መንግስት እና ህዝብ ህገ መንግስቱን በኃይል ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን አይታገሱም

መንግስት እና ህዝብ ህገ መንግስቱን በኃይል ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን እንደማይታገሱ፤ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንዳሉት፥ ሰሞኑን በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን የተሞከሩት የአመፅ እንቅስቃሴዎች ዋና ተልእኮ ህገ መግስታዊ ስርአቱን በኃይል ማፍረስ ነው።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን፥ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 30 ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ከሃላፊነት እና ግዴታ ጋር ይሰጣል ብለዋል።

ባለፉት ሁለት እና ሶስት ቀናት በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ጥቂት ስፍራዎች፥ የተሞከሩት ሰልፎች ከህገ መንግስቱ አንፃር ሲመዘኑ ህገ ወጥ ናቸው።

የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትር እና የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ምክትል ሊቀ መንበር ወይዘሮ አስቴር ማሞ፥ በኦሮሚያ ክልል ሊካሄዱ ታስበው የከሸፉት ሰልፎች ስርአትንና ህግን ያልተከሉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

ህግ መንግስቱ ላይ እንደተደነገገው ሰላማዊ ሰልፈኞች ከጦር መሳሪያ የራቁ መሆን አለባቸው።

በከሸፉት ሰልፎች የሆነው እና የተሞከረው ግን ከዚህ የተቃረነ መሆኑን መንግስት ይገልጻል፤ በሰልፍ ስም የተሞክሩት የአመፅ እንቅስቃሴዎች ግብ እና ተልዕኮ ስርአት አልበኝነትን መፍጠር እንደነበር በመጥቀስ።

እነዚህ ሰልፎች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመናድ በሃይል እና በጉልበት ስልጣን ለመቆጣጠር የተደረገ እንቅስቃሴ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን እና የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ይገልጻሉ።

ሀገሪቱን ወደለየለት ብጥብጥ በማስገባት ማቆሚያ የሌለው መተላለቅ የመፍጠር ግብ እንደነበራቸውም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ የተናገሩት።

ከዚህ ሀገራዊ ሰላምን የማናጋት ህዝብንም ለስጋት እና አለመረጋጋት የመዳረግ ሙከራ ጀርባ፥ ኢትዮጵያ የምትባል ጠንካራ ሀገር ማየት የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ይህን መሰሉ ሴራም ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር በመመሳጠር የተቀነባበረ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህን መመከት የሚያስችል ስራ እየተሰራም ነው ብለዋል።

ወይዘሮ አስቴር ማሞ በበኩላቸው፥ እነዚህ ሃይሎች እንደገና ለመነሳት እየሞከሩ ያሉ የሻዕቢያ ተላላኪዎችና አሸባሪው ኦነግ መሆናቸውን ነው ያነሱት።

መንግስት እንደሚለው ለመካሄድ የሞከሩት ህገ ወጥ ሰልፎች ባለቤት ያላቸው እና ጥርት ያሉ ጥያቄዎችን ያነገቡ ሳይሆኑ፥ ሃገራዊ ትርምስ ፈጥሮ በንፁሃን ዜጎች ደም ህገ መንግስታዊ ስርአት መናድን ያለሙ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ናቸው።

ይሁን እንጅ እነዚህ እንቅስቃሴዎች እውን ሳይሆኑ በመንግስትና በህዝብ ጥረት መክሸፋቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

መንግስት ካሁን ቀደም በህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ለተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ያነሱት ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፥ በዚያው መጠን የህዝቡን እና የሀገሪቱን ህገ መንግስት ለማስጠበቅ እንደማያወላውልም አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻርም የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ የሚያውኩ እና በህጋዊ ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ከዕኩይ ተግባራቸው ለማስቆም እና ሰላም የማስከበር ስራውን መንግስት ይሰራልም ነው ያሉት።

ጥቂትም ቢሆን ህብረተሰቡ በየትኛውም መንገድ የህገ ወጥ ድርጊቲቱ ሰለባ እንዳይሆን ማስተማር የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ሆኖ እየተከናወነ መሆኑም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነስቷል።

ከህዝቡ ጋር ተከታታይ ውይይት ማካሄድ እና ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠትም ዋና የመንግስት ትኩረት ሆኖ ተጠቅሷል።

ህብረሰተቡም ህግን በማስከበሩ እንቅስቃሴ ለመንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።




አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman