ህወሃት- ከባሩድ ስካር መውጣት የተሳነው ሽብርተኛ
የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን ያህል ታላቅና ገናና ታሪክ ያላት ሀገር እውነታ ሳይገባው እንዳሻው መምራት የቻለ የዘመኑን ትውልድ በማሸበር ከፍተኛ ሀገራዊ ውድመትና ተቋማዊ ምስቅልቅል የፈጠረ መጥፎ ፖለቲካዊ ክስተት ነው፡፡ ሀገሪቱንና ህዝቦቿን አብዝቶ በመጥላትና በመፀየፍ ፖለቲካዊ ግቡና አላማውን የስብስቡን አባላት ሆድና ሆድ ብቻ አድርጎ የተነሳው ፋሽስታዊው ህወሃት ኢትዮጵያንና ዜጎቿን ለማሳነስና ለማቆርቆዝ የሚያስችለውን ሀሉን አቀፍ የጥፋት እንቅስቃሴ ያለገደብና ያለአንዳች ሀፍረት በድፍረት ሲፈፅም ቆይቷል፡፡
በሚከተለው የብሔር አክራሪነትን መሰረት ባደረገ ሰንካላና የይስሙላ ፌዴራሊዝም የሴራና የአፈሙዝ የአፈና ፖለቲካ ከባድ በሽታ ሆኖ የተጫነባትን ታላቅ ሀገር ጥቂት አባላቱን ለማበልጼግ እንዳሻው ከአቅሟ በላይ ሃብት ንብረቷን ሲዘርፍና ሲመዘብር ሀገሪቱንና ዜጎቿን ለማይገባቸው ውስብስብ ችግርና ሰቆቃ ሲዳርግ ቆይቷል፡፡ መዝረፍና ማጥፋት እንጂ መልካም ነገር የማይሆንለት የህወሃት አገዛዝ በሀገሪቱ ስልጣን ላይ በቆየባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ እያንዳንዱ ቀን ለዜጎች ጸጋና በረከት ሳይሆን ሰቆቃና እርግማን እንዲሆን በማድርግ የብዙዎች ቤት በሃዘን እንዲወድቅ አድርጓል፡፡
በሚመለከቱትም ይሁን በማይመለከተው በሁሉም ሀገራዊ ጉዳይ እንዳሻው መርህ አልባ በሆነ አግባብ ዘልቆ በመግባት መንግስታዊ ሸክም በመሆን በቆየባቸው ረጅም የስልጣን ዓመታት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከነበሩባት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የቁዩና ወቅታዊ ችግሮች በዜጎቿ ጥረት መሻገር እንዳትችል በማድረግ በተቃራኒው ተቋማዊ አቅመ ቢስነት በማንገስ የጥቅም ትስስር በመፍጠር ጥቂቶች ብቻ ተቀናጅተው በዝርፊያ መክበር የቻሉበትን ፖለቲካዊ ስርዓት እውን አድረጓል፡፡ ይህን ጥቂቶችን በማክበር በርካቶች ተረስተውና ተነፍገው የቀጠሉበትን ህውሃታዊ መንግስታዊ ስርዓት በስመ ዴሞክራሲ ሲያሻው ደግሞ ልማታዊ በሚሉ ማሽሞንሞኖች እያጀበ ውስጣዊ አንድነታችን ጭምር እንዲናጋ ሲያሴር ቆይቷል፡፡
ህዝቧን ለሽብርና ለከፋ ድህነት ዳርጎ ሀገሪቷን አራቁቶ ሲዘርፍ የዘለቀው ዘራፊው የህወሃት ቡድን የኢትዮጵያን ሃብት ከዜጎቿ ነጥቆ ለጥቂቶች ብቻ መጠቀሚያ አድርጓታል፡፡ በዚህም ዘራፊው የህወሃት ቡድን ዜጎችን ለከፋ ችግር ዳርጎ ቆይቷል፡፡
ፋሽስታዊው የህወሃት ለስልጣን ካለው የተዛባ አመለካከትና ከፍተኛ ጉጉት መነሻ በስልጣን በቆየባቸው ጊዜያት በሀገሪቱ ያስከተላቸው ውስብስብ ችግሮች አልበቃ ብሎት በህዝብ ከፍተኛ ግፊትና በፖለቲካዊ ትግል ተሸንፎ ያጣውን ስልጣን በኃይል ለማስመለስ ካልሆነም ሀገር ለማፍረስ በሚል ከንቱ እሳቤ አሁን ላይ ከፍተኛ ሀገራዊ እልቂት እንዲከሰት የሞት ሽረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይ የዚህን ቡድን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ በመጣው ሀገራዊ ሁለንተናዊ ለውጥና በተፈጠረው ህዝባዊ መነሳሳት መፍጠር የተቻለውን ሀገራዊ አቅም እንዲመክንና ሀገራዊ አንድነትን በሚንድ አላስፈላጊ ጦርነት ከፍቶ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል፡፡
ህወሃት ወለድ ሀገራዊ ችግሮቻችን በመጠንም ይሁን በይዘት የቆይታውን ያህል እየበዙና እየገዘፉ ከመምጣታቸውም በላይ በጣም ተወዝፈው የተከማቹና ውስብስብ ችግሮች በመሆን ዜጎችን ለከፋ ጉዳት የዳረጉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ያጋጠሙ ሀገራዊ ችግሮች አድማሳቸው በውስጥ የታጠረ ብቻ ሳይሆን በርካታና አዳዲስ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ሀገራችን ላይ ለማድረስ ፍላጎት ላላቸው ሀገራትና ተቋማት በር የከፈተ ውጫዊ ተግዳሮቶችን የያዙ ናቸው፡፡
ሀገራችንና ዜጎቿ አሁን ባሉበት ሁኔታም ህወሃት ወለድ ሀገራዊ ችግሮችና እራሱ የህወሃት ቡድን ዋነኛ ፈተናዎቻቸው ሊሆኑ ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያን አሸባሪውን ህወሃት ለማስወገድና ህወሃት ካመጣባቸው ውዝፍና ውስብስብ ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ችግሮች ለመላቀቅ እያደረጉ ያለው ትግል ከባድና ሀገር የማስቀጠል የህልውና ጉዳይ ሊሆን ችሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን አገር ማፍረስ ትልሙ ያደረገውንና ዛሬም ከባሩድ ስካር መውጣት ያልቻለውን የሽብር ቡድን ጠራርገው ለማስወገድ በጀመሩበት አንድነት ተጠናክረው ህልውናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች፡፡
በረውዳ ጀማል(PP)
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ