‹‹ለረዥም ጊዜ አልመንና አስበን የጀመርነው ትግል በትንንሽ ሙከራዎች እንደማይደናቀፍ በጉባዔያችን ተረጋግጧል››

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኦዴፓ ሊቀመንበር
ከመስከረም 8 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በጅማ ከተማ ዘጠነኛው ጉባዔውን ያደረገው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በመሸጋገር፣ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ በኦዴፓ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት ያስተላለፉት የኦዴፓ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የፓርቲው ጉባዔ ለረዥም ጊዜ ታስቦበትና ታልሞበት የተጀመረው ትግል በትንንሽ ሙከራዎች እንደማይደናቀፍ ማረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡  
የድርጅቱ ሊቀመንበር ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድርጅታችን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ስሙን፣ ዓርማውን፣ ሕገ ደንቡን፣ አመራሩን፣ አመለካከቱንና አደረጃጀቱን 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠይቀውን አመራር ለመስጠት በሚያስችለው ደረጃ ላለፉት አራት ቀናት በውቢቷ ከተማ ጅማ ያደረገው ዘጠነኛው ጉባዔ በድል ተጠናቋል፤›› ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ስሙንና ዓርማውን ቀይሮ ብቻ ከዚህ ጉባዔ የሚወጣ የመሰላቸው በርካታ ሰዎች ቢኖሩም፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ ላለፉት ሦስት ዓመታት የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው ሲያገለግሉ ከነበሩ 81 ሰዎች መካከል አዲሱን አመራር እንዲቀላቀሉ ጉባዔው የጠቆማቸው 19 አባላት ብቻ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለአዲሱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ለማለፍ የቻሉት 16 ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ድርጅቱ የተማሩ፣ ለመምራት የተዘጋጁና ብቃት ያላቸው ወጣቶች ወደፊት በማምጣት ስያሜውን ብቻ ሳይሆን፣ የአመራር ብቃቱን ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለመውሰድ በሚያስችል ቁመና ራሱን ያዘጋጀና ያደራጀ በመሆኑ፣ ሌሎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታገሉ ድርጅቶች በሙሉ ከኦዴፓ ትምህርት በመውሰድ አዲሱ ኃይል በግጭት ጊዜ ደም የሚያፈስና ድንጋይ የሚወረውር ብቻ ሳይሆን፣ አመራር መስጠት የሚችል መሆኑን ወጣቱን በተግባር በማመን እንደሚያረጋግጡ ተስፋ አለኝ፤›› ብለዋል፡፡
ድርጅታቸው በቅርቡ የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ያደረጉትን ገድል በታላቅ አድናቆት ይመለከተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹የጋሞ ሽማግሌዎች ኢትዮጵያ ሽማግሌዎች እንዳሏት፣ ወጣቶች ዛሬም ባህላቸውን እንዳልረሱና ሽማግሌዎችን እንደሚሰሙ፣ ሰው ከመግደል ይልቅ ሰውን በማቀፍና ባለመግደል ማሸነፍ ስለቻሉ የእነሱን አርዓያ የሚከተሉ ሌሎች ሽማግሌዎች እንዲበዙ፣ የወጣቶቹን ምሳሌ ተከትሎ ታላቆቹን የሚያክብር ወጣት እንዲበዛ፣ ጉባዔያችን ለጋሞ ሕዝብ ያለውን አድናቆት በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይፈልጋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚህ ጉባዔ የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ባህሉ ዛሬም ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለኢትዮጵያ ልማትና ኢትዮጵያን ለመገንባት ኃላፊነት ያለበትና በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑን በዝርዝር ተወያይተን፣ በክልላችን ብሎም በአገራችን የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች ሕግን በተከተለና ብልህ በሆነ አመራር እየፈታን አሁን ያጋጠመውን ለውጥ ወደፊት የምንወስድ እንጂ፣ በማንኛውም ሙከራ ተቀልብሰን ለውጡን የማናቆም መሆኑን ጉባዔው በታላቅ አንክሮ አስምሮበታል፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
‹‹ለውጡ የሚደናቀፍና ሸብረክ የምንል መስሏቸው ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ የጥፋት ኃይሎችም ምክር ሰጥቷል፤›› ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ምክሩም ለረዥም ጊዜ አልመንና አስበን የጀመርነው ትግል በትንንሽ ሙከራዎች የማይደናቅፍ መሆኑንና ድሉንም ያገኘነው በደም፣ ሰላማችንንም የምንጠብቀው በደም እንደሆነ ጉባዔው አረጋግጧል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲዎች፣ በተለያዩ በዓላትና በተደራጁ የሚዲያ ሰዎች በአማራና በኦሮሞ ሕዝብ መካከል የሚደረገው የመከፋፈል ሐሳብ፣ በሲዳማና በወላይታ ሕዝብ መካከል የሚደረገው የመከፋፈል ሐሳብ፣ በሶማሌና በኦሮሞ መካከል የሚደረገው ከንቱ የመከፋፈል ሐሳብ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ ካለመረዳት የመነጨ የማይሳካ ድካም ነው፡፡ አማራና ኦሮሞ፣ ሱማሌና ኦሮሞ፣ ሲዳማና ወላይታ ዛሬም እንደ ትናንቱ አንድ ሆነው ኢትዮጵያን የሚገነቡ ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸውንና እነሱ የማይጣሉ መሆናቸውን አውቃችሁ ሌላ አዲስ ታክቲክ እስክትፈጥሩ ድረስ፣ በዚህኛው ታክቲክ በከሰረ መንገድ ገንዘባችሁንና ጊዜያችሁን እንዳታባክኑ ምክር ሰጥተዋል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
‹‹በመጨረሻም ጉባዔተኛው በኦሮሞ ሕዝብ ከወንድም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በፍፁም ፍቅርና መከባበር አንድ ሆነን የጀመርነውን ሰላም፣ የጀመርነውን ልማት የምናስቀጥል እንጂ ልጅ እያሱ ሞክረው እንደከሸፈባቸው፣ በ1966 ዓ.ም. መንግሥቱ ሞክሮ እንደከሸፈበት፣ በ1983/84 ዓ.ም. ኢሕአዴግም ሞክሮ እንደከሸፈበት እኛ የማይከሽፍብን የዴሞክራሲ ጉዞ መሆኑን የሚያረጋግጥና ለዚያም መፍትሔ የሚሆን አቅጣጫ ጉባዔተኛው በዝርዝር መክሮ ያስቀመጠ መሆኑን፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላበስር እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ጉባዔተኛው ኢትዮጵያን የምንሥለው እንደ ችቦና ደመራ ነው ብሏል፡፡ አንድ ጭራሮ ብቻውን ችቦ ሊሆን አይችልም፡፡ ብዙ እንጨቶች ተደምረው አንድ ችቦ ይሆናሉ፡፡ አንድ እንጨትም ደመራ ሊሆን አይችልም፡፡ ብዙ እንጨት ተሰብስቦ ደመራ ይሠራል፡፡ ከፊታችን የክርስትና እምነት ተከታዮች የመስቀል በዓል ያከብራሉ፡፡ እኛ እንደ ችቦና ደመራ ተሰብስብን የምናምር፣ የምንዘልቅና የምንሻገር ሕዝቦች ስለሆንን አንድነታችንን ለመናድ የሚሞክር ማንኛውንም ኃይል በጋራ የምንመክትና ኢትዮጵያችንን በሰላምና በልማት በጋራ የምናስቀጥል መሆኑን ጉባዔተኛው መክሮ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ስላቀረበ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ መጪው ዘመን በደምና በፍርኃት የምንናጥበት ሳይሆን፣ በአንድነትና በመደመር የምንሻገርበት እንደሆነ በድጋሚ ለማብሰር እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡   
የኦዴፓ ጉባዔ እሳቸውን በድጋሚ ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ምክትል አድርጓል፡፡ ሁለቱም እስከሚቀጥለው ጉባዔ ድረስ ፓርቲውን ይመራሉ፡፡
ፓርቲው ዘጠኝ አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመረጠ ሲሆን፣ እነሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ አቶ አዲሱ አረጋ፣ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው፡፡ ለማዕከላዊ ኮሚቴ በአብዛኛው ወጣቶች ያሉበት 55 አባላት ሲመረጡ፣ ከእነዚህ መካከል 45 አባላት በኢሕአዴግ ምክር ቤት የሚሳተፉ ናቸው፡፡
የቀድሞ የኦሕዴድ 14 መሥራችና ነባር አባላት በክብር እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ ከእነሱም መሀል ታዋቂዎቹ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ አቶ ሽፈራው ጃርሶ፣ አቶ ደግፌ ቡላና ወ/ሮ ጊፍቲ አባሲያ ሜዳሊያና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸው ተሸኝተዋል፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት የኦሮሚያ ገዥ ፓርቲ ሆኖ የቆየው ኦሕዴድ በአሁኑ መጠሪያው ኦዴፓ፣ ከክልሉ ብሎም ከኢትዮጵያ አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ ጠንካራ ፓርቲ ለመሆን ዓላማ ይዞ መነሳቱን አስታውቋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን እንገነባለን፣ አፍሪካን እንገነባለን፣ ማንም ኃይል ከዚህ ሊያስቆመን አይችልም፤›› በማለት በጉባዔተኛው ፊት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ናቸው፡፡  

source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman