ሼክ አል አሙዲ ታስረው እየተመረመሩ ነው

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ አል አሙዲ በሳዑዲ ዓረቢያ በተጀመረው ፀረ ሙስና ዘመቻ ታስረው እየተመረመሩ ነው፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያን ፀረ ሙስና ዘመቻ የሚመሩት የአገሪቱ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በታዋቂው ሪትዝ ካርልተን ሆቴል በቁጥጥር ሥር ካዋሏቸው 11 ልዑላንና 38 ታዋቂ ባለሀብቶች መካከል አንዱ የሆኑት ሼክ አል አሙዲ፣ በሙስና ተጠርጥረው እየተመረመሩ ይገኛሉ፡፡

የአገሪቱ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሼክ ሳውድ አል ሞጀብ የፀረ ሙስና ዘመቻው በሳዑዲ ዓረቢያ የተንሰራፋውን ሙስና ለመንቀል ጅማሮ ነው ብለዋል፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ግለሰቦች ሀብቶችና ኢንቨስትመንቶች መታገዳቸው ታውቋል፡፡
በዚህ መሠረት የሼክ አል አሙዲ በሳዑዲ ዓረቢያ ያሏቸው ኢንቨስትመንቶች የታገዱ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ያላቸው ኢንቨስትመንቶች ላይ ዕገዳ አይኖርም ተብሏል፡፡ ለንደን የሚገኙት የሼኩ ቃል አቀባይ ከሳዑዲ ዓረቢያ ውጪ ያሉ የባለሀብቱ ኢንቨስትመንቶች ምንም እክል እንደማይገጥማቸው ለብሉምበርግ ተናግረዋል፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ እየተካሄደ ያለው የንጉሣዊ አገዛዙ የውስጥ ጉዳይ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ቲም ፒንድሪ፣ ሼኩ ከሳዑዲ ውጪ ያሏቸው ሀብቶችና ኢንቨስትመንቶች ችግር እንደማይገጥማቸው ገልጸዋል፡፡
ሼክ አል አሙዲ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሏቸው ኢንቨስትመንቶች ለ50 ሺሕ ያህል ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን፣ ይህም ከመንግሥት ቀጥሎ ትልቁ የሥራ ዕድል ፈጣሪ ባለሀብት አድርጓቸዋል፡፡ የእሳቸው በቁጥጥር ሥር መዋል ከተሰማ በኋላም ኢትዮጵያ ውስጥ መደናገርና መደናገጥ ተፈጥሯል፡፡ ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው የሚድሮክ ኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊዎችም ግራ መጋባታቸውን ከመግለጽ ውጪ፣ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ሪፖርተር ከሌሎች የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንዳረጋገጠው፣ ከቤተሰቦቻቸው መካከል ከአንደኛው ጋር ብቻ በሆቴሉ ስልክ ይገናኛሉ፡፡ ሪፖርተር ስለጉዳዩ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡  
በሳዑዲ ዓረቢያ የተጀመረውን የፀረ ሙስና ዘመቻ የሚመራው የ32 ዓመቱ አልጋ ወራሽ 11 ልዑላንና 38 ታዋቂ ባለሀብቶች እንዲታሰሩ ማዘዙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ስቧል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም የሳዑዲ ባለሥልጣናትን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ በይፋ አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ፣ ‹‹በሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሥ ሳልማንና በአልጋ ወራሹ ላይ ትልቅ እምነት አለኝ፤ የሚያደርጉትንም በሚገባ ያውቃሉ፤›› ብለው ጽፈዋል፡፡ በሌላ የቲዊተር መልዕክትም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ሳዑዲ ዓረቢያን ለዓመታት ክፉኛ ሲያልቧት እንደነበረም ገልጸዋል፡፡
የፀረ ሙስና ዘመቻው ፊታውራሪ ወጣቱ አልጋ ወራሽ በጀመረው የኢኮኖሚክ ሪፎርም ላይ እንቅፋት ይፈጥራሉ የሚባሉ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የፀረ ሙስና ዘመቻው በሳዑዲ ዓረቢያ ከመጀመሩ ሁለት ሳምንታት በፊት ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ሰዎች በሪያድ ተሰብስበው የነበረ ሲሆን፣ ወጣቱ አልጋ ወራሽ በሚገነባት ዘመናዊዋ ሳዑዲ ዓረቢያ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እንዲሳተፉ ለቢዝነስ ሰዎች ጥሪ አቅርቧል፡፡ አልጋ ወራሹ በሳዑዲ በረሃ ላይ በ400 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባውን ዩቶፒያን ሜጋሲቲ ፕሮጀክት ላይ እንዲሳተፉ የቢዝነስ ሰዎችን ጋብዟል፡፡ አልጋ ወራሹ በጀመረው የኢኮኖሚክ ሪፎርምም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው ግዙፉ ነዳጅ አምራቹ ሳዑዲ አራምኮ ኩባንያ ለሕዝብ እንዲሸጥ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ኩባንያው የልዑላኑ ሀብት ሆኖ እንዲቀጥል በሚፈልጉት ወገኖች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ አንዳንድ ተንታኞችም በፀረ ሙስና ዘመቻው የታሰሩት ልዑላን የሐሳቡ ተቃዋሚና አልጋ ወራሹ በሳዑዲ ዓረቢያ ለማምጣት ለሚፈልገው ለውጥ እንቅፋት የሆኑት መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በእናታቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑት ሼክ አል አሙዲ 10.3 ቢሊዮን ዶላር ሀብት እንዳላቸው የፎርብስ መረጃ ይገልጻል፡፡ በሀብት መጠናቸው በሳዑዲ ዓረቢያ ሁለተኛ ሲሆኑ፣ ከዓረብ አገሮች ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣቸዋል፡፡ ባለሀብቱ በኮንስትራክሽን፣ በእርሻና በነዳጅ ሴክተሮች የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ፣ በሳዑዲ ዓረቢያና በስዊዲን አሏቸው፡፡ ሼክ አል አሙዲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ70 በላይ ኩባንያዎች የመሠረቱ ሲሆን በተለይ በሲሚንቶ፣ በወርቅና በእርሻ ላይ የተሰማሩ ግዙፍ ኩባንያዎች ባለቤት ናቸው፡፡
በሳዑዲው አልጋ ወራሽ የሚመራው የፀረ ሙስና ኮሚቴ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው መካከል የኤምቢሲ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ባለቤት አልዋሊድ አል ኢብራሒም፣ ቢሊየነሩ ልዑል አልዋሊድ ቢን ታላል፣ የሳዑዲ ባህር ኃይል ኮማንደር አብዱላህ ሡልጣን፣ የቀድሞ ገንዘብ ሚኒስትር ኢብራሒም አል አሳፍ፣ እንዲሁም የቀድሞ ገዥ አሚር አል ዳባጋ ይገኙበታል፡፡ በፀረ ሙስና ዘመቻው የታሰሩት 11 ልዑላንና 38 ታዋቂ ባለሀብቶች ሪያድ በሚገኘው ባለ አምስት ኮከብ ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ይገኛሉ፡፡
Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman