አሜሪካ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ላለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኗን አስታወቀች
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው ለውጥ ረዥም በሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ አምባሳደር ራይነር ይህን የተናገሩት የአሜሪካ ኤምባሲ፣ አይሬክስና የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በጋራ በአዳማ ከተማ ለአንድ ሳምንት ያዘጋጁት የጋዜጠኞች ሥልጠና ማብቂያ ላይ በክብር እንድግድነት ተገኝተው ለሠልጣኞች ሰርተፊኬት በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አምባሳደር ራይነር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ግልጽ ራዕይ ይዘው መነሳታቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን የአሜሪካ መንግሥት እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ የለውጡ ፍኖተ ካርታ ነዳፊና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንዲመረጡ እንዳደረገች የሚነገረውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ባቀረቡበትና መንግሥት ለውጥ ለማምጣት ወይም ቀደም ሲል በነበረው አስተዳደር ለመቀጠል ምርጫ ባደረገበት ወቅት፣ አሜሪካ በግልጽ እንደተንቀሳቀች ገልጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተመረጡት በፓርቲያቸው እንጂ በአሜሪካ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹አሜሪካ ይህን የማድረግ ሥልጣን የላትም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አሜሪካ ካላት ኃይል በላይ እንዳላት ያስባሉ፤›› ያሉት አምባሳደር ራይነር፣ የአሜሪካ መንግሥት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን የለውጥ አጀንዳ እንደሚደግፍ ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባገኙት ሰፊ ድጋፍ ምክንያት በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መመረጣቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፣ የለውጥ አጀንዳውን ራሳቸው ቀርፀው ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሆኑና የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለደኅንነት መሥሪያ ቤቶች የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ጥናት በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ከበፊቱ አሠራር ተላቆ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ሙያዊ ሥራውን ለማከናወን የሙያዊ ድጋፍ መጠየቁን ጠቁመው፣ የአሜሪካ መንግሥት በቀረበለት ጥያቄ ደስተኛ እንደሆነና አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ ለተቋሙ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
መጪውን ብሔራዊ ምርጫ በተመለከተም የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ በጀት መድቦ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እየገመገመ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አንዱ ችግር ነፃና ግልጽ ምርጫ አካሂዳ አለማወቋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ ወደ መቀሌ በማቅናት በሕወሓት አመራሮችና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ቅራኔ ለመፍታት ሽምግልና መሞከራቸውን አስመልክቶ ለቀረባቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ሥራዬ ሁሉንም ሰው ማናገር እንደሆነ እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና ከአባል ድርጅቶች ጋር እንደሚወያዩ ገልጸው፣ ከወራት በፊት መቀሌን እንደጎበኙና በቆይታቸው ከሕወሓት አመራሮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደተነጋገሩ አረጋግጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ የውይይቱን ዝርዝር አጀንዳና ስላገኙት ውጤት ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹ጠቃሚ ውይይት አካሂደናል፣ የማንኛውንም ውይይት ዝርዝር አልገልጽም፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኢትዮጵያን ወደፊት እያራመዷት እንደሆነ ገልጸው፣ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ እየተሸጋገረች ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየታዩ እንደሆነና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጡን እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የተጋረጡ ፈተናዎችና ሥጋቶች ቢኖሩም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ተቀራርበው ከሠሩ፣ ፈተናዎቹን አልፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚናፍቀውን ዴሞክራሲና ዕድገት ዕውን ማድረግ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
አሜሪካ በኢትዮጵያ ለትምህርትና ለሌሎች ዘርፎች በዓመት በአማካይ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ ታውቋል፡፡
Source:Reporter
Source:Reporter
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ