በሕግ የበላይነት ሥር የማይተዳደር አገር የሕገወጦች መጫወቻ ይሆናል!

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በአንክሮ የሚከታተል ማንኛውም ሰው በርካታ ግራ የሚያጋቡና አወዛጋቢ ጉዳዮች ይገጥሙታል፡፡ ዋና ዋና በሚባሉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስኮች ውስጥ በየዕለቱ የሚያጋጥሙ አደናጋሪ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መነጋገርና የጋራ መግባባት መፍጠር ካልተቻለ የአገሪቱም ሆነ የሕዝቡ ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡ በአንድ አገር ሰላምና መረጋጋት የሚኖረው ሕዝብ በነፃነት መኖሩ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ነፃነት የሚገኘው ደግሞ በሕግ የበላይነት ሥር መኖር ሲቻል ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መንግሥት በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ብቻ እንዲመሠረት፣ የፀጥታ ኃይሎች ለማንም ወገንተኛ ሳይሆኑ ሕግ ብቻ እንዲያስከብሩ፣ የመንግሥት ተሿሚዎች ሥልጣናቸው በሕግ የተገደበ እንዲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊና ሰላማዊ ሆነው ዓላማቸውን እንዲያስፈጽሙ፣ የአገሪቱ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው እንዲረጋገጥ፣ መደራጀትና ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ባህል እንዲሆን፣ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ለማድረግ የሚፈልጉ ጉልበተኞች በሕግ እንዲዳኙ፣ ወዘተ. ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲጣስ ግን ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡፡ የዜጎች ደኅንነት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ አምባገነንነት ይንሰራፋል፡፡ ይህ ደግሞ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አይመጥንም፡፡
የሕግ የበላይነትን የማይቀበል በሰላም መኖር አይችልም፡፡ ሕግ የማያከብርና የማያስከብር መንግሥት ራሱን ለአደጋ ከማጋለጡም በላይ አገርንና ሕዝብን ትርምስ ውስጥ ይከታል፡፡ ዜጎች የሚያዳምጣቸው ካጡ ሕግ እንዳልተከበረ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የፍሕት መጥፋት የሕግ አለመከበር ውጤት ነው፡፡ ሙስና ተንሰራፍቶ አገር እየተዘረፈች ከሆነ የሕግ የበላይነት ሳይሆን ሕገወጥነት ተስፋፍቷል ማለት ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ተሃድሶ ወይም ግምገማ ቢካሄድ ሕግን አለማስከበር ውጤቱ የከፋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ትልቁ ችግር የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት ጨምሮ የተለያዩ ሕጎችን አለማስከበር ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በስፋት እንዲጣሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር አገር ከማስተዳደር ይልቅ ለአገዛዝ የሚመች ሕግ እያወጡ ለመግዛት መሞከር ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ የቅርብ ጊዜ ሁኔታችንን መለስ ብለን ስንቃኝ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች መብቶቻችን ተጥሰዋል ብለው አደባባይ ወጥተው ምላሹ የከፋ ሆኗል፡፡ በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት ውጥረቶች በግልጽ የሚያሳዩት የሕግ የበላይነት ያለመስፈን ችግርን ነው፡፡ ይህ ለዘመኑ የማይመጥን ነው፡፡
በሕግ የበላይነት መተዳደር የሚያስፈልገው የአገርና የሕዝብ ዕጣ ፈንታ በተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ይሁንታ ሥር እንዳይወድቅ ነው፡፡ የአገሪቱ ፓርላማ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ወክሎ የሕግ አውጭነት ሥልጣን አለው፡፡ በዚህም መሠረት አገሪቱ በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደሯን መቆጣጠር፣ አስፈጻሚውን የመንግሥት አካል መከታተልና ፈሩን እንዳይስት ማድረግ፣ የሕዝብ ድምፅ መሆን የሚገባቸው ሚዲያዎች በነፃነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ማገዝና ከለላ መስጠት፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ለሁሉም ወገኖች በእኩልነት እንዲመቻች መርዳት፣ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖርበት ጫና መፍጠር፣ ለአምባገነንነት መደላድል የሚሆኑ ሕገወጥ አሠራሮችን ማስወገድ፣ አሳሪና አፋኝ ሕጎች እንዳይወጡ በጥብቅ መከላከል፣ የሕዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ፣ ወዘተ. ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ግን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት አይቻልም፡፡ በርካታ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ባሉበት አገር ውስጥ የሕግ የበላይነት ሳይከበር በነሲብ መኖር አይታሰብም፡፡ አገሪቱን ከተለየያዩ አቅጣጫዎች ሰቅዘው የያዙዋት ችግሮች ገደባቸውን ጥሰው የወጡት፣ በዚህ ሳቢያ መሆኑን ማመን ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ እያሰቡ ራስን ለማሳመን መሞከር ከንቱ ልፋት ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከፖለቲካው አዙሪት በተጨማሪ ኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ችግር አለ፡፡ አንደኛው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲሆን፣ ሌላው የቱሪዝም እንቅስቃሴው መዳከም ነው፡፡ በሌላ በኩል የኤክስፖርት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት ሲደፈርስ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይዳከማል፡፡ የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ሲስተጓጎል ማምረት ያቅታል፡፡ ማምረት ካልተቻለ የበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ሥራ አጥ ወጣቶች ሲበዙ ደግሞ አመፅ ይቀሰቀሳል፡፡ ዜጎች ጥረው ግረው ያፈሩት ሀብትና ንብረት የቀማኞች ሲሳይ ይሆናል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት እየተስፋፋ ዘረፋ ይለመዳል፡፡ ኢንቨስትመንት ይዳከማል፡፡ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች በወፍ በረር ለሚቃኝ ማንኛውም አገር ወዳድ ዜጋ የሚያሳስበው መፍትሔ የመፈለግ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሰከን ያለና የተረጋጋ ዓውድ ይፈልጋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደር ሥርዓት ሲኖር ግን ለችግሮች የጋራ መፍትሔ መፈለግ አያቅትም፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በራስ መተማመናቸውን ማዳበር የሚችሉት የሕግ የበላይነት መኖሩን ሲያረጋግጡ ስለሆነ፣ ለመፍትሔ ፍለጋ የሚረዱ ሐሳቦችን ሲያፈልቁ የችግሩን ሥረ መሠረት በነፃነት ያፈርጡታል፡፡ ነገሮችን በማድበስበስ ስለማያልፉ ጠቃሚ አበርክቶ ይኖራቸዋል፡፡ ወ y34መዋሸትና ማድበስበስ ይህችን አገር ምን ያህል ወደ ኋላ እንዳስቀራት ይህ ሐሳብ ገላጭ ነው፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርትና ባልተከናወኑ ሥራዎች አገርን መቀመቅ መክተት እንዲቀር፣ ለሕግ የበላይነት ልዕልና ትኩረት ይሰጥ፡፡ ለዘመኑ የሚያስፈልገው ይኼ ነው፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በእጅጉ ከተጎዳችባቸው ችግሮች መካከል የተማረ የሰው ኃይሏን መጠቀም አለመቻሏ ነው፡፡ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አንቱ የተባሉ ምሁራንንና ኤክስፐርቶችን ያፈራች አገር፣ በፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ የወላድ መካን ሆናለች፡፡ ሙያና የፖለቲካ አቋምን መለየት አለመፈለግ ‹የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው› አስተርቷል፡፡ የተማሩ ዜጎች በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ሲገፉና ከለላ የሚሰጣቸው ሲያጡ ወይ አርፈው ይቀመጣሉ፣ ወይም ከአገር ይሰደዳሉ፡፡ በውጭ ግንኙነት፣ በብሔራዊ ደኅንነት፣ በሕክምና፣ በግብርና፣ በምህንድስና፣ በፋይናንስ፣ በታሪክ፣ በሕግ፣ በትምህርት፣ በሥነ ጥበብ፣ በቴክኖሎጂ፣ ወዘተ. በፖሊሲ ደረጃ ሊያማክሩና ተቋማትን ጭምር ሊመሩ የሚችሉ በርካታ ምሁራንና ኤክስፐርቶች በአገር ውስጥና በውጭ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ወገኖች ዕውቀት ለአገር ጥቅም ሳይውል በከንቱ ሲባክን ለምን መባል የለበትም? ችግሩን ፍርጥርጥ አድርጎ አውጥቶ በመነጋገር መፍትሔ አይፈለግም? የተገፉበትን ወይም የሸሹበትን ምክንያት በግልጽ በመናገር ችግሩን መቋጨት ተገቢ አይሆንም? የሕግ የበላይነት አንዱ ጥቅሙ እነዚህን መሰል ውድ ዜጎች በራስ መተማመን ለመጨመር ነው፡፡ ዘመኑ የሚፈልገውም ይህንን ነው፡፡
የፖለቲካው፣ የኢኮኖሚውና የማኅበራዊው ጉዳይ ሲወሳ ማንም አዕምሮ ውስጥ የሚመጣው የእኩልነት ጥያቄ ነው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ መኖሩ የሚረጋገጠው ደግሞ በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው አካል ሥልጣኑን በፍትሐዊና በነፃ ምርጫ እንዳገኘው ማመን ካልቻለ፣ የሥልጣኑ ምንጭ ጉልበቱ ወይም አሸናፊነቱ ብቻ ከመሰለውና በዚያው የሚነጉድ ከሆነ ስለዴሞክራሲ መነጋገር አይቻልም፡፡ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ነው ብሎ መናገር የሚቻለው ለሕግ የበላይነት መገዛት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሰላማዊ ትግሉ ምንም ያህል መራርና ከባድ ቢሆንም፣ ሥልጣን ላይ የሚወጣው በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መሆኑን ማመን አለባቸው፡፡ ለዚህ እውነታ ሲሉም ለሕግ የበላይነት መታገል ግዴታቸው ነው፡፡ አገር የምታድገውና የምትበለፅገው ሰላምና ዴሞክራሲ ሲኖሩ ነው፡፡ መልማት የሚቻለው ለሕግ የበላይነት የሚገዛ ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡ ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሙስና ውስጥ መዘፈቅና አምባገነናዊ ድርጊቶች ውስጥ የሚገባው የሕግ የበላይነት ሲጣስ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ ግንባርም ሆነ አባል ድርጅቶቹ በራቸውን ዘግተው ሲነጋገሩ የውስጥ ሽኩቻቸው ላይ ብቻ ከሚያተኩሩ፣ መጀመሪያ ለሕግ የበላይነት መገዛታቸውን ይመኑ፡፡ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው አገሩ በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ እንድትተዳደር ነው፡፡ ሕዝብን አለማክበር ደግሞ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትን እያነገሠ አገርን ለጥፋት ይዳርጋል፡፡ ለዚህም ነው በሕግ የበላይነት ሥር የማይተዳደር አገር የሕገወጦች መጫወቻ ይሆናል የሚባለው!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman