በፍጻሜው ጦርነት-ክብርና ፍቅር ለትግራይ ወገናችን
ትግራይን በደንብ ከሚያውቁ ‘’የመሀል አገር ሰዎች ‘’አንዱ ነኝ፡፡በዚህም ራሴን እንደ ዕድለኛነት እቆጥራለሁ፡፡ከማይጨው እስከ ዛላንበሳ፣ከአብይአዲ እስከ ሽረ እንዳስላሴ፣ከአክሱም አስከ አድዋ፣ከአዲግራት እስከ አዲዳዕሮ፣ ከመቀሌ እስከ እንዳባጉና….አብዛኞቹን የትግራይ ከተሞችና ገጠሮች አውቃለሁ-ከ30 ዓመታት በፊት!!የትግራይን ምድርና የህዝቡን አኗኗር በአካል ከማወቄ በፊትም በት/ቤት ደረጃ አብረውኝ የተማሩ የምወዳቸው ጓደኞችና የማከብራቸው አስተማሪዎች (የትግራይ ልጆች) ነበሩ፡፡ከልብ የምወደው የጥ/ቤትና የሰፈር ጓደኛየ ገብረኪዳን ስዩምንና የ7ኛ ክፍል አስተማረየን ጋሸ ይህደጎ ኃይሉን መቼም ቢሆን የምረሳቸው አይደሉም፡፡ጋሽ ይህደጎ እጅግ ጨዋ፣መካሪና ጎበዝ ተማሪን አበረታች ስለነበር ተማሪዎቹ በተለየ ሁኔታ ክብርና ፍቅር ነበረን፡፡በት/ቤት ጓደኞቸና አስተማሪዎቸ ጨዋነትና እውነተኛነት ምክንያት ለትግራይ ተወላጆች የተለየ ክብር ኖሮኝ እንዳደኩ አስታውሳለሁ፡፡በዚህ ዓይነት ስነልቦና ውስጥ እያለሁ ነበር ትግራይን በአካል የማወቅ ዕድል የገጠመኝ፡፡በእርግጥም የአብሮአደግ ጓደኞቸና አስተማሪዎቸ ጨዋ ባህሪና እውነተኛነት ከትግራይ ህዝብ ባህሪ የተቀዳ መሆኑን ተረዳሁ፡፡እውነት ነው የምላችሁ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ጨዋና እውነት ነው ብሎ ለሚያምንበት ነገር ሟች ነው፡፡ጨዋነትና ለእውነት ሟችነት የትግራይ ህዝብ ሀብቶች ናቸው፡፡መዋሸት፣ማበል፣ማጭበርበር፣ በሰው ላይ ማሴርና ክፋት መስራት በትግራይ ህዝብ ዘንድ የተነወሩ ባህሪያት ናቸው፡፡የትግራይ ህዝብ ለሀገሩ ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅርና ‘’ለመሀል አገር ሰው ‘’የሚያሳየው አክብሮት ልብ ይነካል፡፡የትግራይ ጎረምሳ እጅግ ከተቆጣብህና ከተናደደብህ ‘’በቴስታ ‘’ከመሬት ይደባልቅህ ይሆናል እንጂ እንደዋልጌው ጌታቸው ረዳ የምርጥ ስድብ አተላ አይደፋብህም፡፡
እርግጥ ነው የትግራይ ልጆች አካባቢያቸውን ይወዳሉ፤ለትግራይም ከፍተኛ ፍቅር አላቸው፡፡ይህ ደግሞ የማንም ሰው ስውአዊ ባህሪ ነው፡፡እኔ ራሴ ለተወለድኩበትና ለአደኩበት አካባቢ የተለየ ፍቅር አለኝ፡፡አካባቢየን ስለወደድኩ ሌሎች አካባቢዎችን እጠላለሁ ማለት ግን አይደለም፣ለኢትዮጵያ ፍቅር የለኝም ማለትም አይሆንም፡፡እንደውም አገር የሚወደደውም የሚገለጸውም በአካባቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ኢትዮጵያን በእናት መስለህ የምትወደው ከሁሉም በላይ እናትህን ስለምትወድ ይመስለኛል፡፡የትeግራይም ህዝብ እንደዚህ ነው-አካባቢውን ይወዳል-አገሩንም ይወዳል!!
ይህ ሁሉ ግን ከ30 ዓመት በፊት የነበረ እውነት ነው፡፡ባለመታደል በዚህ ጨዋና ለእውነት ሟች፣ለወደደው ታማኝና ለሀገሩ ሟች በሆነው ህዝብ ውስጥ ትህነግ የሚባል አረም በቀለ፡፡‘’የሸዋ አማራ ስልጣናችንን ቀማን ‘’የሚል ቂም በቀል የነበራቸው የትግራይ ፊውዳል የባዕድ ባንዳዎች ልጆች ተጠራርተው በኋላ ቀሩ ስታሊናዊ ‘’የበሄር ጭቆና ‘’ባዕድ አስተሳሰብና ጥላቻ ተጠፍጥፈው በደደቢት በረሃ ተከሰቱ፡፡ከዚህ ጊዜ በኋላ ድሮም እንደየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በድህነትና በተዛባ አስተዳደር ይሰቃይ የነረው የትግራይ ህዝብ መከራ በረከተ፡፡ምንም እንኳ ይህ የትግራይ ህዝብ መከራ ቀማሚ ቡድን ‘’ የትግራይን ሪፐብሊክ እመሰርታለሁ ‘’በሚል ቅዠት ሱዳን ውስጥ ማኒፌስቶ ነድፎ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም በሀገሩ አንድነት በማይደራደረው የትግራይ ህዝብ ብርቱ ተቃውሞ ማኒፌስቶው ከጥቂት ወራት በላይ መቀጠል አልቻለም፡፡ያም ሆኖ ትህነግ የትግራይን ህዝብ ከመግደልና ከማጎሳቆል አልታቀበም፡፡በተለይ ዓላማውን በሚቃወሙና ኢትዮፕያን በሚወዱ ታላላቅ ሰዎች ላይ የጭካኔ ሰይፉን መዘዘ፡፡‘’ የትግራይን ህዝብ ለሸዋ አማራ የሸጡ፣የኢዲዩ አባላት፣የደርግ ሰላዮች…‘’እያለ አገር ወዳድ ተቃዋሚዎችን እየመረጠ በጭካኔ ገደላቸው፣ሰወራቸው፡፡የትገራይ ህዝብ በደስታውም ሆነ በመከራው ወቅት ከእጁ የማይለያትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዳያውለበልብ አሸማቀቁት፣በመጨረሻም ቡድኑ ሰፍቶ የሰጠውን ጨርቅ እንዲያውለበልብ ተገደደ፡፡ይህን የትግራይን ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ጽኑ ፍቅር ቀስ በቀስ ከሸረሸረና ከአዳከመ በኋላ ነበር የሀሰት ትርክትና ፕሮፓጋንዳ የበላይነቱን የያዘው፣በትውልድ መሀልም ክፍተት የፈጠረው፡፡በዚህ ሀሰተኛ ትርክቱና ፕሮፓጋንዳው ጸረ-ኢትዮጵያ አስተሳሰብና ጥላቻ አነገሰ፡፡ከሁሉም የከፋው ትርክትና ፕሮፓጋንዳው ‘’የትግራይ ህዝብና ወያኔ አንድ ናቸው ‘’የሚለው ነው፡፡ትህነግ ታሪክ ዘርዝሮ የማይጨርሰውን ግፍና በደል እንዲፈጽም ጉልበት የሆነውም ይህ መርዘኛ ፕሮፓጋንዳው መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
በት/ቤት ዘመኔም ሆነ ትግራይ ውስጥ እያለሁ በርካታ የትህነግ የፕሮፓጋንዳ በራሪ ወረቀቶችንና ቡክሌቶችን የማንበብ ዕድል አጋጥሞኛል፡፡በኢትዮጵያና በአማራ ህዝብ ላይ ያለው ጥላቻ፣የታሪክ ክህደቱና የባዕድ ባንዳነቱ ያስፈራኝ ነበር፡፡ትህነግን አምርሬ እንድቃወመው ያደረጉኝን ምክንያቶች ያወቅሁትም በዚያን ወቅት ነው፡፡ከአነበብኳቸው በራሪ ወረቀቶች መካከል እስካሁን በአዕምሮየ ተጽፈው የማሰታውሳቸው አሉ፡፡‘’አማራን በመጠራረግ ትግራይን ዳግማዊ ቬትናም እናደርጋታለን ‘’የሚለው አሁንም በአዕምሮየ ያቃጭላል፡፡ይህ ብቻ አይደለም፤‘’የአድዋ ድል የትግራይ ህዝብ እንጂ የኢትዮጵያ አይደለም ‘’ብሎ የጻፈውን አንብቤአለሁ፡፡እንደውም የምኒልክ ሰራዊት የትግራይ ህዝብ ጦርነቱን ከጨረሰው በኋላ ወደትግራይ መጥቶ ህዝብን ‘’ያበሳበሰና ድል የቀማ ወራሪ ነው ‘’ብሎ በድፍረት ታሪክን የካደ ቡድን ነው፡፡ከየአቅጣጫው ወደ አድዋ ዘምተው የጣሊያንን ቅኝ ገዥ ሰራዊት የበታተኑ የኢትዮጵያ ጀግኖችን ፣ ሌላው ቀርቶ በአድዋ ተራሮች ላይ ተአምር የሰሩ የኦሮሞ ፈረሶችን ሸምጥጦ የካደ ባዕድ ቡድን ነው፡፡‘’ጎጃም የዋሸራ ቅኔ የሚለው ከትግራይ ቀምቶ ነው ‘’ብሎ የሚያምን ነውረኛ ቡድንም ነው፡፡የኢትዮጵያን ጥሩ ጥሩ ታሪኮች ቀምቶ ለአንድ አካባቢ የሚሰጥ ያለበለዚያም የሚክድ ቡድን ነው፡፡የቡድኑ ፊታውራሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ‘’የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው? ‘’ያለህ ከህ ከሀዲ አስተሳሰቡ የመነጨ ነበር፡፡ ትርጉሙም የአክሱም ሀውልት የወላይታውም ፣የሲዳማውም፣ የሶማሌውም፣ የአማራውም፣ የኦሮሞውም ….ምኑም አይደለም ማለት ነው፡፡
አሁን ከብዙ ግፍና መከራ፣ታይቶ የማይታወቅ የሀገር ፈተና በኋላ እነሆ የትህነግ ጉልበት ዝሏል፡፡ትህነግ በአካል እንዳልነበረ ሊሆን ዋዜማው ላይ ይገኛል፡፡ትህነግ በጦርነት ተሸነፈ፣ቡድኑም ፈረሰ ማለት ግን አስተሳሰቡ ተሸነፈ ማለት አይደለም፡፡‘’ጦርነት ባህላዊ ጨዋታህ ነው፣አንተን የሚያሸንፍ ኃይል በምድር ላይ የለም፣ተራራ ያንቀጠቀጥክ የዓለም ጀግና ነህ… ‘’እያለ የገነባው ፋሽስታዊ ስነልቦና ችግር መፈጠር መቀጠሉ አይቀርም፡፡ጀርመኖች የሂትለር ናዚን አፍረስው አስተሳሰቡ ዳግም እንዳያንሰራራ በህግ ቢያግዱትም አስተሳሰቡ አሁንም እየተፈታተናቸው መሆኑ እውነት ነው፡፡እናም ትህነግን በጦርነት አሸንፎ የማፍረሱ ትግል በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ለውጆች ወደ ፍጻሜው ቢደረስም ትህነግ በህዝብ መካከል የፈጠረው ቁርሾ ቀላል አይደለም፡፡በነሱ ዘረኛና የጥላቻ አስተሳሰብ የተበከለው ‘’ ብሄረተኛ‘’ኩርፊያ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ከሁሉም በላይ ‘ህወኃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ‘’የሚለው አስተሳሰብ በትግራይ ህዝብ ዘንድ የተሸናፊነት ስሜት እንዳይፈጥር መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡የትግራይ ህዝብ አልተሸነፈም፣ተሸንፎም አያውቀም-ከትህነግ አፈና ነጻ ወጣ እንጂ!!ትህነግ ተሸንፎ ቢፈራርስም በውጭ አገር ሆነው ፈረንጅ በሰራው አሰውፋልት ላይ የሚንደባለሉ ጥቅመኞቹና ባዕድ ቅጥረኞቹ ህዝቡን ወደ ተሸናፊነት ቁጭት እንዳይነዱት ከባድ ስራ ይጠይቃል፡፡የተሸናፊነት ስነልቦና የትህነግ መሸነፍ የትግራይ ህዝብ መሸነፍ አስመስለው የሚሰብኩና የብሽሽቅ ፖለቲካ የሚያራምዱ የሌላ ብሄር ዘረኞችና የጥላቻ ነጋዴዎችም አደብ ይገዙ ዘንድ አስፈላጊው ሁሉ መደረግ አለበት፡፡የትገራይ ህዝብ ነጻ ወጣ እንጂ አልተሸነፈም፡፡እናም በፍጻሜው ጦርነት ለትግራይ ህዝብ ፍቅርና ክብር መስጠት፣ከችግርና ከጦርነት ስነልቦና በፍጥነት እንዲያገግም መርዳትና ለደህንነቱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡
ፀሐፊው ዓለምነው አበበ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ