጠቅም በሚችል መልኩ ወደ ስራ በማዋል ምግባችንን ከጓሯችን ማብቀል መጀመር ይኖርብናል። ለልጆቻችን ምቹና ለምለም ኢትዮጵያን ለማውረስም የዛሬው የኛ በጎ አሻራ ያለውን ሚና ተገንዝበን በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ሀገራችንን አረንጓዴ በማልበስ በኩራት ለትውልድ የምንናገረውን ስራ ዛሬ ላይ እንሰራለን።
በዚህ ፈጣን አለም ውስጥ ከሚለዋወጡ አዳዲስ አስተሳሰብና አሰራሮች ጋር ራሳችንን በፍጥነት በማላመድ አንድም በምግብ ራስን ለመቻል በሌላ አንጻር ደግሞ የኢኮኖሚ አቅምን ለመደጎም ጭምር አስበን ጠንክረን ለመስራት ቃል እንገባለን!!
7ኛ) የኑሮ ውድነት አለማቀፋዊ ገጽታ እንዳለው እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ በየአካባቢያችን የሚገኙ ስግብግብ ነጋዴዎች መነሻነት እየተቃወሰ ያለው የሀገር ኢኮኖሚ ሁላችንንም እንደሚመለከተን አምነን በአንድ በኩል የተለያዩ ኢኮኖሚውን ሊያግዙ የሚችሉ የምርት ሂደቶች ውስጥ በመግባት፤ በሌላ በኩል እያጋጠመ ካለው ፈተና አኳያ የኑሮ ዘይቤያችንን ከማስተካከል ጀምሮ ብልሹ የሆኑ አሰራሮችን ጭምር በመታገል የተሻለ ነገን ለመፍጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲኖረን ለመስራት ቃል እንገባለን!!
8ኛ) በሃገር አብሮ በፍቅር መኖር፣ ለሃገር ሲባል ደግሞ አብሮ መሞት ለኢትጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ በኑሮ ካዳበረው እሴቱ ውስጥ የመተጋገዝና የመረዳዳት አይነተኛ ባህርይ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።
ከነአባባሉም "ከሩቅ ቤተሰብ የቅርብ ጎረቤት ይሻላል" የሚሉ እህትማማችነትንና ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱ ለማህበረሰባዊ ትስርርር ትልቅ ግምትን የሚሰጡ እሴቶች ያሉባት ታላቅ ሃገር ባለቤት ነን።
በመሆኑም ለፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያ ሳንሆን ራሳችንን ከጽንፈኝነት አርቀን ይህ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ወንድምን እህትን ባልንጀራን እንደራስ አድርጎ የመውደድ አስተሳሰብ በውስጣችን በመቅረጽ ለእኛ የምንሻውን ሁሉ ለእህታችን/ወንድማችን የሚያስፈልገው እንደሚሆን በመረዳት የእህትማማችነትና ወንድማማችነት መርሃችንን ይበልጥ ወደ እያንዳንዱ ሰው እንዲደርስ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን።
9ኛ) በቀጣይ ዓመት ይጀመራል ተብሎ የሚታሰበውን ሀገራዊ የምክክርና የውይይት መድረክ ይበልጥ ስኬታማ ሆኖ ሀሳባችን የምንገልጽበት የሌሎችንም ሀሳብ የምናዳምጥበት እንዲሆን ከወዲሁ ሴቶች ባላቸው ማህበረሰባዊ ቦታ ተጠቅመው ሊሰሩ ይገባል፡፡
ይህን ለዛሬዋና ለነገዋ የበለጸገች ኢትዩጵያ መፈጠር ትልቅ ሚና ያለውን እንቅስቃሴ ከወዲሁ ለማጠልሸት ብዙዎች በርካታ እንቅፋቶችን ሲደረድሩ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም ፈተናዎቹን ተራምደን ካሰብነው ለመድረስ ያስችለን ዘንድ የታቀደው የሀገራዊ ምክክር መድረክ ውጤታማ እንዲሆን የድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን!!
በመጨረሻም ይህ ጉባኤ እንዲሳካ ቀን ከሌት ለደከማችሁ፤ በጉባኤው ለመታደም ከሩቅም ከቅርብም የተገኛችሁትን በሙሉ በብልጽግና ሴቶች ሊግ ስም ላቅ ያለ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን። እስከ ቀጣይ ጉባኤ እንዲተገበሩ አቅጣጫ የተቀመጠባቸውንና ሌሎችንም ተግባራት ከግብ ለማድረስ የበኩላችንን እንድንወጣም በመላው የኢትዮጵያ ሴቶች ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ብልጽግና ለሴቶች፤ ሁሉም ሴቶች ለብልጽግና!!
የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘልአለም ትኑር!!
ሰኔ 24/2014 ዓ.ም
ሀዋሳ፣ ሲዳማ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ