ኢንጂነር ስመኘው ራሳቸውን እንዳጠፉ የምርመራ ውጤቱ እንደሚያመላክት ፖሊስ ገለፀ

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በሰው በደረሰባቸው ጉዳት ህይወታቸው እንዳላለፈና ራሳቸውን እንዳጠፉ የምርመራ ውጤቱ እንደሚያመላክት ፖሊስ ገለፀ።
ፖሊስ የኢንጂነር ስመኘውን አሟሟት በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፥ ኢንጅነር ስመኘው ራሳቸውን ማጥፋታቸውን የተደረገው የምርመራ ውጤት ያመላክታል ብሏል።
ፖሊስ በመግለጫው ሞተው የተገኙበት መኪና ውስጥ የተገኘው ሽጉጥም በእርሳቸው ስም ተመዝግቦ የሚገኝ መሆኑን ገልጿል።
በፎረንሲክ ምርመራ በተገኘው ውጤት መሰረትም የሽጉጡ ቀልሃና የተገኘው እርሳስም የዚሁ ሽጉጥ መሆኑን ፖሊስ እንዳረጋገጠ አስታውቋል።
ኢንጅነሩ ከመሞታቸው ቀደም ብሎ ባለው ቀን ባደረጉት የስልክ ልውውጥ፥ በአብዛኛው የስንብት ይዘት ያለው መልዕክትን ከልጃቸውና ፀሃፊያቸው ጋር ተለዋውጠዋልም ነው ያለው ፖሊስ።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ለፀሃፊያቸው ልጀን አደራ የሚል መልክዕክት ማስተላለፋቸውን የፌደራል ፖሊስ ጀኔራል ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ተናግረዋል።
በሞቱበት ዕለት ማለዳ ላይም ለአንደኛው ሾፌራቸው ፖስታ በመስጠት ለማን እንደሚያደርስላቸው እነግርሃለው ማለታቸውን እና ለሌላኛው ሾፌር ደግሞ ፖስታ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንዲያደርስላቸው መስጠታቸውም በመግለጫው ተነስቷል።
በዕለቱ ማለዳ 2 ሰዓት ከ30 ላይ ለፖሊስ የኢንጅነሩ መሞት መረጃ ደርሶት ከ10 ደቂቃ በኋላ በስፍራው ደርሷል።
በወቅቱም ፖሊስ ስፍራው ሲደርስ መኪናው ሞተሩ እንዳልጠፋና አራት በሮቹ ተቆልፈው ማግኘቱን አስታውቋል።
ኢንጅነሩ በህይዎት መኖር አለመኖራቸውን ለማረጋገጥም የእጅ ጓንት በመጠቀምና የመኪናውን መስታዎት በመስበር በሩን መክፈት ተችሏልም ነው ያለው።
መኪናው ከተከፈተ በኋላም ኢንጅነር ስመኘው ጥይቱ በቀኝ ጆሮ ግንዳቸው ገብቶ በግራ በኩል እንደወጣ የምርምራ መረጃውን ዋቢ አድርጎ ገልጿል።
አሟሟታቸውም በራሳቸው ሽጉጥ ራስን የማጥፋት መሆኑን የተደረጉ የፎረንሲክና የህክምና የምርመራ ውጤቶች እንደሚያመላክቱም ተገልጿል።
በምርመራ ሂደቱ ወቅትም ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና ከተሽከርካሪው ጋር በተያያዘም ከሞኤንኮ ጋር በትብብር መስራቱንም ነው ያስታወቀው።
ይህም ያደረጉትን የስልክ ጥሪ ልውውጥና በሞቱበት ወቅት ተሽከርካሪው ሞተሩ ሳይጠፋ ተቆልፎ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ ያሉ መረጃዎችን ለማጣራት የተደረገ ነው ተብሏል።
ፖሊስ በመግለጫው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ መጓተት ለኢንጅነር ስመኘው ሞት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ግምቱን አስቀምጧል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከሞታቸው ጀርባ ያሉ ጉዳዮችን የምርመራ ቡድኑ እያጣራ መሆኑን ጠቅሶ፥ ሙያዊ በሆነ መንገድ የሚካሄደው ምርመራ እንደተጠናቀቀም ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ ይሆናሉ ብሏል።
በኢንጅነር ስመኘው የቀብር ስነ ስርዓት ወቅት በመኖሪያ ቤታቸው የተፈጸመው ዝርፊያም መደበኛ የሚባል ዝርፊያ መሆኑንም በመግለጫው አንስቷል።
ዝርፊያው ከውጭ ሃገር በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ለመገኘት የመጡ ዘመዶቻቸው እቃዎቻቸውን ባስቀመጡበት ክፍል ስለመፈጸሙም ጠቁሟል፤ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመጥቀስ።
በተያያዘ ዜና በሰኔ 16ቱ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በመስቀል አደባባይ ስለተፈጸመው የቦምብ ጥቃት አሁን ላይ ምርመራ እየተደረገ ከመሆኑ አንጻር ዝርዝር መረጃ እንደማይሰጥም አስታውቋል።

Source:FBC

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa