በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት በድምሩ የ28 ሰዎች ህይወት አልፏል- ፖሊስ

በአዲስ አበባ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት በድምሩ የ28 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ በመዲናዋ ባንዲራ ከመስቀል እንዲሁም ከሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት ጋር ተያይዘው በተነሱ ግጭቶች የሰው ህይወት ማለፉን ተናግረዋል።
ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ፥ በከተማዋ ከመስከረም 5 በፊት ማንኛውንም አይነት የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ አልተሰጠም፤ ሆኖም ግን ሁከት እስካልተፈጠረ ድረስ ማንኛውም ሰው ባንዲራ ሲሰቅል ነበር፤ የፀጥታ ሀይሉም ይህንን በንቃት ሲከታተል ነበር ብለዋል።
ሆኖም ግን ባንዲራ ከመስቀልና የመንገድ ጠርዞችን ቀለም ከመቀባት ጋር ተያይዞ የመፍቀድና የመከልከል ስራው የፖሊስ ሆኖ ሳለ፤ ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት ከየመንደሩ በመውጣት ስርዓት አልበኝነት በሰፈነበት መንገድ ለማስቆም ሲሉ ግርግር ተፈጥሯል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከመስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 7 2011 ዓ.ም በከተማዋ ሁከት እና ግርግር ተፈጥሯል ብለዋል ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ።
ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግርም በኮልፌ ክፍለ ከተማ የ14፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 5፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ 1፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 3፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 5 በድምሩ የ28 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የአብዛኛዎቹ ህይወት ያለፈው በድብደባ፣ በድንጋይ እና በዱላ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ የሰባት ሰዎች ህይወት ደግሞ በፀጥታ ሀይሉ ነው ብለዋል።
በፀጥታ ሀይሉ ህይወታቸው ካለፈው ውስጥ አንድ ሰው በፖሊስ ስህተት ነው ህይወቱ ያለፈው ያሉ ሲሆን፥ ይህን የፈፀመው ፖሊስም በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን አስረድተዋል።
በተጨማሪም አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሊዘርፍ ሲል በፀጥታ ሀይል ህይወቱ ማለፉን እና ቀሪዎቹ 5 ሰዎች ደግሞ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ.ም በተፈጠረው ሁከት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ህይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ላይ በድብደባ ጉዳት ደርሷል ያሉ ሲሆን፥ በንብረት ላይም ባንክን ከመዝረፍ ሙከራ ጀምሮ በርካታ ጉዳቶች መድረሳቸውን ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጠፋው የሰው ህይወት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማውም ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ ተናግረዋል።
ፖሊስ ሁከቱን ለማስቆም ባደረገው ሙከራም በህገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው የተገኙ በርከት ያሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛውን በማጣራት እና በመምከር ከእስር እንዲለቀቁ ማድረጉንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሁከቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩ 1 ሺህ 204 የሚሆኑ ግለሰቦችን ከተለያዩ አካባቢዎች በመሰብሰብ በቀጣይ ሌላ ጥፋት ላይ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ሰንዳፋ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ለተሃድሶ ስልጠና ወደ ጦላይ እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በ10ሩም ክፍለ ከተሞች በሁከትና ግርግሩ ተሳታፊ የነበሩ እና ማስረጃ የተገኘባቸው 107 ተጠርጣሪዎችን ደግሞ ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ነው ኮሚሽነሩ ያስታወቁት።
ከዚህ ውጪ ግን ፖሊስ ከሺሻ ቤት፣ ቁማር ቤት እና ጫት ቤት ጋር በተያያዘ በድምሩ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።
ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል ባደረገው ዘመቻም በሺሻ ቤት 1 ሺህ 459 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፥ 94 ሰዎች በጫት ቤት እንዲሁም 31 ሰዎች በቁማር ቤት በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
ከእነዚህ ውስጥም በቁማር ቤት ከተያዙት ውጪ አብዛኛው ምክርና እና ተግሳፅ ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውንም ተናግረዋል።
ከዚህ ውጪ ግን ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች ገሚሱ ስንዝናና፣ ስንጠጣ፣ ኳስ ስናይ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አዋለን እየተባለ የሚሰራጨው ወሬ ሀሰት መሆኑንም ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ አስታውቀዋል።
ይህንን ማረጋገጥ ለሚፈልግ አካል ካለ ፖሊስ አስፈላጊውን ማስረጃ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
ነገር ግን ፖሊስ ህገ ወጥነትን ለመከላከል በሚሰራበት ወቅት የሚናፈሱ ወሬዎች ህገ ወጥነትን ለማስፋፋት ካልሆነ ሌላ አላማ የላቸውም ሲሉም ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ አክለውም፥ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ውስጥ እስከ መኪና ስርቆት የደረሰ ዘረፋ መስፋፋቱንም አንስተዋል።
አብዛኛዎቹ ዘራፊዎችም ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ የመጡ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ከደሴ፣ ጎንደር እና አርባ ምንጭ ከተሞች የመጡ ዘራፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቀዋል።
ፖሊስ ከዚህ በኋላ ዝርፊያን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚሰራውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል፤ ህብረተሰቡም ለፖሊስ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥል ሲሉ ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman