ʺየሞቱት ያስለቅሳሉ፣ የተረፉት ያስጨንቃሉ"



የሞቱት ያስለቅሳሉ፣ የቀሩት እጣ ፈንታ ያሳስባል፣ ምን ይገጥማቸው? ማን ይመጣባቸው? ማንስ ይነሳባቸው? በማለት፡፡ እንኳን በግፍ ያለፈ፣ በእድሜው ያረፈ እንኳን ያስለቅሳል፡፡ የሞት ጥላ ከባድ ነው፣ ጨለማ ጥሎ ብርሃን ያስናፍቃል፣ ሳቅን አስረስቶ በእንባ ማዕበል ያጥለቀልቃል፡፡

ሞት አዲስ ነው አይለመድም፣ ባይተዋር ያደርጋል፣ ተስፋ ያሳጣል፣ በጨለማ ይከባል፤ በግፍ ሲሆን ደግሞ ሞት ብቻ ሳይሆን የሞት ሞት ይሆናል፡፡ ብልኾች ሲጸልዩ ʺአሟሟቴን አሳምረው" ይላሉ፡፡ ሞታቸው በግፍ እንዳይሆን፣ ሰው በሌለበት፣ አፈር አልባሽ ቀባሪ በማይገኝበት፣ ታሞ ፈጣሪ ይማርህ በማይበላበት እንዳይሆን ሲመኙ፡፡ አለፍ ሲልም ሞቴን በክረምት አታድርግብኝ ይላሉ፡፡ ለምን ካሉ ለቀብር የሚመጣው እርሻ ማረሱን፣ አረም ማረሙን፣ ከብቶች ማሰማራቱን ይተዋል፣ ፍየሎቹን ነብር ይበላበታል፣ ልጆቹን ጎርፍ ይወስደባታል ብለው ሲለሚያስቡና ስለሚጨነቁ ነው፡፡
ሞትም ክብር አለው፣ ቀብርም ጌጥ አለው፤ ሠውን ፈጣሪ እስትንፋስ እንደ ሰጠው ሁሉ እስትንፋሱን ነጥቆ ቢወስደው ሁሉም በእርሱ ነውና አንተ ታውቃለህ፣ አንተ ሰጠህ አንተው ነሳህ፣ ተመስገን ተብሎ ይታላፋል፡፡ የፈጣሪን ሥራ ሰው ሲያፈርሰው፣ የንጹሐንን ደም በግፍ ሲያፈስሰው ግን አብዝቶ ያስቀልሳል፡፡
ለወትሮው ፍትሕና ርትዕ በሰፈነባት፣ ሰው በሰውነቱ በሚከበርባት፣ ሰላምና ፍቅር በነገሠባት፣ አንድነት በጠነከረባት፣ የሀገር ፍቅር ኃያል በሆነባት፣ ከራስ በፊት ሀገርና ሕዝብ በሚቀድምባት፣ ለክብሯ ደምና አጥንት በሚገበርባት፣ ሕዝብን ለማስከበር፣ ሠንደቅ ዓላማን ለማክበር ሕይወት በሚሰጥባት በታላቋ ኢትዮጵያ ፍቅር ተረስቶ፣ ጥላቻና እኔ ልቅደም ተስፋፍቶ ንጹሐን በግፍ ይሞታሉ፣ ልጆች አሳዳጊ አልባ ይቀራሉ፣ አዛውንቶች ጧሪ አልባ ይሆናሉ፡፡
ʺዓለም ሁለት ነው፣ አንድም ሲወልዱ ቀን አንድም ሲድሩ ነው" እያለች የምታዜመው እናት፣ ወልዳ የልጆቿን ሰርግ ለማየት አልታደለችም፤ መውለድ እንጂ ማሳደግ አልተፈቀደላትም፡፡ አምጣ ትወልዳለች፣ አዝላ ታሳድጋለች ለቁም ነገር ይደርሱልኛል ብላ ስትጠብቅ በክፉዎች ሰይፍ ከፊቷ ላይ ታጣቸዋለች፡፡ በግፍ ትነጠቃለች፡፡
የረቀቀው ኢትዮጵያዊነት፣ ከክብርም ክብር የሚሰጠው ሰብዓዊነት ተረስቶ በደል ያልተገኘባቸው፣ ጥፋት ያልተመዘገበባቸው ንጹሐን በሀገራቸው፣ በሚወዷት ቀያቸው፣ ልጆች ወልደው ባሰደጉበት ባድማቸው በግፍ ላይመለሱ ያልፋሉ፤ ለዘላለም ያሸልባሉ፡፡
ከሳምንታት በፊት የንጹሐንን ደም ያፈሰሰው የሽብር ቡድን ሌላ ግድያ ፈጽሟል፡፡ የተሰበረው ልብ ሳይጠገን ሌላ ሐዘን አምጥቷል፡፡ ጠባሳው ሳይሽር ተጨማሪ ጠባሳ ሰጥቷል፡፡ ከአንደኛው አካባቢ ወደ ሌላኛው አካባቢ እተዘዋወረ ንጹሐንን ዒላማ ያደረገ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ቀጥሎበታል፡፡ በጥላቻ የሰከረው ኦነግ ሸኔ በንጹሐን ደም እጁን እየታጠበ ይሳካልኛል የሚለውን ዓላማ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ላይ ነው፡፡
ማንነት ተኮር ጥቃት የሚደርስባቸው ንጹሐን ማሳቸውን አርሰው ቡቃያ በሚያዩበት፣ ወተት ከላሞቻቸው፣ እሸት ከበሬዎቻቸው በሚጠብቁት በክረምት የክፉዎች ሰይፍ እያረፈባቸው ነው፡፡ እንሽሽ ቢሉስ ወንዝ በሚሞላበት፣ ዝናብ በሚበዛበት፣ ጉም በሚጎተትበት፣ ገደል በሚናድበት በዚህ በክረምት ከሞቀ ቤት ወጥቶ፣ ከቀየ ተሰናብቶ ወደ የት ይሄዳል? እንኳን ሰው እንጨትና ገለባ ወደ ቤት በሚገባበት፣ የራቀው በሚቀርብበት፣ ወፍ እንኳን ማደሪያዋን ሠርታ በምትገባበት በክረምት የት ይደረሳል? የትስ ይሄዳል? በደል ያልተገኘባቸው፣ የሚያራምዱት ፖለቲካ የሌላቸው ንጹሐን አንገታቸው ለሰይፍ፣ ግንባራቸውን ለጥይት እየሰጡ በክፉዎች እጅ ላይመለሱ ያሸልባሉ፡፡
በግፍ የሚፈስሰው እንባና ደም አላቋረጠም፡፡ የሽብር ቡድኑ ሞፈርና ቀንበር በተሸከሙ አባቶች፣ እንዝርትና ጥጥ በጨበጡ እናቶች፣ ጭቃ እያቦኩ በሚቦርቁ ሕጻናት ላይ በትሩን ማሳረፉን ቀጥሎበታል፡፡ እነርሱ ለታረበ ማብላት፣ ለተጠማ ማጠጣት ነበር ግብራቸው፣ ምላሹ ግን ሞትና ስቃይ ኾነባቸው፡፡
ድሮ ለሟች ይበላኝ ቋሚ ይጠነክራል፤ ይጽናናል ከሐዘኑ የሚያጽናናው አይጠፋም ይባል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ይብላኝ ለቋሚ፣ ይብላኝ ለቀሪ ኾኗል፡፡ ምክንያቱም በክፉዎች ሰይፍ ላለመጨፍጨፍ በየ ደቂቃዋ ይጨነቃሉ። ከአሁን አሁን ክፉዎች ይገድሉኝ እያሉ መሳቀቅ አለና፡፡ የተረፉት ያስጨንቃሉ፡፡ የተረፉት እንቅልፍ ያሳጣሉ፡፡
ብዙዎች የሚቀኑባት፣ እናታችን የሚሏት፣ ተስፋቸው ያደረጓት፣ ታሪኳን መስማት፣ ዝናዋን ማንሳት የሚመኙላት ኢትዮጵያ በጥቂት ክፉ ልጆቿ ደም የሚፈስስባት፣ የጅምላ መቃብር የበዛባት፣ በእድሜ መሞት፣ ታምሞ ማሸለብ እንደ እድል የሚቆጠርባት ኾናለች፡፡
የሚፈስሰው ደም ይቆም ዘንድ እንደ ቀደመው ሁሉ ለሰብዓዊነት እንቁም፣ ከሀገርና ከሕዝብ በፊት ራስን እናስቀድም፡፡
ኢትዮጵያዊነት አንድነት ነው፤ አንድነት ያጠነክራል፣ ፍቅር ያስከብራል፣ አስተሳስሮ ያኖራል፡፡ ዘረኝነት ይጥላል፣ ዘረኝነት ይከፋፍላል፤ ሀገር አልባ ያደርጋል፡፡ መወቃቀሱን ወደ ጎን ትቶ በአንድነት ተነስቶ የጋራ ጠላት በጋራ ማጥፋት፣ በእድሜ እንጂ በግፍ ንጹሐን የማይሞቱባት ኢትዮጵያን መፍጠር ግድ ይላል፡፡
የውጭ ጠላትን እየመለሰ፣ ከወንዝ ማዶ እየደመመሰ የኖረ ሕዝብ ከጉያው የበቀለውን፣ በጥላቻ የሰከረውን ቡድን ማጥፋት አይሳነውም፤ በአንድነት ከተነሳ፣ ክንዱን በጥፋተኞች ላይ ካነሳ ሆኖለት የሚሰነብት የሽብር ቡድን አይገኝም፡፡ አንድ ኾነን በመቆም፣ በማስተዋል፣ በብልሃት ለንጹሐን እንድረስላቸው፣ ሰላም ይመጣ ዘንድ በጋራ እንትጋላቸው፡፡ ለተጨነቁት እንድረስላቸው፣ አለን እንበላቸው፣ ከስጋት እናላቅቃቸው፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa