የዜጎችን መብትና ነፃነት አፋኝ ነው የተባለው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ........

የዜጎችን መብትና ነፃነት አፋኝ ነው የተባለው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ እንደገና እንዲቀረፅ ጥያቄ ቀረበ

በምርጫ 97 ማግሥት የወጣው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን መብት፣ ነፃነትና አጠቃላይ እንቅስቃሴን አፋኝና ገዳቢ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ተሰርዞ ውይይት ተደርጎበት መቀረፅ እንዳለበት ተገለጸ፡፡
ከሁለት ወራት በፊት የተቋቋመው የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ረቡዕ ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ እንደተገለጸው፣ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የተቀረፀውና በሥራ ላይ እንዲውል የተደረገው በዓለም ላይ ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው አገሮች ቃል በቃል ተወስዶ መሆኑ የተነገረ ቢሆንም፣ የአገሪቱን ሕዝቦች ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዬ ደንደአ እንደገለጹት፣ የአገሪቱ ሕዝቦች ስለሕጉ አስፈላጊነት፣ ጥቅምና ጉዳት ማወቅ አለባቸው፡፡ ግንዛቤ ወስደውም ሐሳባቸውን ማንፀባረቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ሕጉ ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው አገሮች እንደተወሰደ ቢነገርም፣ ሕዝቡ ውይይት ስላላደረገበት እንደገና ውይይት ተደርጎበት መቀረፅ፣ አተገባበሩንና አፈጻጸሙም መታወቅ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የአፈጻጸም ችግር እንዳለበት የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ጠበቆችና ዳኞች ውይይት አድርገውበት ችግሩ መቀረፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሕጎች ሲቀረፁ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ በመሆን መብቶችን የሚያሰፉ፣ ችግሮችን የሚቀርፉ፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ፣ የዓለም ምርጥ ተሞክሮዎችን ያካተቱና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው አክለዋል፡፡ ይኼንንም ለማድረግ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸው የሕግ ምሁራን የተካተቱበት ጉባዔ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ሕጉ ፈጥኖ መቀረፅ ወይም መሻሻል ያለበት አገር አቀፍ ምርጫ እየደረሰ በመሆኑ፣ የሕዝብ እሮሮ ያለበት መሆኑንና ኅብረተሰቡም በቂ ውይይት ማድረግ ስላለበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሕጉ በጣም የተለጠጠና ሰፊ የሆነ ትርጉም እንዲኖረው በመደረጉ የዜጎችን መብትና ነፃነት ለመግፈፍ የዋለ መሆኑን የገለጹት፣ የጉባዔው ጸሐፊና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ አጥኚ ቡድን አስተባባሪ ጌዴዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የቡድን አስተባባሪው እንዳስረዱት፣ አዋጁ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅና ከለላ ለማድረግ የሚችሉ አንቀጾችን አላካተተም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት መብቶችን በሚያጣብብ ሁኔታ የተቀረፀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አተገባበሩም ችግሮቹን ይበልጥ የሚያባብስ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ዜጎች የሚቀርብባቸውን ክስና መረጃ ዓይተውና ተጋፍጠው ለመሟገት፣ እንዲሁም ራሳቸውን ከተመሠረተባቸው ክስ ለመከላከል በሚያመች ሁኔታ የተቀረፀ አለመሆኑን ጌዴዮን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ ፍትሐዊ የሆነ የፍርድ ሒደት ለማግኘት የሚችሉበትን አካሄድ በሚያጣብብ ሁኔታ የተቀረፁ የሕግ አንቀጾችና ድንጋጌዎች መሆናቸውን አጥኚ ቡድኑ መረዳቱን ጠቁመዋል፡፡ ሕጉ ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው አገሮች የተወሰደ መሆኑን ሕጉን ያወጡት አካላት የተናገሩ ቢሆንም፣ ‹‹አንድ ዓረፍተ ነገር መውሰድ የእነዚያ አገሮች ተሞክሮና ልምድ ሙሉ በሙሉ ወይም በበቂ ሁኔታ ወስደናል ለማለት አያስደፍርም፤›› ብለዋል፡፡
የተወሰደው አንቀጽ የአገሪቱን ተቋማዊ ዓውድ ግንዛቤ ውስጥ ላያስገባና የአንድን አገር ምርጥ ተሞክሮ ወስደናል ማለት እንደማይቻልም ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ተቋማዊ ዓውድ ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ድንጋጌዎቹ ተወስዶባቸዋል የተባሉት አገሮች በዚያው የቆሙ ሳይሆን፣ ባወጡት ሕግ ላይ ቀጣይ ውይይትና ክርክር በማድረግ ኢትዮጵያ የወሰደቻቸውን አንቀጾች ማሻሻላቸውን የቡድን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቶቻቸውም አተረጓጎማቸውን ማሻሻላቸውንም አክለዋል፡፡ በአጠቃላይ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ችግር አተገባበሩ ብቻ ሳይሆን አቀራረፁ፣ ይዘቱና አፈጻጸሙ በመሆኑ ከሕገ መንግሥታዊ መሠረታዊ የሰው ልጆች ነፃነቶችና መብቶች አንፃር በርካታ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑም በአጥኝ ቡድኑ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡
አንድ ሕግ ሲወጣ መታየት ያለበት ተግባራዊ የሚሆንበትን አጠቃላይ ዓውድ፣ ተቋማዊ ዝግጅት፣ የሕግና የፖለቲካ ባህልን ታሳቢ ባደረገ መንገድ መቀረፅና መዘጋጀት እንዳለበት ጌዴዮን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ የሕግ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ሊወያዩበት፣ ሊከራከሩበትና ሐሳባቸውን ሊሰጡበት ስለሚገባ በአዋጁ ላይ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በባህር ዳር፣ በሐዋሳና በመቀሌ ከመስከረም 7 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ውይይት እንደሚደረግና ግብዓትም ይገኛል የሚል ተስፋ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ አዋጁን ለመገምገም የተዋቀረው ቡድን አዋጁ ያሉበትን ክፍተቶች ከማጥናት ባለፈ አዲስ ረቂቅ ሕግ አለመዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
ሌላው በተለይ የዜጎችን የመደራጀት መብት ገፏል የተባለውና ከምርጫ 97 በኋላ የፀደቀው አዋጅ ቁጥር 621/2001 ሲሆን፣ አዋጁን ሙሉ በሙሉ ሊያስቀይሩ የሚችሉ 40 አንቀጾች መለየታቸው ተነግሯል፡፡ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ የሚያጠናው ቡድንን የሚያስተባብሩት የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል እንደተናገሩት፣ አዋጁ ሲቀየር ከስሙ ይጀምራል፡፡
 ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ›› መባል እንዳለበት አጥኝ ቡድኑ ሐሳብ ማቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ ነባሩ አዋጅ ድርጅት የሚመሠርቱ ሰዎች የፋይናንስ ምንጫቸው ከውጭ ከሆነ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ላይ እንዳይሠሩ የሚገድብ ቢሆንም፣ በአዲሱ አዋጅ ገደብ እንዳይጣልበት መደረግ እንዳለበት ቡድኑ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ሌሎች ገደብ የተጣለባቸው ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ገንዘብ የማግኘት መብት፣ የተሳትፎና የሥራ መመርያ፣ ወዘተ በአጠቃላይ ከ40 በላይ የሕጉ አንቀጾች ገደብ እንዳይኖራቸው ተደርጎ ሐሳብ መቅረቡን አቶ ደበበ አስረድተዋል፡፡
በአዋጁ ላይ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም.  ሁሉን አሳታፊ ውይይት በአዲስ አበባ መጀመሩንና በአዳማ፣ በባህር ዳር፣ በሐዋሳና በመቀሌ እስከ መስከረም 10 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ 

Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman