ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያ በሰብአዊ ድጋፍ ያላትን ሚና አደነቁ
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ
ኦባማ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ እያደረገች ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ አደነቁ።
በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው
71ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በተጓዳኝ ፕሬዚዳንት ኦባማ በዋነኝነትና ስድስት አገሮች በትብብር ያዘጋጁት የውይይት
መድረክ ተካሂዷል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ካናዳ፣ ጀርመን፣
ጆርዳን፣ ሜክሲኮና ስዊድን መድረኩን በተባባሪነት ያዘጋጁና በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አገሮች ናቸው።
ፕሬዝዳንት ኦባማ በዚሁ ወቅት
እንዳሉት ኢትዮጵያ የተለያዩ አገሮችን ስደተኞች ተቀብላ ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀመች ነው።
ጀርመን፣ ቱርክ፣ ፓኪስታን፣
ካናዳና ስዊድንም አስተዋጾአቸው የጎላ መሆኑን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፥ ሌሎች አገሮችም ይህንኑ ተመክሮ ቢጋሩ በስደተኞች ላይ እየደረሰ
ያለውን ውስብስብ ችግር መፍታት እንደሚቻል ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅት የዓለማችን አንድ
በመቶ ወይም ከ65 ሚሊየን ህዝብ በላይ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ተሰደው ይገኛሉ።
ከእነዚህ ስደተኞች መካከል አብዛኛዎቹን
አስጠግተዋቸው የሚገኙት ከ10 የማይበልጡ አገሮች ሲሆኑ፥ ኢትዮጵያም 800 ሺህ ስደተኞችን በማስጠጋት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ
ይዛለች።
ፕሬዚዳንት ኦባማ በተለያዩ የዓለም
አገሮች በስደት ላይ የሚገኙ ሰዎች የትምህርት፣ ፍትህና እኩልነት ጉዳይ ትኩረት መሰጠት ያለበት መሆኑን ነው በአጽንኦት የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም
ደሳለኝ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ባላት አቅም ሁሉ ስደተኞችን በመቀበል ድጋፏን ታጠናክራለች ብለዋል።
አሁን በአገሪቷ የሚኖሩ ስደተኞች
ያለምንም መገለል የትምህርት እድል እንዲያገኙ፣ በግብርና እና በሌሎች የስራ መስኮች እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ወስጥ
30 በመቶ ለስደተኞች የስራ እድል እንዲያገኙ መመቻቸቱንም ገልፀዋል።
በአሜሪካ ኒው ዮርክ እየተካሄደ
ያለው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዋና ትኩረቱን በስደት ላይ አደርጎ እየመከረ ይገኛል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ