በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ስም በባንክ የተቀመጠ 16 ሚሊዮን ብር ታገደ

የፖሊስ ኮሚሽነሩን ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ
በወላይታና በሲዳማ ግጭት የተጠረጠሩ ከንቲባውን ጨምሮ 100 ሰዎች ተከሰሱ
በነፍስ ግድያ፣ ከቀዬ በማፈናቀል፣ በአስገድዶ ማስደፈር፣ የሃይማኖትና የንግድ ተቋማትን በማቃጠል፣ በዝርፊያና በሌሎች በርካታ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው የታሰሩት የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስቀመጡት ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ታገደ፡፡
ዕግዱ የተጣለባቸው በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ከሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በቁም እስር ቆይተው፣ ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ)፣ አቶ መሐመድ አሸር፣ ሰባን ሙአድና ጀማል ፈርሃ መሐመድ ናቸው፡፡ ገንዘቡ በተለያዩ የሒሳብ ቁጥሮች የተቀመጠ መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት አሳውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ገንዘቡ በማንኛውም መንገድ እንዳይወጣና ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ የዕግድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በአቶ አብዲ፣ በክልሉ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ራህማ መሐመድና በዳያስፖራ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱራህዛቅ አሚን ላይ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የጠየቀውን ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤት ፈቅዷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ተረኛ ወንጀል ችሎትን የጠየቀው፣ ረቡዕ ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ ነገር ግን በዕለቱ ተጠርጣሪ ሆነው ቀርበው የነበሩ የክልሉ የመስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሡልጣን መሐመድ፣ ‹‹እኔ የክልሉ ምክር ቤት አባል ነኝ፡፡ ያለመከሰስ መብት እያለኝ መታሰሬ ተገቢ አይደለም፡፡ ያለ መከሰስ መብቴ አልተነሳም፤›› በማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክተው ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ከመርማሪ ቡድኑ ሲያጣራ መርማሪ ፖሊስ፣ ‹‹ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል፤›› ብሎ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲያሳየው ሲጠይቅ፣ በወቅቱ ምንም ሰነድ ያልያዘው ፖሊስ፣ ‹‹በስልክ ጠይቀን ነግረውናል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን የምክር ቤት አባል መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሡልጣን ያለመከሰስ መብት መነሳት አለመነሳቱን የሚያረጋግጥ ሰነድ በአዳሪ ሐሙስ ነሐሴ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. መርማሪ ቡድኑ ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ከላይ የተጠቀሰውን ትዕዛዝ ከመስጠቱ በፊት የተጠርጣሪዎችን ማንነት ካረጋገጠ በኋላ፣ መርማሪ ቡድኑ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት መጠየቁን አስመልክቶ የተጠርጣሪዎቹን አስተያየትም ጠይቆ ነበር፡፡ አራቱም ተጠርጣሪዎች በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ዱርቀቡ ቀበሌ እንደሚኖሩ ከገለጹ በኋላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከ39 ወደ 40 ዓመት በሽግግር ዕድሜ ላይ መሆናቸውን በፈገግታ የገለጹት አቶ አብዲ የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች እንዲጎዱ አንድም ነገር እንዳላደረጉ ወይም ሠርተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ከታሰሩ 25ኛ ቀናቸው እንደሆነና፣ ለ20 ቀናት የታሰሩት በቤታቸው ሳይሆን፣ ቤታቸውን በሚመስል ቪላ ውስጥ እንደነበር፣ ወደ መውጫው በር እንዲደርሱ ባይፈቀድላቸውም የፈለጉትን ያገኙ እንደነበረ፣ ይጠብቋቸው የነበሩ ሰዎች ያዘዟቸውንና የሚፈልጉትን በማቅረብ መንከባከባቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ባያገኙም የቆዩበት ሁኔታ ጥሩ መሆኑን በመግለጽ አመሥግነዋል፡፡
ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ቢገለጽም፣ ሐሰት መሆኑን ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡ ወደ ቤታቸው የወሰዷቸው ለመቅረፅ ነው ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ከተነገረበት ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ግን በቀን እየተሰጣቸው ያለው አንድ ዳቦና አንድ ስኒ ሻይ መሆኑን፣ ቤተሰቦቻቸው የሚያቀርቡላቸው ምግብ እንዳይደርሳቸው ፖሊስ መከልከሉንም ተናግረዋል፡፡ የታሰሩበት ክፍል አየር የማይገባበት መሆኑን፣ የደም ግፊትና የጨጓራ መድማት (ቁስለት) ሕመምተኛ መሆናቸውን በማስረዳት፣ ዋስትና የማግኘት መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
ወ/ሮ ራህማና አቶ አብዱራዛቅ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ነሐሴ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. መሆኑን አስረድተው፣ ፍርድ ቤት እስከቀረቡበት ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ምግብ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ ራህማ ከመታሰራቸው ባለፈ ያጠፉት ጥፋት ምን እንደሆነ አለማወቃቸውንም አክለዋል፡፡ እሳቸውም የጨጓራና የደም ግፊት ሕመምተኛ መሆናቸውን በመናገር፣ ሕክምናና መድኃኒት እንዲያገኙ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ አብዱራዛቅም ተመሳሳይ አቤቱታ አሰምተው፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የተጠርጣሪዎችን አቤቱታ የሰማው ፍርድ ቤቱ፣ በአዳር ከሰዓት በኋላ ተሰይሞ የመጀመርያ ጥያቄ ያደረገው፣ ‹‹ያለመከሰስ መብቴ አልተነሳም፤›› በማለት ያመለከቱትን የክልሉ መስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሡልጣን መሐመድ ጉዳይን ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ የአቶ ሡልጣን ያለመከሰስ መብት አለመነሳቱንና የተያዙትም በስህተት መሆኑን አስረድቶ፣ ከእስር እንደፈታቸው ያረጋገጠበትን ሰነድ ለፍርድ ቤቱ አሳይቷል፡፡
በመቀጠልም ፍርድ ቤቱ በአዳር የተስተካከለ ነገር ካለ በማለት ተጠርጣሪዎችን ጠይቋቸው፣ አቶ አብዲ የምግብ ችግራቸው መስተካከሉን ተናግረው ጤናቸውን በሚመለከት ግን፣ የእሳቸውን ሕመም ሊያክም የሚችል ሐኪም ሳይሆን ያገናኟቸው ነርሶችን መሆኑን በማስረዳት ተጨማሪ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡
ወ/ሮ ራህማ ግን ምግብ አለማግኘታቸውን ሲያስረዱ ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ጭራሽ አልቀረበልዎትም?›› በማለት ጠይቋቸዋል፡፡ ምግብ ለመቀበል ረዥም ወረፋ ከመኖሩም በተጨማሪ፣ ምግቡ ለሁሉም ስለሚሠራና ጨው ስለሚገባበት እሳቸው የደም ግፊት ሕመምተኛ በመሆናቸው ስለማይመገቡት እንደማይቀበሉ ተናግረዋል፡፡ የታሰሩትም አየር በማያስገባና ንፅህናው ባልተጠበቀ ጠባብ ክፍል ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ አብዱራዛቅም ተመሳሳይ አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡   
ሌላው በጅግጅጋ ከተማ  ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸውና ነሐሴ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር ፍርድ ቤት የቀረቡት፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ፈረሃን ጣሂር ናቸው፡፡ ኮሚሽነሩ የተጠረጠሩት የክልሉን ወጣቶች ‹‹ሒጎ›› በሚባል ስያሜ በማደራጀት ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ሴቶችን በማስደፈር፣ ሕገወጥ መሣሪያ በማስታጠቅ፣ ለዘመናት አብረው የኖሩትን ሕዝቦች በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሳ በመከፋፈል በርካታ ሰዎች እንዲሞቱ፣ የአካል ጉድለት እንዲደርስባቸው፣ ከቀዬአቸው እንዲሰደዱ፣ ሀብት ንብረታቸውን እንዲዘረፍና እንዲቃጠል በማድረግ፣ የሃይማኖት ተቋማት እንዲቃጠሉና ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም በማድረግ መጠርጠራቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ለተጨማሪ ምርመራም 14 ቀናት ጠይቆባቸዋል፡፡ በአስተርጓሚ መርማሪ ቡድኑ ስላቀረበባቸው የተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች አስተያየት የተጠየቁት ኮሚሽነሩ፣ የተጠየቀባቸው የምርመራ ጊዜ ይበዛል ብለዋል፡፡ በእስር ቤት ውስጥ መስገድ እንደተከለከሉ ገልጸው፣ እንዲፈቀድላቸውና የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ሁሉም ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ እንደሚቃወም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በክልሉ የተፈጸመው ወንጀል ውስብስብና ገና ምርመራው ጅምር ነው ብሏል፡፡ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ በክልሉ በመሥራት ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ የወንጀሉ ድርጊቶች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ቃጠሎ፣ ዘረፋ፣ ማፈናቀልና ሌሎችም በመሆናቸው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 እና ሌሎች አንቀጾችን ድንጋጌ የሚጥሱ መሆናቸውን አመላካች በመሆኑ፣ ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ አስረድቷል፡፡ የተጠርጣሪዎቹን አያያዝ በሚመለከት በሰጠው ምላሽ፣ ስለአቶ አብዲ የሚያውቀው በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ከነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንጂ፣ ከዚያ በፊት የት እንደነበሩ የሚያውቀው እንደሌለ አስረድቷል፡፡ ምግብን በሚመለከት ተቋሙ ለተጠርጣሪዎቹ የተለየ ምግብ እንደማያዘጋጅ፣ ነገር ግን እንደ ማንኛውም እስረኛ የተዘጋጀውን ምግብ እያቀረበላቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ለእነሱ ቤተሰቦቻቸው የሚያቀርቡላቸው ከሆነ ተቀብሎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑንም አክሏል፡፡ ከጤና ጋር በተያያዘ የፌዴራል ፖሊስ የጤና ባለሙያዎች (ነርሶች) እንዳሉና በእነሱም እየታዩ መሆናቸውን ጠቁሞ፣ ተጨማሪ ሕክምና ካስፈለጋቸው ሪፈራል ሆስፒታል ስላለው ከኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው እንዲታከሙ እንደሚያደርግ አስረድቷል፡፡ የታሰሩበትን ክፍል በሚመለከት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተዋሰው ሕንፃ ውስጥ መታሰራቸውን ጠቁሞ፣ ሌሎች እስረኞች እንደታሰሩት እነሱም መታሰራቸውን፣ ነገር ግን ንፁህ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ እንደገለጸው፣ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ከባድ፣ ውስብስብና ገና ጅምር መሆኑን ተረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የነበሩበትን ኃላፊነትም ከግምት ውስጥ በማስገባት መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተገቢ መሆኑን በማመኑ፣ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የተጠየቀውን 14 ቀናት መፍቀዱን አስታውቋል፡፡ የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን እንዲወጡ በታሰሩበት ቢሰግዱ እንዳይከለከሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሌሎቹ ተጠርጣሪዎችም ያቀረቡት አቤቱታ ተስተካክሎ እንዲቀርብ ለመስከረም 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ከሁለት ወራት በፊት በደቡብ ክልል የጨምበላላ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሲዳማና በወላይታ ማኅበረሰቦች መካከል ለተፈጠረው ግጭት ምክንያት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ፣ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ 100 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሥርቷል፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ግጭት ከአሥር በላይ ሰዎች መሞታቸውና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ለመፈናቀላቸው ምክንያቱ የተከሰሱት ተጠርጣሪዎች መሆናቸውን፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለተዘዋዋሪ ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡ በክሱ የክልሉ ማረሚያ ቤት ኃላፊና ሌሎች አምስት ሠራተኞች ተካተዋል፡፡   

Source:Reporter

LinkedIn

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa