"ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አፈጉባኤው ከአንድ ፓርቲ መሆን አለበት ብዬ አላምንም"


"ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አፈጉባኤው ከአንድ ፓርቲ መሆን አለበት ብዬ አላምንም" አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሥራ መልቀቂያቸውን ለኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስገቡ የሚለው ዜና ከተሰማ በኋላ እንደገና ወደ ስራቸው ተመልሰዋል።
አቶ አባዱላ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት የሕዝቤ ክብር ተነክቷል ብለዋል። ይህንን ተከትሎም በርካቶች አቶ አባዱላ ወደስልጣናቸው የተመለሱት ተነካ ያሉት የሕዝባቸው ክብር ከምን ደርሶ ነው ሲሉ ይጠይቃሉ።
አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው "እኔ ስልጣኔን ልልቀቅ ስል የጠየኩት ለግላዊ ጉዳይ አይደለም" በማለት የፖለቲካ ስልጣኑም የግል መሻታቸው ሳይሆን የድርጅት ተልዕኮ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ድርጅታቸው ኦህዴድ ኢህአዴግ ተልዕኮ ሰጥቷቸው ባስቀመጣቸው ስፍራ ላይ ግን የሕዝቡን ትግል የሚያሰናክሉ እና ወደኋላ የሚጎትቱ ነገሮች ሲገጥሟቸው ቅር መሰኘታቸውን አልሸሸጉም። እንደሳቸው አባባል በዋነኛነት መለቀቂያቸውን እንዲያስገቡ የተገደዱበት ምክንያት ይህ ነው።
የእርሳቸው የልልቀቅ ጥያቄ ከፓርቲያቸው ወይም ከፓርላማ መቀመጫቸው ሳይሆን ከአፈ ጉባኤነታቸው እንደሆነም ይገልፃሉ። እንደ አቶ አባዱላ እምነት ብዙዎች የተሰዉለት አላማ በእርሳቸው እድሜ ብቻ ሳይሆን "በሚመጡት ትውልዶች እድሜም ተሳክቶ አያልቅም" ይህ ሁለት ሶስት ትውልድ የሚጠይቅ ትግልን ትቶ መሄድ አለመምረጣቸውንም ያስረዳሉ። የመረጣቸውን ሕዝብ አክብረው የመንግስት ሃላፊነትን ይዞ ለመቀጠል የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ እንዳልነበሩ ግን አልሸሸጉም።

ምክንያታቸው ምን ነበር?

እንደ አቶ አባዱላ ከሆነ ከአፈ ጉባኤነቴ ልነሳ ብለው ጥያቄ ካቀረቡበት ምክንያት አንዱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ መካከል የተነሳው ግጭትና መፈናቀል ቀዳሚው ነው። "ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም" ይላሉ አቶ አባዱላ።
ለአቶ አባዱላ የስልጣኔን ልልቀቅ ጥያቄ ሰበብ የሆነው ሌላኛው ምክንያት ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ነው። ይህንንም ለመመለስ የክልሉ መንግስት የኦሮሞ ተወላጅ የግል ባለሃብቶችና ሌሎችም የሚሳተፉበት የኢኮኖሚ አብዮት እንቅስቃሴዎን መጀመሩን ያስታውሳሉ።
ይህ የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት እንቅስቃሴ ግን እንዳሰቡት ውጥኑ በሁሉም ወገን በበጎ አይን አልታየም።
የእርሳቸው እና አብረዋቸው ሃሳቡን በማመንጨት የሚንቀሳቀሱ አካላት ፍላጎት በክልሉ ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር ማስተካከል ቢሆንም ኦሮሞን ብቻ ነጥሎ በኢኮኖሚ ውስጥ ማስገባት በሚል በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት አጣ፤ ተቃውሞም ገጠመው።
በአቶ አባዱላ እምነት ኦሮሞን እና ኦህዴድን ከሚያውቅ ሰው ይህ መምጣት አልነበረበትም። ምክንያቱም ይላሉ ''ኦሮሞ ከሌሎቹ ውጭ አይኖርም ሌሎቹም ከኦሮሞ ውጭ አይኖሩም'' ስለዚህ ይህ መስተካከል አለበት የሚል ጠንካራ እምነት ነበራቸው።
"ኦህዴድ በጦርነት ውስጥ ተፈጥሮ በጦርነት ውስጥ ያደገ ትልቅ ለኢህአዴግ አቅም የሆነ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት መጠናከር አለበት የሚለው ደግሞ የሁሉም እምነት ነው። ነገር ግን ጣልቃ ገብነት ያስቸግረዋል" ይላሉ።
ይህ በየጊዜው የሚገጥመው የግለሰቦች ጣልቃ ገብነት ድርጅቱን እንደተፈታተነውም ይገልፃሉ።
ለዚህ ደግሞ አስረጅ ሲጠቅሱ 2008 መጨረሻ 2009 መጀመሪያ ላይ ኦህዴድ ያካሄደውን ጥልቅ ተሃድሶ ተከትሎ አመራሮቹን ሲቀይር ትልቅ ጫጫታ መፈጠሩን ያስታውሳሉ። በአቶ አባዱላ እምነት ኦህዴድ ያላመነበትን የመሻር፤ ይሰራልኛል ያለውን ደግሞ የመሾም ስልጣን አለው።
ይህንን ማወክ ኦህዴድን ብቻ ሳይሆን አገርንም ይጎዳል ብለው ያምናሉ። አክለውም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆኑ አጋር ድርጅቶች ሲነኩ አገር ይጎዳል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ አቶ አባዱላ።
ስለዚህ ይህን እምነታቸውን የሚያናውጥ ነገር በገጠማቸው ወቅት ቅሬታቸውን ይዘው ለቀድሞው የድርጅቱ ሊቀመንበር ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ። በዚህ ብቻ ሳያበቁ ከአራቱ ፓርቲዎች ሊቀመናብርት እና ምክትል ሊቀመናብርት ጋርም ተወያይቻለሁ ይላሉ።

"ጥያቄዬን ሁሉም በአንድ ድምፅ ተስማማበት እናም በጋራ ሊታገሉበት ተስማሙ።"

17 ቀኑም የኢህአዴግ ስብሰባ ወቅት ሰፊ ውይይት እና ክርክር ተደርጎበት መተማመን ላይ እንደተደረሰ እና በጋራ ተቀባይነት ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ። አቶ አባዱላ ያነሷቸው ጥያቄዎች በሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች ተቀባይነት ካገኘ እና በጋራ ለመታገል ከተስማሙ በኋላ "ችግሮቹ ሲፈጠሩም ነበርኩ ለመፍትሔውም አብሬ መታገል አለብኝ በሚል እምነት ጥያቄዬን አንስቻለሁ" ይላሉ።
መውጣቴም ልክ ነበር፤ መመለሴም ትክክል ነው፤ የሚሉት አቶ አባዱላ ችግሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል፤ ሰው ተሰዶ አሜሪካ ካልገባ የታገለ ስለማይመስለው ነው በማለት ነባሩን የፖለቲካ ባህል ይተቻሉ።
"በኔ እምነት ይህ ስርአት ሲፈጠር ነበርኩ፤ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ታግያለሁ፤ ችግሩ ሲፈጠር እዚሁ ነበርኩ፤ በተፈጠረው ችግር እጄ የለበትም አልልም፤ በማስተካከሉም ማዶ ሆኜ የማማው ሰው መኖር የለበትም። ስለዚህ በማስተካከል ውስጥም እጄ መኖር አለበት።"
ከስልጣናቸው ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ ለምን በመገናኛ ብዙሃን ቀድመው አሳወቁ?
እኔ ኢህአዴግ ሆኜ የታገልኩት ሕዝብ ብቻ ነፃ እንዲሆን አይደለም፤ እኔም ነፃ እንድሆን ነው። የፈለኩትን እንድደግፍ የፈለኩትን እንድቃወም ነው የሚሉት አፈ ጉባዔ አባዱላ፤ የድርጅት ዲሲፕሊን መኖር እንዳለበትም ይስማማሉ።
በመቀጠልም ሕይወቴን የምከፍልለት ድርጅት ስለሆነ ሕይወቴን ለምከፍልበት አላማ ነፃ መሆን ይኖርብኛል በማለት የፈለጉትን ለመቃወም እና ለመደገፍ ያላቸውን ነፃነት ያስረዳሉ።
በኢህአዴግ ውስጥም መቃወም ይቻላል፣ ማስተካከል ይቻላል፣ መታግል ይቻላል ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
አክለውም የወሰዱት እርምጃ ለብዙዎች ድፍረትን የጨመረ እርምጃ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
"ያኔ ይሄንን ለመፍጠር ብዬ አይደለም ያደረኩት ዘግይቼ ሳየው ግን ይህ ተፈጥሯል። ያኔ ከራሴ ጋር ተሟገትኩ። የማልሸከማቸው ነገሮች ሲያጋጥሙ ስልጣን ስለተሰጠኝ ብቻ አንገቴን ደፍቼ የማልፍበት ምንም ፍርሃት የለብኝም፤ ለወደፊቱም አላደርገውም።" በማለት ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ።

በውዥንብር ውስጥ የፀደቀው የአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር

የአቶ አባዱላ ስም ሲነሳ ሌላው አብሮ የሚነሳው ጉዳይ በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው።
አቶ አባዱላ ስለዚህ ድንጋጌ ሲያብራሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለፓርላማ ብቻ አይደለም የቀረበው ይላሉ።
"በመጀመሪያ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ተወያይቶበታል። አስፈላጊነቱንም አምኖበታል።
ቀጥሎ ደግሞ የዘጠኙም ድርጅቶች፤ የአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እና የአምስቱ አጋር ፓርቲዎች መሪዎች፤ የፓርላማ አባላትን ሰብስበው -መደበኛ በሆነ መድረክ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት እና ድርጅቶቹ ያመኑበት መሆኑን አስረድተዋል።" ይላሉ።
በወቅቱም የፓርላማ አባላቱ ከመሪዎቻቸው ጋር መከራከራቸውን እና የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ያስታውሳሉ።
"ስለዚህ በድርጅት አሰራር አልቋል ማለት ነው። ለዚህም ነው ምክር ቤቱን በመግባባት መወሰን ይቻላል በማለት የጠየኩት።" ሲሉ ያክላሉ።
በአፈጉባኤ አባዱላ ግምት የፓርላማ አባላቱ ከድርጅታቸው አቋም አይወጡም የሚል ነበር። ነገር ግን የሕዝብ እንደራሴዎቹ በድምፅ ብልጫ ለመወሰን ጠየቁ።
በድምፅ ቆጠራው ወቅት ስለተፈጠረው ስህተት የተጠየቁት አፈጉባኤ አባዱላ የፓርላማው አሰራር በማብራራት መልሳቸውን ይጀምራሉ።
ማንኛውም የፓርላማ አባል ጠዋት ሲገባ እንደሚፈርም ይህም የፈረመበት እንደሚቀመጥ ያስታወሱት አፈጉባኤው ይህ ለአመታት የዘለቀ የምክር ቤቱ አሰራር እንደሆነ ያስረዳሉ። ለእርሳቸው ያን ቀን የሆነውም እንደዛ ነው።
"በእለቱ ከሚፈለገው በላይ የህዝብ እንደራሴ ነው የተገኘው፤ 495" ይላሉ። ስለዚህ የምክር ቤቱ ኮሚቴው በወሰነው መሰረት 2/3 የሚለውን ከተገኘው ሳይሆን ከምክር ቤቱ አባል ስለሆነ፤ ከተገኙ የፓርላማ አባላት የተቃወሙና ድምፃቸውን ያቀቡ ተቀንሰው 2/3 ኛውን ሞልተዋል ይላሉ።
"እንዲህ አይነት መድረኮች ክርክር የተሞላባቸው ናቸው። እነዚህ ክርክሮች መድረኩን የሚመራውን ሰው ይፈታተኑታል። በሚገባ ማከራከር፣ ለሁሉም ተገቢውን እድል መስጠት፣ አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል።" በማለት የስራውን ከባድነት የሚናገሩት አቶ አባዱላ "አፈ ጉባኤ ብሆንም የራሴ ሀሳብ አለኝ፤ የራሴ ሃሳብም ይፈታተነኛል" በማለት በወቅቱ የነበሩበትን አካላዊና ሕሊናዊ ሁኔታ ያስረዳሉ።
በእርግጥ የምክር ቤት አባላቱን የመቁጠር እና የደገፉ የተቃወሙ እና ተአቅቦ የዳረጉ ሰዎችን ቁጥር ማሳወቅ የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት ሰራተኞች ስራ ነው። ታዲያ እርስዎ እንዴት ተሳሰቱ ለሚለው ጥያቄም ሲመልሱ "ቁጥሩን ይዘውታል፤ ግን ሲነግሩኝ ተሳሳቱ፤ ካወጅኩት በኋላ ወዲያውኑ የቁጥር ስህተት መኖሩን አረጋገጥኩኝ። የምክር ቤት አባላቱን መዶሻ መትቼ ተመለሱ ማለት አልችልም። ማድረግ የምችለው ቁጥሩን ማስተካከል ነው። ወዲያውኑ አስተካከልኩኝ" ብለዋል።
የተሳሳቱት ቆጥረው የነገሩኝ የፅህፈት ቤት ሰራተኞች ናቸው የሚሉት አፈጉባኤ አባዱላ ጥፋቱን ግን ወደ ሙያተኞቹ ማስተላለፍ ተገቢ ነው ብለው አያምኑም።
"ጊዜ ቢወስድም እኔ ነበርኩ እየደመርኩ እና እየቀነስኩ ማረጋገጥ የነበረብኝ። ለዚህ ነው በቴሌቪዥን ቀርቤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ የጠየኩት" ብለዋል።
አንዳንድ ሰዎች ያልነበረ ቁጥር ነው ለሚሉትም ሲያስረዱ ያንን ለማድረግ የሞራል ግዴታቸውና የፈፀሙት ቃለመሃላ እንደማይፈቅድላቸው ይገልፃሉ።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር

አፈ ጉባኤ አባዱላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እና አቶ ለማ መገርሳን ከልጅነት ጀምሮ እንደሚያውቋቸው ይናገራሉ።
ሁለቱም ግለሰቦች ኦህዴድ ባለፈባቸው ውጣ ውረዶች ውስጥ ተፈትነው ያለፉ መሆናቸውን ይመሰክሩላቸዋል። "እነዚህ ጓዶች በነበረው ውጥንቅጥ ውስጥ እየተሳሉ፤ እያደጉ እና እየተጠናከሩ የመጡ ናቸው።" ሲሉም ይገልጿቸዋል።
ከአቶ ለማ እና ከአቶ አብይ ብዬ ለማወዳደር እቸገራለሁ የሚሉት አፈ ጉባኤ አባዱላ፤ ሁለቱም ምርጥ ታጋዮች መሆናቸውን ይመሰክሩላቸዋል። "ለዚህ በኦህዴድ አመራር ውስጥ የተደረገውን የስልጣን ቅብብሎሽ ማየት በቂ ነው። ለኔ እገሌ ከእገሌ ይበልጣል ብዬ ሳይሆን የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ናቸው ብዬ ነው የማስበው።"
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ባህሪያቶች ሲገልጹም "በጣም ተማሪ የለውጥ ሰው፣ ወደኋላ ብዙ የማይመለከቱ፣ ፈታኝ ነገር የማያቆማቸው" ይሏቸዋል።
አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ውጤታማ ስራ ይሰራሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል። "/ አብይ ሲመረጥ በሕይወቴ ከተደሰትኩባቸው ሶስት ቀኖች አንዱ ነው" በማለት ያላቸውን ተስፋና መተማመን ይገልፃሉ።
ለደስታቸው ሰበብ የሆነውም / አብይ ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውና ከኦህዴድ የተገኙ መሆናቸው እንደሆነ ይገልፃሉ።

አሁንስ ከአፈ ጉባኤነት አይነሱም?

ኦህዴድ በስራ አስፈፃሚውም ሆነ በሕግ አውጭው ውስጥ አሉ የሚባሉ ቁልፍ ስልጣኖችን ይዟል። በፓርላማውም ውስጥ አብላጫው መቀመጫ የኦሮሞ ነው። ይህንን ፓርላማ የሚመሩት አፈጉባኤ አባዱላም የተገኙትም ከኦህዴድ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ በመሆኑ የመንግሥትን የሥራ አፈጻጸም፣ የሕጎች አተገባበርና የበጀት አጠቃቀም ጉድለቶችን በመለየት ሥራ አስፈጻሚውን መከታተልና መቆጣጠር ላይ አድልኦ ይፈፀማል ብለው አያምኑም አፈጉባኤ አባዱላ። እንደውም ምንም አይነት አድልዖ አይፈፀምም ይላሉ። ግን ሀገራችን በፌደራላዊ ስርዓት የምትመራና ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉባት ሀገር በመሆኗ ከተለያዩ ብሔሮች ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወከሉ ሰዎች የተለያዩ ኃላፊነቶችን ቢይዙ መልካም ነው ብለው ያምናሉ። "ጠቅላይ ሚኒስትር እና አፈጉባኤ ከአንድ ፓርቲ መሆን አለበት ብዬ አላምንም ሽግሽግ መደረግ አለበት ብዬ አምናለሁ። ይሄ መስተካከል ይኖርረበታል። ድርጅቱም ይህንን ያደርጋል ብዬ አምናለሁ።" ይላሉ።

ማሕበራዊ ሚዲያና አባዱላ

ማህበራዊ ሚዲያዎችን የማይከታተሉት አፈ ጉባኤ አባዱላ በዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎች ግን ምን እንደተባለ ዘወትር ይነግሯቸዋል። "ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያ እንዲህ ብለዋል ሲሉኝ እኔ በማህበራዊ ሚዲያ የሚገነባ ስምም የሚጠፋ ማንነትም የለኝም እላለሁ" ይላሉ።
ማህበራዊ ሚዲያ አንድ ቀን ያነገሰውን በማግስቱ ያረክሳል የሚሉት አቶ አባዱላ "እኔ በአግባቡ ከሚሽረኝ ሕዝብ ጋር ሲሾመኝም ማንነቴን አውቆ ከሚሾመኝ ሕዝብ ጋር መኖርን እመርጣለሁ" ይላሉ። የኔ ማንነት በደምና ታሪክ ተገንብቷል የሚሉት አቶ አባዱላ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለእርሳቸው ከሚወሩ ነገሮች መካከል የሰሙት በእርሳቸው ስም የሚጠራውን መኪና ብቻ ነው።
Source:BBC/amharic

 Hub:Barreeffamoota fuula kana irratti argaman hunda dubbisuuf gubbaa irraa"Diinni diina caalu hiyyummaadha" mata duree jedhu cuqaasaa.
Hirmaannaa taasiftaniifi barreeffamakoo irratti yaada kennitaniif akkasumas like waan jettaniif galatoomaa,hirmaannaan keessan cimee itti haafufu.

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa