‹‹በእኔ ዕይታ የአፈጻጸም ክፍተት ካልሆነ በስተቀር የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር አላመጣም››

‹‹በእኔ ዕይታ የአፈጻጸም ክፍተት ካልሆነ በስተቀር የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር አላመጣም››

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከ1987 ዓ.ም. እስከ 1993 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ርዕሰ ብሔር ወይም ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ከዚያ በፊት በሽግግሩ ጊዜ በመጀመርያ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በኋላ የማስታወቂያ ሚኒስትር፣ እንዲሁም ጎን ለጎን የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ ከ1984 ዓ.ም. እስከ 1987 ዓ.ም. ሥራ ላይ የነበረውና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን ያረቀቀው የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽንም አባል ነበሩ፡፡ ሕገ መንግሥቱን ያፀደቀው የሕገ መንግሥት ጉባዔም አባልና ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ በሐምሌ ወር 1983 ዓ.ም. የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ)ን የተቀላቀሉት ለረዥም ዓመታት ይኖሩበት ከነበረው ጀርመን በመምጣት ነበር፡፡ ኦሕዴድን በመወከል ለአሥር ዓመታት በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ በ1993 ዓ.ም. በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት ከኦሕዴድም ሆነ ከኢሕአዴግ ተለይተዋል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. በግል ተወዳድረው በማሸነፍ የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ የተቃውሞውን ፖለቲካ ከተቀላቀሉ በኋላ ደግሞ የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ (አንድነት) ሊቀመንበርና የውጭ ግንኙነት ኃላፊም ነበሩ፡፡ መድረክ እንዲቋቋም ተነሳሽነት ከወሰዱ ግለሰቦችም አንዱ ናቸው፡፡ ሰለሞን ጎሹ የሕገ መንግሥቱን ዲዛይንና አፈጻጸም በተመለከተ የሚነሱ ውዝግቦችንና የኦሕዴድ አዲስ አመራሮችን የአመራር ዘይቤ ጨምሮ በተለያዩ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በምርጫ 2007 በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶችን ሙሉ በሙሉ እንዳሸነፈ በምርጫ ቦርድ የተነገረለት ኢሕአዴግ፣ ውጤቱ ሕዝቡ ከኢሕአዴግ ውጪ ላሉ የፖለቲካ ኃይሎች ቦታ እንደሌለው ያሳያል ሲል ተናግሮ ነበር፡፡ አዲስ መንግሥት ባዋቀረ ማግሥት የጀመረው የሕዝብ ተቃውሞና አመፅ ግን አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ፣ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እያስከተለ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደ ቀጠለ ነው፡፡ በእርስዎ ዕይታ የዚህ ችግር መነሻ ምንድነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- መጀመርያ እንቅስቃሴው የተጀመረው በኦሮሚያ ጊንጪ ነው፡፡ አንቀሳቃሾቹ ደግሞ ወጣቶች ወይም ‹ቄሮዎች› ነበሩ፡፡ ለዘመናት ጥበቃ የተደረገለት የጭልሞ ደን ለኢንቨስተር በመሰጠቱና ከትምህርት ቤትና ከወጣቶች መጫወቻ መሬት ላይ ተወስዶ ለአካባቢው ባለሥልጣናት ቤት መሥሪያ መሰጠቱን በመቃወም ነው ችግሩ የተጫረው፡፡ ተመሳሳይ ችግሮች በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎችና ክልሎችም የነበሩ ይመስለኛል፡፡ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ደግሞ ችግሩን አባባሰው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 (5) ተግባራዊ ሳይሆን ከ20 ዓመት በላይ መቆየቱ ከዚህ ጋር ሲደመር ችግሩ ይበልጥ እንዲከር አድርጎታል፡፡ ስለዚህ መነሻው የመሬት አስተዳደር ነው፡፡ ከምርጫ 97 በፊት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ አዳማ እንዲሄድ ተወስኖ ነበር፡፡ ይህንን የተቃወሙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታስረዋል፡፡ 300 የሚሆኑትም ለአንድ ዓመት ታግደዋል፡፡ በኦሮሚያ ሕገ መንግሥት የክልሉ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንደሆነች ተደንግጓል፡፡ ክልሉ ከከተማዋ ጋር ታሪካዊ ቁርኝትም አለው፡፡ ከተማዋ የኦሮሚያ መሬት ስለሆነች ለምን እንለቃለን በማለት ነበር ተማሪዎቹ የጠየቁት፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ግን ከተማዋ መልሳ የኦሮሚያ ዋና ከተማ እንድትሆን ተደርጓል፡፡
የካቢኔ አባል ሆኜ በምሠራበት በሽግግሩ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስተር ፕላን አዘጋጅቶ እንዲናፀድቅለት አምጥቶ ነበር፡፡ ስናየው በደርግ ጊዜ የተዘጋጀና እስከ ደብረ ብርሃን፣ አምቦ፣ ፍቼ፣ አሰላና ወሊሶ ድረስ የሚያካት ሰፊ ፕላን ነበር፡፡ እሱን ውድቅ አድርገን እስከ ለገጣፎና አቃቂ ወንዝ ድረስ ብቻ ወደ ጎን የሚሰፋ ማስተር ፕላን እንዲዘጋጅና ድንበሩም እንዲካለል ወስነን ነበር፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ አቶ ዓሊ አብዶ የከተማዋ ከንቲባ እያሉ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ጉዳዩ ተነስቶ፣ በአስቸኳይ ኮሚቴ ተቋቁሞ የድንበር ድንጋዮች እንዲተከሉ መወሰኑንም አስታውሳለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ውዝግብ አልፎ የተዘጋጀው ማስተር ፕላን በቂ ሕዝባዊ ውይይትም አልተደረገበትም፡፡ መሬቱ ተነጥቆ ለባለሀብት የሚሰጥበት ገበሬም በቂ ካሳና መቋቋሚያ የማይሰጠው መሆኑም ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ናቸው ተቃውሞና አመፅ የቀሰቀሱት፡፡
ሪፖርተር፡- አገሪቱን የገጠማት የፖለቲካ ቀውስ ምን ያህል ከባድ ነው? ከዚህ ችግርስ ለመውጣት በአጭርና በረዥም ጊዜ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- አገሪቱን ከገጠሟት ችግሮች አንዱ ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለሰዎች ሕይወት ማጣትና መጎዳት ምክንያት የሆኑትን የቅማንት፣ የወልቃይትና የኮንሶን ጥያቄዎች ለአብነት ማንሳት እንችላለን፡፡ የቅማንት ጥያቄ ምላሽ ያገኘ ቢመስልም ሌሎቹን ለመመለስ ምን እየተሠራ እንደሆነ አላውቅም፡፡ የድንበር ማካለል ችግርም ሌላው የግጭት መነሻ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ፣ እንዲሁም በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉምዝ መካከል ያለው የድንበር ጭቅጭቅ እስካሁን አልተፈታም፡፡ እነዚህ ችግሮች በጊዜ ትኩረት አግኝተው ካልተፈቱ ቀውሱ መባባሱ አይቀርም፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ድንበር ላይ ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ነበር፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ሙሉ በሙሉ አልተተገበረም፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በአግባቡ ለመፍታት የሚያስችሉ ድንጋጌዎችና ሥርዓቶች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ተካተው ይገኛሉ፡፡
ለአብነት ያህልም የፌዴራል ሥርዓቱን፣ የመሬት ይዞታ አጠቃቀምና የሕዝቦች ተሳትፎን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በአግባቡ ተግባር ላይ እየዋሉ አይደለም፡፡ ግለሰቦች የጫሯቸው ግጭቶች የተወሰነ ብሔር አባላት ላይ ጉዳት ወደ ማድረስ ሲሸጋገሩ ዓይተናል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ችግሩ ቶሎ ካልተቀረፈ ወደ ብሔሮች ግጭት ሊያድግ እንደሚችል ነው፡፡ ኢትዮጵያን ወደ መበጣጠስ ደረጃ ሊያድግ ይችላል የሚሉ አሉ፡፡ ይኼ አይከሰትም የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ነገር ግን ችግሮች በፍጥነት ካልተፈቱ የሕዝቦች እርስ በርስ ጦርነት ሊመጣ ይችላል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱን ስትቀርፁ፣ አገሪቱ በምን ዓይነት የመንግሥት መዋቅር ትደራጅ የሚለውን ስትወስኑና ብሔር ተኮር የፌዴራል ሥርዓት ሕዝቦችን ወደ ግጭት ሊመራ ይችላል፡፡ አገሪቱንም ወደ አለመረጋጋት ሊከታት ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ እንዲያውም አንድ የግጭት መፍቻ መንገድ ነው በሚል ሥጋቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡ ይህን ውሳኔ ስትወስኑ አሁን በአገሪቱ በተንሰራፋው መጠን ብሔር ተኮር ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል ገምታችሁ ነበር? ይህስ እንዳይከሰት፣ ከተከሰተም ለመቆጣጠር የሚችሉ ተቋማትን የማደራጀት ጉዳይ ላይ በበቂ ተወያይተናል ብለው ያምናሉ?   
ዶ/ር ነጋሶ፡- ከ29 የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባላት መካከል ሰባት ያህሉ ብቻ ከተወካዮች ምክር ቤት ስንወከል፣ የኢሕአዴግ አባላት የነበርነው አቶ ዳዊት ዮሐንስና እኔ ብቻ ነበርን፡፡ አንቀጽ 39 ወይም የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት ይኑር? ወይስ ይቅርና መሬት በመንግሥት ይዞታ ሥር ይሁን? ወይስ በግለሰቦች ሥር ሆኖ ይሸጥና ይለወጥ? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ከነበረው ክርክር ውጪ የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ተቃውሞ አልነበረም፡፡ የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የሚችለው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሥርዓት ነው የሚል አመለካከት ነው በዚያን ጊዜ የነበረው፡፡ ብሔር ተኮር የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር ያመጣል ብለው የተከራከሩት በተለይ በጉባዔው በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ አዲስ አበባን የወከሉት ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእኔ ዕይታ የአፈጻጸም ክፍተት ካልሆነ በስተቀር የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር አላመጣም፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ግን በቂ ትኩረት ሰጥተን እንዳልተወያየን ይሰማኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ወቅታዊው የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ በቅርብ መነሻዎችና ለረዥም ጊዜ ሲንከባለሉ በመጡ ችግሮች ቢቀሰቀስም፣ በዋናነት ብዙዎች የሚስማሙበት መነሻ ግን በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ የቡድኖችና የግለሰቦች መብቶችና ነፃነቶች እየተተገበሩ አለመሆኑን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሁሉንም በእኩልነት እየጠቀመ እንዳልሆነም ቅሬታ ይቀርባል፡፡ በይዘት ደረጃ የሚጠቀሱ ቅሬታዎች እንዳሉ ሆነው፣ እርስዎ ከጊዜ በኋላ የሕገ መንግሥቱ የመጨረሻ ረቂቅ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ቢደረግ ኖሮ የተሻለ ይሆን እንደነበር መገንዘብዎን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ሐሳብ ይስማማ ነበር ብለን ግምት ብንወስድ፣ ሕገ መንግሥቱ የተለያዩ ሐሳቦችን ከመያዙ አኳያ ይህ እንዴት ሊፈጸም ይችል ነበር?  
ዶ/ር ነጋሶ፡- የእኔ ዕይታ ትኩረት አጨቃጫቂ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም መታየት የነበረባቸው ሌሎች ድንጋጌዎች አሉ፡፡ እንደ አዲስ መግባት ያለባቸው ድንጋጌዎችም አሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁሉም ሰው በጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት አመለካከት ይኖረዋል ለማለት አንችልም፡፡ ድጋፍ ወይም ተቃውሞ ይኖራል፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያሉት ተቃውሞዎች ለብዙ ጊዜያት ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በቂ ውይይትና ክርክር ሊደረግበት ይገባል፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ሐሳቦች በነፃነት ቀርበው እነዚህ ላይ ሕዝቡ የመምረጥ ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህ ካልተደረገ ችግሮቹ ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ሊጣስ ይችላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ተቀባይነትም ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ነው የሕገ መንግሥቱ ማርቀቅና ማፅደቅ ሒደት አሳታፊነት ላይ ጥያቄ የማቀርበው፡፡ ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ አልነበሩም፡፡ 73 ጥያቄዎችን ወደ ሕዝብ አውርደን 23,000 ቀበሌዎች በተወያዩበት ወቅት፣ የተሳተፈው የሕዝብ ብዛት አጥጋቢ አልነበረም፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣና የኢሕአዴግ ልሳኖች ሕዝቡ በሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተወያየ ሲጽፉ አያለሁ፡፡ ነገር ግን ውይይቱ የተካሄደው በተለዩት 73 ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ከውይይቱ በመነሳት ነው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት አንቀጾች የተዘጋጁት፡፡ በእሱ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት ከተወያየበትና ከተከራከረበት በኋላ ነው የሕገ መንግሥት ጉባዔ ያፀደቀው፡፡ እርግጥ በኢሲኤ በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ አማካይነት የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን ያደረጉትን ጨምሮ የተለያዩ ውይይቶች በረቂቁ ላይ ተደርገዋል፡፡ ግን እነዚህን ሕዝባዊ ውይይት አልላቸውም፡፡ ፍላጎት ካለና ጠቀሜታው ላይ መግባባት ካለ ሕዝባዊ ውይይት ማድረግ ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያን ጊዜ ማድረግ ባይቻልም አሁን ይቻላል፡፡ አሁን ከ22 ዓመታት በኋላ ጥያቄዎቹ በስለዋል፡፡ አዲስ ትውልድም ተፈጥሯል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች መሠረታዊ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ሁልጊዜ መቀያየር ጥሩ ባይሆንም ከእነዚህ ለውጦች ጋር አብሮ የሚሄድ ሕገ መንግሥት ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ 
ሪፖርተር፡- በርካታ የሕገ መንግሥትና የፌዴራሊዝም ባለሙያዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የተዋቀሩበት መንገድ ችግር እንዳለበት፣ በተግባርም የሕገ መንግሥቱ አፈጻጸም ላይ መሰናክል እንደሆነ በመጥቀስ እንዲሻሻል ሲጠይቁ ይሰማሉ፡፡ እርስዎም በዚህ እንደሚስማሙ በቅርቡ ገልጸዋል፡፡ ይህ አቋምዎ የመጣው እነዚህ ተቋማት በእርስዎ የግል የፓርላማ ተወዳዳሪነት ምክንያት ለቀድሞ ፕሬዚዳንት የተገቡ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያጡ ከወሰኑ በኋላ ነው ወይስ በፊትም ነበር?
ዶ/ር ነጋሶ፡- እኔ ስለሕገ መንግሥቱ በዝርዝር መናገር የጀመርኩት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ ከለቀቅኩ በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን መድረክን ስናቋቁም ለዚች አገር ምን ዓይነት ሕገ መንግሥት ነው የሚያስፈልጋት? በሚለው ጥያቄ ላይ እንወያይ ነበር፡፡ አሁን እኮ ገዥው ፓርቲ ራሱ ሕገ መንግሥቱን በድጋሚ ለማየትና ለማሻሻል ተስማምቷል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር መድረክ ላይ የአገሪቱን የምርጫ ሕግ ለመቀየር ተስማምተዋል፡፡ ይህን ለመተግበር የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ማሻሻል የግድ ይላል፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ የጠየቅኩት እንደ ማንኛውም ሰውና አካል ሁኔታዎች የተሻለ እንዲሆኑ ነው እንጂ በግሌ ስለተበደልኩ አይደለም፡፡ የእነዚህ ተቋማት አባላት ከአሸናፊው ፓርቲ የሚውጣጡ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ተሸንፎ ሌላ ፓርቲ ቢመጣም አባላቱ የአዲሱን ገዥ ፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቃቸውን ይቀጥላሉ፡፡ የፖለቲካ አካል የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተለይ በፖለቲካ ሥሌት ተመርቶ ሕገ መንግሥቱን ሲተረጉም የሕገ መንግሥቱን መንፈስ ሊያዛባ ይችላል፡፡ ከዚህ ይልቅ በነፃ ፍርድ ቤት ቢተረጎም ይሻላል፡፡ በተለይ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ቢቋቋም የተሻለ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በእርስዎ አመራር ጊዜ የነበረውና አሁን በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦሕዴድ መሠረታዊ ልዩነት ምንድነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ስለኦሕዴድ ከተናገራቸው ነገሮች መካከል ሁለት ነገሮች አስታውሳለሁ፡፡ አንደኛው የኦሕዴድ ካድሬዎች ዲሲፕሊን የሌላቸው፣ ችግር ፈጣሪዎችና ገና ያልበሰሉ ናቸው ብሎ የአሜሪካ አምባሳደር ነገረኝ ያለው ነው፡፡ በ1989 ዓ.ም. ባደረግነው ግምገማ ችግር የነበረባቸውን ወደ 10,000 የሚጠጉ ካድሬዎች አባረናል፡፡ በሙስና ወንጀል ታስረው የነበሩ ግለሰቦች እኛ ከድርጅቱ ስንወጣ ተፈተዋል፡፡ ተመልሰው ሥራ የጀመሩ ሰዎች አሉ፡፡ አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ በተወሰነ ደረጃ ሙስናን ለመዋጋት ሞክሯል፡፡ በእኛ ጊዜ ፍላጎታችንና ተግባራዊ የምናደርገው ልዩነት ነበረው፡፡ ያኔ በአመራር በኩል የተፈለገው ነገር አሁን የመጣ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው አቶ መለስ ኦሕዴድ መብቱን ጠያቂ ድርጅት አይደለም ያሉት ነው፡፡ አሁን ከጊዜ ብዛት የተወሰኑ ጠንካራ የኦሕዴድ አባላት በሕገ መንግሥቱ መሠረት መሠራት አለበት ብለው እየተከራከሩ ነው፡፡ ሕዝቡም በተለይ አርሶ አደሩ ጠያቂ ሆኗል፡፡ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉንም ነገር አሜን ብሎ አይቀበልም፡፡ የፖለቲካ ብስለት እያሳየ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኦሮሞ ፖለቲካ አሁን አዲስ ቅርፅ ይዟል ማለት ይቻላል? ኦነግና ኦሕዴድ ያራምዱት ከነበረው የፖለቲካ አስተሳሰብ ውጪ እነ ጃዋርና ቄሮ ሌላ አማራጭ አቅርበዋል ብለው ያምናሉ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ከፖለቲካ ድርጅቶች አንፃር ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የኦሮሞ ፖለቲካ ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ ያኔ ኦሕዴድ አገሪቱን ዴሞክራሲያዊ በማድረግ፣ በኢኮኖሚ፣ በቋንቋና በባህል፣ እንዲሁም የውስጥ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነበር፡፡ ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ የመገንጠሉ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ ኦነግን ጨምሮ ሌሎቹ ድርጅቶች ግን ኦሕዴድ የሌሎች ድርጅቶች ወኪል ነው ይሉ ነበር፡፡ ኦሕዴድ ከኢሕአዴግ ከለቀቀ ብቻ ነው አብረነው የምንሠራው ይሉ ነበር፡፡ የእነ ጃዋርና ቄሮ ፖለቲካ ተፅዕኖ እየፈጠረ የመጣው በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ነው፡፡ ውጭ አገር ያሉ ሬዲዮና ቴሌቪዥኖችም ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች አማካይነት በርካታ ጥያቄዎች ገፍተው እየመጡ ቢሆንም በትክክል ምንድነው የሚፈለገው  የሚለው ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ የእንቅስቃሴው ግብ ምንድነው? የአስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ ነው? ነፃና ሉዓላዊ ኦሮሚያን መፍጠር ነው? እንቅስቃሴው በግልጽ አደረጃጀትና በዲሲፕሊን መመራት አለበት፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ ስታደርግ ሕጋዊ መንገዶችን መከተል አለብህ፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንዶች በሕገ መንግሥቱ የታቀፈው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ቢወገድ የአገሪቱ ችግር ይቀረፋል ይላሉ፡፡ ሌሎች ግን በተለይም የኦሮሞ ፖለቲከኞች ችግሩን ከዴሞክራሲ ዕጦት ጋር ያያይዙታል፡፡ በሌላ በኩል የኢሕአዴግ ፖሊሲዎች ጭብጦች ከሕገ መንግሥቱ ጋር አብረው አይሄዱም በማለት ይተቻሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አገር የምትሆነው ኢሕአዴግን ጨምሮ ሁሉም ድርጅቶች ዴሞክራሲያዊ ሲሆኑ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ባህልን በሕዝቡ ውስጥ ማስረፅ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ፕሮግራም ውስጥ የእኔ ብቻ አቋም ልክ ነው የሚል አስተሳሰብ የሰረፀ ይመስለኛል፡፡ የሌሎችን አቋም የምታከብረው ዴሞክራሲያዊ ስትሆን ነው፡፡ እዚያ ላይ ችግር አለ፡፡ ይህን ደግሞ የሚያስተካክለው ሕዝቡ ነው፡፡ እነ ለማ ከሕዝቡ የመጣ ጥያቄ ስለሆነ እንደከዚህ ቀደሙ መሄድ አንችልም ማለት የጀመሩት፣ የሕዝቡ ጠያቂነት እየበረታ ስለመጣ ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም. በነበረው ተሃድሶ ኢሕአዴግ ያወጣው ፕሮግራም በ25 ዓመታት ውስጥ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ እንዲኖራት እናደርጋለን ይላል፡፡ ያኔ በኢኮኖሚ ጠንካራ ስለምንሆንና በሕዝቡ አኗኗር ላይ መሠረታዊ ለውጥ ስለምናመጣ ሕዝቡ ቢያባርረንም እንቀበላለን፣ ተቃዋሚ ሆነን በድጋሚ ለመመረጥ እንሞክራለን ብሏል፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን ሥልጣን ላይ ለመቆየት ነው የወሰነው፡፡ ይኼ ሐሳብ አሁንም የተቀየረ አይመስለኝም

source:Reporter  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa