ትልቅ ህዝብ ትልቅነቱ የሚለካው አመዛዝኖ በመኖሩ
ትልቅ ህዝብ ትልቅነቱ የሚለካው አመዛዝኖ በመኖሩ እና ነገሮችን በእርጋታ መከወን በመቻሉ ነው።ትልቅ ህዝብ ቤተክርስቲያን ተቃጠለችብን ብሎ በምላሹ መስኪድ ላንድድ ብሎ በደቦ አይነሳም።አልያም በእኩይ አላማቸው መስኪድ ያቃጠሉ ሰዎች በሚኖሩ ጊዜ ማጣፊያው ቤተክርስቲያን ማቃጠል ነው ብሎ አያምንም።
ለውጡ ፍፁም የራስ ምታት የሆነባቸው እና የታለመለትን ግብ እንዳይመታ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሀይሎች ለውጡን ለመቀልበስ እና አሁን ያለው የለውጡ አመራር ሀገር መምራት አልቻለም የሚል አንድምታ በመፍጠር አምባገነንነትን ዳግም በእጅ አዙር ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት ያግዝልናል ብለው የሚያስቡት የተለያዩ አጀንዳዎችን በመቅረፅ ብጥብጦችን ማስነሳት እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ላለፉት 8 ወራት በማንነት፣በወሰን፣በመልካም አስተዳደር፣ጉዳዮች ላይ የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት የብጥብጥ አጀንዳዎችን ቀርፀው በመንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥፋቶችን አድርሰዋል።
በርካቶች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፣የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል፣የበርካቶች ንብረት ወድሟል።በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በለውጡ ምክንያት ከ3 ሚሊዮን ዜጎች በላይ ተፈናቅለውባታል ብለው መንግስት ላይ እጃቸውን ይቀስራሉ።ማፈናቀሉን፤ማገዳደሉን አጀንዳችን ነው ብለው ደፍረው አይናገሩም።አላማቸው በሙስና እና በወንጀል በተጨማለቀ እጃቸው ለውጡን ጥላሸት መቀባት ነውና፡፡
እነዚህ እኩያን ኢትዮጵያን ጠንቅቀው ያውቋታል።የትጋር ስትጫር እሳት መፍጠር እንደምትችል ስለሚያውቁ ለአጀንዳቸው ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
ሱማሌ ክልል ላይ በቀኝ እጃቸው ቤተክርስቲያን ላይ ክብሪት ይጭሩና በግራ እጃቸው የሀይማኖት ነፃነት ይከበር የሚል መፈክር ይዘው ይደመጣሉ፣ጎንደር ላይ መስኪድ ያቃጥሉና ህዝበ ሙስሊሙን መንግስት ላይ ሰልፍ ውጣ አንጂ ብለው ይቀሰቅሳሉ፣ ቴፒ ላይ ሰው ያርዱና ሀገሪቷ መንግስት አልባ ሆነች እኮ ምነው ዝም አላችሁ ይላሉ፣ አጥንቷ እስኪቀር የጋጧትን ሀገር ንብረት ማሸሻ መፈናፈኛ ሲያጡ ዶላሯ ሸሸ እኮ ምን ተሻለን የሚል ቅስቀሳ ይጀምራሉ።የሆነው ሆኖ ከጊዜያዊ ግርግር ውጪ ይሄ ነው የሚባል የመንግስትን አቅም ሊፈትን የሚችልና ከአቅም በላይ የሆነ ሁከት እስካሁን ሊከሰት አልቻለም ምክንያቱም የህዝብን ስሜት ለጊዜው ግልፍተኛ ማድረግ እንጂ ልቡን ማግኘት አልቻሉምና።ነገር ግን ህዝብ ቀድሞ ስለማይነቃ አጀንዳቸውን ለጊዜው የተሳካ ያስመስለዋል።
አሁን ደግሞ የያዙት ዋና አጀንዳ የሀይማኖት አጀንዳ ነው ኢትዮጵያውያን በሀይማኖታቸው ላይ ያላቸውን አቋም ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ሌላኛው መኳረፊያ እንዲሆን ይፈልጋሉ።ማምለኪያ ስፍራዎችን ማቃጠል፣መስገጃ ቦታዎችን ማፍረስ፣ አንዱ በአንደኛው ላይ የሀይማኖት ጥቃት እየፈፀመ እንዳለ አድርጎ ማሳየት የአጀንዳቸው አካል ነው።
አንድም ቀን ከቤቱ አጠገብ አዛን ሲጮህ ምቾት ነስቶት የማያውቀውን ህዝበ ክርስቲያን ምን ይሻላል እንቅልፍ ነሱህ እኮ ተነስ እንጂ ይሉታል። በቅዳሴ ድምፅ ሌት መንጋት የሚያውቀውን ጨዋውን ሙስሊም ተበደልክ እኮ እያሉ እረፍት ሊነሱት ላይ ታች ይላሉ።
ጥያቄያቸው የሀይማኖት እኩልነት እና ነፃነት የሚል መፈክር ይኖረውና አላማው 4 ኪሎ ያለችውን ወንበር ህዝብ እንዲነሳባት ማድረግ ይሆናል።ህዝብ ይሄንን ጠንቅቆ ሊረዳና የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ በአጭር ጊዜ ያሳየውን እምርታ ሊደግፍ፣ሊንከባከብ እና ሊጠብቅ ይገባዋል።
እንደ ድርጅትም ሆነ እንደ ሀገር የጀመርነው ለውጥ የሀይማኖት እኩልነትን ማክበር ለኢትዮጵያ የህልውናዋ ጉዳይ እንደሆነ ጠንቅቆ የሚረዳ አና ሁሉም ሀይማኖቶች በእኩልነት የሚስተናገዱባት ሀገር እንድትሆን ትልቅ አጀንዳ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለ ለውጥ ነው፡፡ለዚህም እንደ ማሳያነት በሁለቱ ሲኖዶሶች መሀከል የነበረውን ኩርፊያ በእርቅ ለመቋጨት የተደረገው እንቅስቃሴ እና በሙስሊሙ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እየተደረገ ያለው የንግግር ሂደት ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር የሁላችንም ቤት ናትና በስሜት ተንድተን ሰላሟን የምናደፈርስ ሊሆን አይገባም።የምንሰማቸው መረጃዎች ከጀርባቸው ያዘለውን እኩይ አላማ ማጤን ይኖርብናል።ተጣድፎ በደቦ ሆ ብሎ ከመነሳት ይልቅ ዘመናትን አቻችሎ ያኖረንን መልካም ባህላችንን አስታውሰን ለሁላችንም የምትበቃ በልካችን የተሰፋች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደግፍ።
Source:EPRDF Official facebook page
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ