በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የተደረሱ ስምምነቶች ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለማደግ ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል - ምሁራን
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት ሀገራት ባደረጉት ጉብኝት የተደረሱ ስምምነቶች ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለማደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።
ምሁራኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ኢትዮጵያ በጅቡቲ እና ሱዳን ወደቦች ላይ የራሷ ድርሻ እንዲኖራት ከስምምነት ላይ መደረሱ የሀገሪቱን ወጪ እና ገቢ ንግድ የሚያሳደግና ለኢንቨስትመንት ፍሰት የራሱ አስተዋፅኦ ያለው ነው ብለዋል።
ዋና ትኩረቱን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ባደረገው በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የሀገራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ውስጥ ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት ውስጥ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት ይሰጣል።
ዶክተር በለጠ በላቸው በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ዙሪያ በሚያተኩረው ውይይትና የጥናት ትብብር ማዕከል ወይም ሴንተር ፎር ዲያሎግ ኤንድ ሪሰርች ኮኦፕሬሽን ውስጥ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት ተመራማሪ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት መስጠታቸውም አብዛኛው የሀገሪቷ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጥቅሞች የተሳሰሩት ከጎረቤት ሃገራት ጋር በመሆኑ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅቡቲ እና በሱዳን ባደረጓቸው ጉብኝቶች ከመሪዎች ጋር ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት ወደቦች የራሷ ድርሻ እንዲኖራት ለማድረግ ተስማምተዋል።
ይህን አካሄድ በቅርበት የሚከታተሉት ዶክተር በለጠ ሰሞነኛውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጎረቤት ሀገራት ጉብኝት ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር ብለውታል።
እንዲሁም አሁን ባለው የመነሳሳት መንፈስ መሰረት ትብብሩ የሚቀጥል ከሆነም ተግባራዊ እንደሚሆን ይናገራሉ።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኮሌጅ ምክትል ዲን እና መምህር የሆኑት ዶክተር ደምስ አላምረውም እንደሚሉት ደግሞ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን በተናገሩ ማግስት ጉብኝት ማድረጋቸው ቃላቸውን እየተገበሩ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
በጅቡቱ እና በሱዳን ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ከሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጋር የደረሱት ስምምነት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል ዶክተር ደምስ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅቡቲ ባደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ምጣኔ ሀብታዊ ውህደት የሚያፋጥኑ ስምምነቶችን የፈጸሙ ሲሆን፥ ከእነዚህ ስምምነቶች መካከልም በጅቡቲ ወደብ ኢትዮጵያ ድርሻ እንዲኖራት የሚያደርገው ስምምነት ቀዳሚው ነው።
በሱዳን በነበራቸው የሁለት ቀናት ጉብኝትም በተለያየ ምክንያት በሱዳን ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ የሚያደርገውን ስምምነት ከመፈራረማቸው አንስቶ፥ በሱዳን ወደብ ኢትዮጵያ ድርሻ እንዲኖራት የሚያደርግ ስምምነት ከፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ጋር ፈጽመዋል።
ኢትዮጵያ የወደብ ድርሻ እንዲኖራት ከስምምነት ላይ መደረሱ የሀገሪቱን የወጪ ገቢ ንግድ እንዲያድግና ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገራት ጋር የተፈራረመቻቸው የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የምጣኔ ሀብት ስምምነቶች ተግባር ላይ እንዲውሉ የራሱ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ሰሞነኛው አካሄድ በምስራቅ አፍሪካ ለመፍጠር የታሰበውን የጋራ ምጣኔ ሀብታዊ ውህደት የሚያፋጥንና ብሎም ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ይዞ እንደሚመጣም ገልጸዋል።
ከጠቀሜታዎቹ መካከል ሌሎች ሃገራት መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ፈሰስ በማድረግ መሰረተ ልማት እንዲስፋፋና የስራ እድል እንዲፈጠር እንደሚረዱም አስረድተዋል።
የምስራቅ አፍሪካን በተለይ የአፍሪካ ቀንድን ጂኦ ፖለቲክስ በቅርበት የሚከታተሉት ዶክተር በለጠ በላቸው፥ ከሁሉም በላይ ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጉብኝት የተገኘ አንድ ወሳኝ ውጤት አለ ይላሉ።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለምትፈልገው የውጭ ንግድ እንቅስቃሴዋ ተጨማሪ ጥንካሬ ይሆናታል ተብሎ ይጠበቃል።
ምሁራኑ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ እና በዓለም አቀፉ መድረክ ያላት ተሰሚነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው አሁንም ተጨማሪ የቤት ስራዎች ይጠብቋታል ብለዋል
Source:FBC(Fana Broadcasting Corporate)
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ