“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ


“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

I. መግቢያ
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሰኔ 3 እስከ 5 ያካሄደዉን አስቸኳይ ሰብሰባ አጠናቋል።
ህወሓት/ኢህአዴግ 17 ዓመቱ የትጥቅ ትግልም ሆነ ሩብ ክፍለ ዘመን ባስቆጠረው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ትግል ምዕራፎች ሁሉ ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በመሆን ባደረግነው ትግል በርካታ ድሎችን እየተጎናፀፍን እዚህ ላይ መድረስ ችለናል። 43 ዓመታት የድልና የፅናት ጉዟችን ስኬት ምንጭ የጠራና ብቁ አብዮታዊ መስመር ይዘን የዘለቅን መሆኑ ነው። ይህንን መስመር በፅናት ጨብጦ በፅናት ታግሎ የሚያታግል ድርጅት ባለቤት ስለሆንም ነው። ባለፉት 27 ዓመታት በአጠቃላይ፣ ባለፉት 17 የተሐድሶ ዓመታት ደግሞ በተለይ ዙርያ መለስ መሰረታዊ ለውጥ ማስመዝገብ ችለናል። ሃገራችን ኢትዮዽያ የነበረችበት እጅግ አስፈሪ የመበታተንና የማሽቆልቆል ጉዞ ተገቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገርና ስምና ክብር ከፍ ብሎ እንዲጠራ ኢህኣዲግ እልህ አስጨራሸ ትግል አካሂዷል። በተደረገዉ ትግል የሃገራችን ህዝቦች የመልማት እኩል ዕድል ያረጋገጠ ስርዓት ተገንብቶ ህዝቦችን በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ረገድ ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ ዉጤት ለማረጋገጥ ተችሏል። በእርግጥም አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ሃገራችንን ከጥፋት የታደገ፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠበት አዲሲቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ያደረገና ለወዲፊትም የሃገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ መሆኑ የእስከአሁኑ ትግላችን ያረጋገጠው እውነት ነው።
ይኸ ተዓምር የፈጠረና የሃገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ የሚያስችል ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አደጋ ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ እንዲፈጠር ከምንም በላይ የመሪ ድርጅታችን ኢህኣዴግ አመራር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህርይው እየተሸረሸረ በከፋ የጥገኛ ዝቅተት አረንቋ ውስጥ በመዘፈቁ መሆኑን ድርጅታችን ኢህአዴግ በሚገባ የተነተነዉ ጉዳይ ነዉ። ይሁን እንጂ ይህንን ፈተና በሚገባ ለማለፍ ሲባል በድርጅታችን የተጀመረዉ በጥልቅ የመታደስ እንቅስቓሴ ኣሁንም ቢሆን በሚፈለገዉ ደረጃ ሊሳካ አልቻለም።
ይህንን መነሻ በማድረግ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በወሰናቸዉ ዉሳኔዎች በሃገራችንና ክልላችን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በቀጣይ የትግል አቅጣዎቻችን ላይ በዝርዝር በመውያየት ውሳኔዎች አሳልፏል።

II. ውሳኔዎች
. የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግንቦት 28/2010 . ባካሄደዉ አስቸኳይ ሰብሰባ የኢትዮ-ኤርትራን ግጭት በሰለማዊ መንገድ ለመፍታትና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አስመልክቶ በህወሓት ስራ አስፈፃሚ የቀረበለት ሪፖርት በዝርዝር በማየት የሚቀጥሉትን ውሳኔዎች አሰልፏል።
1. ከምንም ነገር አስቀድሞ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሊያየው ይገባ የነበረዉ ጉዳይ የኢህአዴግ ምክር ቤት በመጋቢት /2010 . ያስቀመጠዉን ወሳኔና ግምገማ መሰረት በማድረግ በድርጅታችን በግልፅ እየታየ የመጠዉን መሰረታዊ የአመራር ብልሽትና ያስከተለዉን ጉዳት፣ እንዲሁም ባለፈዉ የተጀመረዉ በጥልቀት መታደስ የደረሰበት ደረጃን በጥልቀት በመገምገም በሃገራችን ዋነኛ ችግር ላይ ትኩረት አድርጎ ማየት አለመቻሉ አንድ መሰረታዊ ጉድለት ነው።
2. የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ ማየት የነበረበት ሌላ መሰረታዊ ጉዳይ አሁን ገጥሞን ላለው መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ላይ ትኩረት አድርጎ መወያየት መሆን ሲገባው ችግሩ ባስከተላቸው ውጤቶችና ለጊዚያዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ መስጠቱ አንድ ሌላ ጉድለት እንደ ሆነና፣ ዘለቂው መፍትሔ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችን በግልፅ የለያቸውን የልማት አቅምቻችን ማለትም መላው ህዝባችን፣ መንግስትና የግል ባለሃብቱን በማደራጀት ርብርብ እንዲያደርጉ መቻል ላይ ያለብን ችግር ላይ ትኩረት ስጥቶ መውያየት አልቻለም።
3. እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ጉድላቶች እንደ ተጠበቁ ሆነው ስራ አስፈፃሚው የኢትዮጵያና የኤርትራን ጉዳይ አስመልክቶ የወሰነው ውሳኔ በመሰረቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ በኢህአዴግ የሚመራዉ መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም በአጠቃላይ ለሁለቱ ሃገራት ወንድማማች ህዝቦች በተለይ ሲባል ስምምነቱን ያለቅድመ ሁኔታ በመቀበል ህዝባችንና መላዉ አበላችንን በማወያየትና በማሳመን እንድሁም ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ከጎኑ በማሳለፍ ለተግባራዊነቱ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት 18 ዓመታት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ አልተቻለም። ስለሆነም የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈዉ ዉሳኔ በመሰረቱ ከሰላም ፖሊስያችን ጋር የተጣጣመ መሆኑን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ዉሳኔ መተላለፉ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ደምድሟል።
አፈፃፀሙን በሚመለከት ግን ሃገራችን ከሌሎች ጎረቤት ሃገራት ጋር ከሏት የአዋሳኝ ድንበር ጉዳዮች አንፃር ጭምር እጅግ ከፍ ያለ ትርጉም ያለዉ በመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባዉ አፅንኦት ሰጥቶ ተውያይቷል። ከዚህ ጋር በተያየዘ በኢትዮ-ኤርትራ አዋሳኝ አከባቢዎች የሚኖረው ህዝብና ሚሊሻ ላለፉት 20 ዓመታት ከኑሯቸዉና ከሥራቸው ተፈነቅለዉ የሃገራችንን ልዓላዊነትና ህገ-መንግስታችን ለማሰከበር ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን በመቆም ለሳዩት ቆራጥነትና ከከፈሉት የማይታመን መስዋዕትነት የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ያለዉን ክብርና አድናቆት እየገለፀ ድርጅታችን ኢህአዴግና ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን በቂ ድጋፍ ሊያገኙ እንዲሚገባ ወስኗል።
4. የኢህኣዴግ ስራ ኣሰፈፃሚ ኮሚቴ አሁን የገጠመንን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት እንዲቻል ከመንግስት የልማት ድርጅቶችን መካከል ቴሌ፣ ኤሌክትሪክ ማመንጨዎች፣ ሎጀስቲክስና የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ከፍተኛዉ ድርሻ በመያዝ የግል ባለሃበቶችን ለማሳተፍ እንዲሁም የቀሩትን የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ የወሰነዉ ውሳኔ ከፕሮግራማችንና ፖሊስዎቻችን ጋር የማይጋጭ፣ ባለፉት ጉባኤዎቻችን እየተወሰነ የመጣና ወቅታዊ መሆኑን በማረጋገጥ ተቀብሎታል። ይሁን እንጂ ኣፈፃፀሙ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲዳረግና ልማታዊ ዴሞከራሲያዊ መስመራችንንም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መከናወን እንዳለበት አፅንኦት ሰጥቶበታል።
5. በኢትዮ-ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ጉዳይም ሆነ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያየዘ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ኢህአዴግ ምክር ቤት ሳይቀርቡ፣ አጋር ድርጅቶች ሳይሳተፉበት እና የሚመልከታቸው አካላት በዝርዝር ሳይወያይበት እንደመጨረሻ ውሳኔ ተወስዶ ለህዝብ ይፋ መደረጉ አንድ ጉድለት እንደሆነ ማእከላዊ ኮሚቴዉ ደምድሟል።
6. የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከዳር እስከዳር በከፍተኛ ሃገር ፍቅር የተሳተፉበት እና መስዋእት የከፈሉበት ጉዳይ በዝርዝር ሳይወያዩበት እና በቂ መተማመን ሳይደረስበት በሚዲያ ይፋ መግለጫ መሰጠቱ ህዝባችን ላይ ቅሬታ፣ ቁጣና መደነጋገር የፈጠረ በመሆኑ አንድ ሌላ ጉድለት ነው።
. የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በጥልቀት ከተወያየባቸው ጉዳዮች አንዱ አሁን ያለንበት ክልላዊ እና ሃገራዊ ሁኔታ እንዲሁም ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎች የሚመለከት ነው። በኢህኣዴግ ደረጃም ሆነ በህወሓት ካለፉት አመታት ጀምሮ ልማታዊ መስመራችን እና በህገመንግስታችን ላይ እያጋጠመ ያለዉን ችግር ሲገምግም ቆይቷል። ይሁን እንጂ የችግሮቹ ስፋትና ትርጉም በኢህአዴግ ደረጃ በጥልቀት መገምገም እንዳለበት በመግባባት ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።
1. የኢህአዴግ ምክር ቤት በመጋቢት 2010 ባስቀመጣቸው ውሳኔዎች ድርጅታችንን ከአደጋ ለማዳን እንዲቻል የለየናቸው ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸው በጥብቅ ድስፕሊን እና ተጠያቅነት እንዲተገበሩት ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጧል። በዚህ ረገድ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴው የደረሰበት ደረጃ በኢህአዴግ እንዲገምገም የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።
2. በዴሞክራሲ ሀይሎች እና በጥገኝነት መካከል የሚደረገው ቀጣዩ የትግል ምእራፍ በዋናነት በዴሞክራሲ እና በልማት ዙርያ በሚለኮስ ንቅናቄ ማሕበራዊ መሰረታችን እና ከልማታችን ተጠቃሚ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት የተደራጃ ትግል ነው። ይህን ለማድረግ እንዲቻል መላው ህዝባችን እና አባላችን የምንገኝበትን መድረክ ባህሪ መነሻ በማድረግ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በሃገር ደረጃ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ትግል በቁርጠኝነት እንዲረባረብ ወስኗል።
3. በአሁኑ ወቅት በኢህአዴግ ደረጃ እየተደረጉ ያሉ የኢህአዴግን ህገ-ደንብ እና ተቋማዊ አስራር ያልተከተሉ የአመራር ምዳባዎች እንዲታረሙ የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ይጠይቃል።
4. ለደርጅታችን ነባር አመራሮች እውቅና እንዲሰጥ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ወስኗል።
5. በሃገራችን ህገ መንግስት በሚገባ መልስ የሰጠባቸው የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎችን ፈደራላዊ ስርዓታችን በመፃረር እና የህዝባችን ክብር በሚነካ መልኩ በሀይል እና በተፅእኖ የትግራይ እና ህዝብ አድነት እና ሰላም ለመረበሽ እየተደረጉ ያሉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሶች ህወሓት ከህዝቡ ጋር በመሆን በፅናት ለመታገል ወስኗል።
6. የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ የአብዮታዊ ዴሞከራሲያዊ መስመራችን አስተማማኝ ደጀን በመሆን ትግላችንን የሚያጠናክር እና እንደ ካሁን ቀደሙ በመሰመራችን ዙርያ ጠንካራ ርብርብ እንዲደረግ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ወስኗል።
7. ከህዝባችን ጋር ባለፉት ጥቅት ወራት ባካሄድናቸው መድረኮች በርካታ ችግሮች እንዳሉ ተገንዝበናል። ድርጅታችን የነዚህ ችግሮች መነሻ እንዲሁም የመፍትሔ አቅጫጫ በግልፅ አስቀምጦ በተግባር ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሌት ተቀን ርብርብ ለማድረግ ወስኗል።
8. ህዝባችን መሪ ድርጅቱ እንዲታደስ በተለያዩ መድረኮች ያደረገዉ ተሳትፎ እና ትግል ልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊ ባህሪውን ጠብቆ እንዲሄድ ላረገው አስተዋፅኦ ማእከላዊ ኮሚቴው አድናቆቱን እየገለፀ፤ በቀጣይም ቢሆን ትግሉን በተደራጀ መልኩ እንዲቀጥል ጥሪውን ያቀርባል። በዚህ አጋጣሚ ሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ ተከትለው አማራጭ ሃሳብ ከሚያራምዱ ሀይሎች ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት መግለፅ ይወዳል። ይሁን እንጂ ህወሓት እና የትግራይን ህዝብ ለማዳከም እና ለመምታት በተለያዩ መንገዶች ፀረ ትግራይ ህዝብ እና ፀረ ህወሓት እንቅስቃሴ የሚያድርጉ የውስጥም የውጭም ሀይሎች ህዝቡ አምርሮ እንዲታግላቸው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።
9. ወቅታዊ ሁኔታዉን በፍጥነት ለማየት እና ለመገምገም የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ እና ምክር ቤት አስቸኳይ ሰብሰባ እንዲጠራ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።

ህገ መንግስታችንና ህገ መንግስታዊ ስርአታችንን ለማጠናከር እንረባረብ!!
ዘለአለማዊ ክብርና ሞጎስ ለትጉሉ ሰማእታት!!
የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ
ሰነ 06/2010 .
መቐለ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa