ለትህነግ ሞት ሲያንሰው ነው
’’Why political parties die?’’(ለምን የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሞታሉ?)ብሎ ይጠይቃል አንድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድገትና አሟሟት ላይ የወጣ የጥናት ውጤት፡፡መልሱ አጭርና ግልጽ ነው-አዎ ፓርቲዎች ሟቾች ናቸው( Yes, parties are mortal) የሚል፡፡የፓርቲዎቹ አሟሟት ግን ውስብስብ ነው፡፡እርግጥ ነው ሟቾች ፓርቲዎች ብቻ አይደሉም፡፡ የተፈጥሮ ሰውም ሆነ በህግ የሰውነት ደረጃ የተሰጠው ማንኛውም ‘’ህጋዊ ሰው‘’/ድርጅት መሞታቸው አይቀርም፡፡ መወለድ፣ ማደግ፣ ማርጀትና መሞት የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡በህግ ‘’የሰውነት ደረጃ የተሰጠው ሰው ‘’እንዴት ይሞታል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ‘’ህግ የሰውነት ደረጃ የሰጠው ‘’ ማን ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡
የህግ ባለሙያዎች እንደሚሰጡት ብያኔ ህግን መሰረት አድርጎና ህጋዊ ዕውቅና አግኝቶ የሚቋቋም ማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኃማኖታዊ ድርጅት/አካል ህጋዊ ሰው ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ሲያጠፋ ይወቀሳል፣ ይከሰሳል፣ ይቀጣልም፡፡ ከትልቁ ህጋዊና ፖለቲካዊ ሰው ብንጀምር ደግሞ መንግስትን አንድ ማለት እንጀምራለን-መንግስት በህገ መንግስት መሰረት የሚቋቋም ፖለቲካዊ ድርጅት/ህጋዊ ሰው ነውና!!በፖለቲካዊ ምክንያት የሚቋቋሙት ሌሎች ድርጅቶች መጥቀስ ካስፈለም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀዳሚ ናቸው፡፡
ሁለቱም የሰው ዓይነቶች የተፈጥሮን ህግ ተከትለው ይወለዳሉ፣ያድጋሉ፣ያረጃሉ፣ ይሞታሉ፡፡ይህም ሆኖ የዕድሜ ዘመናቸውና አሟሟታቸው የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡እንደውም አንዳንዶቹ ‘’ህጋዊ ሰዎች ‘’የተቋቋሙበትን ዓላማና ተልዕኮ በየጊዜው በማደስ ከተፈጥሮ ሰው የበለጠ ዕድሜ ሊኖራቸው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ሁለቱ የሰው ዓይነቶች አፈጣጠራቸውም ቢሆን የተለያየ ነው፡፡የተፈጥሮ ሰው በአምላኩ የተፈጠረ ሲሆን ህግ ሰው ያደረገው ግን ሰው ራሱ በአጸደቀው ህግ የፈጠረው ነው፡፡
አሁን ስለ ‘’ህጋዊ ሰዎች ‘’ በተለይም ስለፖለቲካ ድርጅቶች ሞትና አሟሟት እንመልከት፡፡የትህነግን ሞት አይቀሬነት የምንረዳውም በዚህ ዓጠቃላይ እውነት ውስጥ ስለሆነ!!በፖለቲካ ፓርቲ ስርዓት የሚተዳደሩ አገሮች ታሪክ ሲመረመር ብዙ ፓርቲዎች ተፈጥረው መሞታቸውን እንረዳለን፡፡በተለይ ደግሞ ‘’አናሳ ፓርቲዎች‘’ (shelf political parties)ለፈጣን ሞት የቀረቡ ናቸው፡፡ አሟሟታቸው ደግሞ የተለያየ መልክ አለው፡፡በጣም ብዙዎቹ ፓርቲዎች ተወልደው የሞቱት በያዙት ዓላማ/ፖሊሲ ምክንያት ነው፡፡በአንድ ወቅት የህዝብ ዋነኛ አጀንዳ በሆነ ጉዳይ ላይ ተመስርተው ይቋቋሙና የወቅቱ የህዝብ ዋነኛ አጀንዳ የሆነው ጉዳይ ሲፈታ አብረው ይሞታሉ፡፡አንዳንዶቹ ደግሞ ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ይሆኑና በህዝባዊ አመጽ ወይም በህግ ድንጋጌ እንዲሞቱ ይደረጋል፡፡ሌሎቹ ደግሞ ደጋፊና አባል በማጣት በፓርቲው አባላት ውሳኔ እንዲሞቱ ይደረጋሉ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወልደው፣አድገውና አርጅተው ወይም እንደተወለዱ ለዕድገትና ለአርጅና ሳይበቁ ይሞታሉ የሚል አጠቃላይ ግንዛቤ ቢኖርም ሞትን እያሸነፉ ረጅም ዘመን የሚኖሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አሉ፡፡በዚህ ረገድ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ የኖሩት የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካው ዴሞክራቲክ ፓርቲ (በ1850ዎቹ የተመሰረተ) እና የእንግሊዙ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ለረጅም ዘመን በህይወት የመኖራቸው ብቻ ሳይሆን እየወደቁና እየተነሱ አገር የማስተዳደራቸው ምስጢር አንድና ግልጽ ነው-ወቅትንና ተለዋዋጭ የሆነውን የህዝብ ፍላጎትን መሰረት አድርጎ የፖሊሲ ለውጥ (Adaptability of party policy) ማድረግ፡፡
በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለውን የፓርቲዎች ታሪክ ብንመረምር በህይወት ካሉት ይልቅ የሞቱት በብዙ እጥፍ የሚበልጡ ናቸው፡፡የሞታቸውን ተጨባጭ ምክንያት ለማወቅ ጥልቅ ጥናት ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ቢታወቅም የብዙዎቹ ሞት ምክንያት የራሳቸው ድክመት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡አንድም የአንድን ወቅት የህዝብ አጀንዳ ተከትለው ስልጣን ለመያዝ ተመሰርተው ህዝብን አስተባብሮ መምራት ባለመቻል፣የባዕድ ርዕዮተ ዓለም ተሸካሚ በመሆንና የህዝብ ድጋፍ በማጣት፣በብሔር ፖለቲካ ሽፋን ስልጣን ለመያዝ፣በሀገርና በህዝብ ጥቅም ላይ የጋራ አቋም ይዞ በልዩነት ላይ ሰላማዊ ትግል ከማድረግ ይልቅ እርስ በረስ የመጠላለፍ ፖለቲካዊ ሴራ፣በመንግስታት ተጽዕኖ…በመሳሰሉት ምክንያቶች ሞታቸውን ያወጁ ናቸው፡፡ብዙዎቹ ፓርቲዎች/የፖለቲካ ድርጅቶች ወቅትን፣የሀገርንና የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርገው ስር ነቀል የፖሊሲ ለውጥ (Radical shifts of their policy positions) ከማድረግ ይልቅ ሲወለዱ በቆሙበት አስተሳሰብ ላይ ተገትረው መቅረታቸው ግልጽ ነው፡፡አሁን ‘’በህይወት ‘’ያሉትም ቢሆኑ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መሞታቸው የማይቀር ነው፡፡በኔ እምነት እንደአስፈላጊነቱ የፖሊሲ ለውጥ (Adaptability of party policy)በማድረግ ብዙ ዘመን በህይወት ይኖራሉ ብየ የማሰባቸው ፓርቲዎች ከሁለትና ከሶስት አይበልጡም( ብልጽግናና ኢዜማ ግንባርቀደሞች ናቸው)
ከአጠቃላዩ የፓርቲዎች ህይወትና ሞት አንጸር ሲታይ ወቅት የሞት ፍርድ ያሳረፈበት ትህነግ ነው፡፡ትህነግ በባዕድ ርዕዮተ-ዓለም የደነቆረ፣ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን የሚንቅና የሚጠላ፣ስር ነቀል የፖሊሲ ለውጥ (Radical shifts of its policy positions) ለማድረግ ተፈጥሮው የማይፈቅድለት እጅግ ዘረኛና ሴረኛ ቡድን ነው፡፡ይህ ቡድን እንኳንስ በአዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ የፖለቲካ መድረክ ሊቀጥል ቀርቶ እስከዛሬ መኖሩም የሚገርም ሟች ድርጅት ነው፡፡በአጭሩ በዚህ ወቅት ለትህነግ ሞት ሲያንሰው ነው፡፡ለምን ቢባል፡-
-ትህነግ ‘’ኢትዮጵያን በማፍረስ ታላቋን ትግራይ ሪፐብሊክ እመሰርታለሁ ‘’የሚል የመታገያ መኒፌስቶ ያወጣ፣ዛሬም ከ50 ዓመታት በኋላ ጭራሽ ‘’ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ፣ከሰይጣንም ጋር እተባበራለሁ‘’ብሎ ያወጀና ለጥፋት የተሰማራ ቁሞ ቀር ቡድን ነው፡፡
-ትህነግ ገና ከጅምሩ በዘረኝነትና በቂም በቀል የተለወሰ የብሄረተኝነት ፖለቲካን እያራመደ፣ ሌላውን ህዝብ በተለይ የአማራን ህዝብ ጠላት ብሎ በመፈረጅ የተፈጠረ ቡድን ነው፡፡ዛሬም ‘’በአማራ ህዝብ ላይ የማወራርደው ሂሳብ አለኝ ‘’ያለ፣በጥላቻና በሴራ የቆረበ አጥፊ ቡድን ነው፡፡
-ትህነግ ‘’ጠላት ‘’የሚለውን ህዝብ/አካል በጉልበት ካልደመሰሰ በስተቀር ተቻችሎና ተከባብሮ በአንድነት መኖርን አጥብቆ የሚጠላ ቡድን ነው፡፡ዛሬም በዚህ ክፉና የአብሮነት ጠንቅነት አቋሙ ፀንቶ አንዱን ህዝብ ከሌላው ጋር ለማፋጀት እንቅልፍ ያጣ የሰይጣኖች ቡድን ነው፡፡
-ትህነግ ‘’እኛና እነሱ ‘’በሚል የባዕድ ርዕዮተ ዐለም የተመሰረተ፣ዛሬም ‘’ጠላትን እቀብራለሁ ‘’የሚል ጨካኝና ዋልጌዎች የሚዘውሩት፣ለዘመናዊ የፓርቲ ፖለቲካ ውድድርም እንቅፋት የሆነ ኋላቀር ድርጅት ነው፡፡
ታዲያ ይህ ኋላቀርና ዘረኛ ቡድን እንደምን ከሞት ያመልጣል?ሰው ሳይሆን ዘመን ራሱ የሞት ፍርድ የሚበይንበት ነውረኛ ቡድን ነው፡፡እንደውም ለትህነግ ሞት ሲያንሰው ነው፡፡
@ዓለምነው አበበ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ